1እስራኤልም ጓዙን ሁሉ ጠቅልሎ ተነሣ፤ ቤርሳቤህም ሲደርስ፣ ለአባቱ ለይስሐቅ አምላክ መሥዋዕት ሠዋ።
2እግዚአብሔርም ሌሊት በራእይ ለእስራኤል ተገልጦ፣ “ያዕቆብ፣ ያዕቆብ” ብሎ ጠራው። እርሱም፣ “እነሆ፣ አለሁ” አለ።
3እግዚአብሔርም እንዲህ አለው፤ “እኔ የአባትህ አምላክ እግዚአብሔር ነኝ፤ ወደ ግብፅ ለመውረድ አትፍራ፤ በዚያ ታላቅ ሕዝብ አደርግሃለሁና፤
4አብሬህ ወደ ግብፅ እወርዳለሁ፣ ከዚያም መልሼ አወጣሃለሁ፣ የዮሴፍ የራሱ እጆች በምትሞትበት ጊዜ ዓይኖችህን ይከድናል።
5ከዚህ በኋላ ያዕቆብ ከቤርሳቤህ ተነሣ፤ የእስራኤል ወንዶች ልጆችም አባታቸውን ያዕቆብን ልጆቻቸውንና ሚስቶቻቸውን ፈርዖን ለያዕቆብ በላከላቸው ሠረገላ ላይ አወጧቸው።
6ከብቶቻቸውንና በከነዓን ምድር ያፈሩትን ሀብት ንብረታቸውን ይዘው፣ ያዕቆብና ዘሮቹ በሙሉ ወደ ግብፅ ወረዱ።
7ወደ ግብፅም የወረደው፤ ወንዶች ልጆቹንና ወንዶች የልጅ ልጆቹን፣ ሴቶች ልጆቹንና የልጅ ልጆቹን ማለት ዘሮቹን ሁሉ ይዞ ነው።
8ወድ ግብፅ የወረዱት የእስራኤል ልጆች፣ የያዕቆብ ዘሮቹ እነዚህ ናቸው፦ የያዕቆብ የበኩል ልጆ ሮቤል።
9የሮቤል ልጆች፦ ሄኖኅ፣ ፈሉሶ፣ አስሮን እና ከርሚ ናቸው።
10የስሞዖን ልጆች፦ ይሙኤል፣ ያሚን፣ ኦሃድ፣ ያኪን፣ ጸሐርና ከከነዓናዊቷ ሴት የተወለደው ሳኡል ናቸው።
11ልጆች፦ ጌድሶን፣ ቀዓትና ሜራሪ ናቸው።
12የይሁዳ ልጆች፦ ዔር አውናን፣ ሴሎም፣ ፋሬስ እና ዛራ ናቸው። ነገር ግን ዔርና አውናን በከነዓን ምድር ሞቱ።
13የይሳኮር ልጆች፦ ቶላ፣ ፉዋ፣ ዮብና ሺምሮን ናቸው፤
14የዛብሎን ልጆች፦ ሴሬድ፣ ኤሎንና ያሕልኤል ናቸው፤
15እነዚህ ወንዶች ልጆች ያዕቆብ በሰሜን ምዕራብ መሰጴጦምያ ሳለ፣ ልያ የወለደችለት ናቸው። ሴቷን ዲናን ጨምሮ፣ የወንዶችና የሴቶች ልጆቹ ቁጥር ሠላሳ ሦስት ነው።
16የጋድ ልጆች፦ ጽፎን፣ ሐጊ፣ ሹኒ፣ ኤስቦን፣ ዔሪ፣ አሮዲና አርኤሊ ናቸው፤
17የአሴር ልጆች፦ ዩምና፣ የሱዋ፣ የሱዊና በሪዓ ናቸው፤ እኅታቸውም ሤራሕ ናት፤ የበሪዓ ልጆች፦ ሐቤርና መልኪኤል ናቸው፤
18እነዚህ ዐሥራ ስድስት ልጆች ሁሉ ላባ ለልጁ ለልያ ከሰጣት ከዘለፋ ላይ ያዕቆብ የወለዳቸው ናቸው።
19የያዕቆብ ሚስት የራሔል ልጆች፦ ዮሴፍና ብንያም ናቸው፤
20በግብፅም የኦን ከተማ ካህን የጶጥፌራ ልጅ አስናት፣ ምናሴንና ኤፍሬምን ለዮሴፍ ወለደችለት።
21የብንያም ልጆች፦ቤላ፣ ቤኬር፣ አስቤል፣ ጌራ፣ ንዕማን፥ አኪ፣ ሮስ፥ ማንፌን፣ ሑፊምና አርድ ናቸው።
22እነዚህ ዐሥራ አራቱ፣ ራሔል ለያዕቆብ የወለደችለት ልጆችና የልጅ ልጆች ናቸው።
23የዳን ልጅ፦ ሑሺም ነው፤
24የንፍታሌም ልጆች፦ ያሕጽኤል፣ ጉኒ፣ ዮጽርና ሺሌም ናቸው፤
25እነዚህ ሰባቱ ልጆች ሁሉ ላባ ለልጁ ለራሔል ከሰጣት ከባላ ላይ ያዕቆብ የወለዳቸው ናቸው።
26ከያዕቆብ ጋር ወደ ግብፅ የሄዱት የገዛ ዘሮቹ ብዛት ስድሳ ስድስት ሲሆን የልጆቹን ሚስቶች አይጨምርም።
27ዮሴፍ በግብፅ የወለዳቸውን ሁለት ልጆች ጨምሮ ወደ ግብፅ የወረደው የያዕቆብ ቤተ ሰብ ቁጥር ሰባ ነበር።
28ያዕቆብም ወደ ጌሤም ለመሄድ መመሪያ ይቀበል ዘንድ፣ ይሁዳን አስቀድሞ ወደ ዮሴፍ ላከው። እርሱም ጌሤም ሲደርሱ፣
29ዮሴፍ ሠረገላውን አዘጋጅቶ፤ አባቱን እስራኤልን ለመቀበል ወደ ጌሤም አመራ። ዮሴፍ አባቱ ዘንድ እንደደረሰ አንገቱ ላይ ተጠምጥሞ ለረጅም ጊዜ አለቀሰ።
30እስራኤልም ዮሴፍን፣ “በሕይወት መኖርህን ስላየሁ፣ ከእንግዲህ ብሞትም አይቆጨኝም” አለው።
31ከዚህ በኋላ ዮሴፍ ወንድሞቹንና የአባቱን ቤተ ሰዎች እንዲህ አላቸው፤ “ወደ ፈርዖን ወጥቼ እነግረዋለሁ፤ እንዲህም እለዋለሁ፣ ‘በከነዓን ምድር የሚኖሩት ወንድሞቼና የአባቴ ቤተ ሰዎች ወደ እኔ መጥተዋል።
32ሰዎቹ ከብት የሚጠብቁ ስለሆኑ እረኞች ናቸው፣ ሲመጡም በጎቻቸውን፣ ፍየሎቻቸውንና ከብቶቻቸውን እንዲሁም ያላቸውን ሁሉ ይዘው መጥተዋል።
33ፈርዖን አስጠርቶአችሁ፣ ‘ሥራችሁ ምንድን ነው?’ ብሎ ቢጠይቃችሁ፤
34እናንተ፣ ‘እኛ አገልጋዮችህ ሥራችን ከልጅነታችን ጀምሮ ልክ እንደ አባቶቻችን ከብት ማርባት ነው’ ብላችሁ መልሱለት። ከብት አርቢዎች በግብፃውያን ዘንድ እንደ ጸያፍ ስለሚቆጠሩ፣ በጌሤም ምድር እንድትኖሩ ይፈቅድላችኋል።”