1በዚያን ጊዜ ዮሴፍ አጠገቡ በነበሩ ሰዎች ፊት ስሜቱን ሊገታ ባለመቻሉ፣ “እዚህ ያሉትን ሰዎች በሙሉ አስወጡልኝ” ብሎ ጮኾ ተናገረ፤ ስለዚህም ዮሴፍ ራሱን ለወንድሞቹ በገለጠበት ጊዜ ከእርሱ ጋር ሌላ ማንም ሰው አልነበረም።
2ዮሴፍም ድምፁን ከፍ አድርጎ በማልቀሱ ግብፃውያን ሰሙት፣ ወሬውም ወደ ፈርዖን ቤተ ሰዎች ደረሰ።
3ዮሴፍም ወንድሞቹን፣ “እኔ ዮሴፍ ነኝ፤ ለመሆኑ አባቴ እስካሁን በሕይወት አለ?” ሲል ጠየቃቸው። ወንድሞቹ ግን በፊቱ ተደናግጠው ስለነበር መልስ ሊሰጡት አልቻሉም።
4ዮሴፍም ወንድሞቹን፣ “እስቲ ወደ እኔ ቀረብ በሉ” አላቸው፣ ወደ እርሱም በቀረቡ ጊዜ እንዲህ አለ፤ “ወደ ግብፅ የሸጣችሁኝ እኔ ዮሴፍ ነኝ፤
5አሁንም በመሸጣችሁ አትቆጩ፤ በራሳችሁም አትዘኑ፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር ሕይወት ለማዳን ሲል ከእናንተ አስቀድሞ እኔን ወደዚህ ልኮኛል።
6በምድር ላይ ራብ ከገባ ይኸው ሁለት ዓመት ሆነ፣ ከዚህ በኋላም የማይታረስባቸውና ሰብል የማይሰበሰብባቸው አምስት ዓመታት ገና አሉ።
7ነገር ግን እግዚአብሔር ሕይወታችሁን በታላቅ ማዳን ለመታደግና ዘራችሁ ከምድር ላይ እንዳይጠፋ በማሰብ ከእናንተ አስቀድሞ ወደዚህ ላከኝ።
8ስለዚህ አሁን ወደዚህ የላከኝ እግዚአብሔር እንጂ እናንተ አይደላችሁም፣ እርሱም ለፈርዖን እንደ አባት፤ በቤት ንብረቱ ላይ ጌታ፣ እንዲሁም በግብፅ ምድር ላይ ገዢ አደረገኝ።
9አሁንም ‘በፍጥነት ወደ አባቴ ተመልሳችሁ እንዲህ በሉት፤ “ልጅህ ዮሴፍ እንዲህ ይላል፤ ‘እግዚአብሔር የመላው ግብፅ ጌታ አድርጎኛል፤ ስለዚህ ሳትዘገይ ወደ እኔ ና።
10ልጆችህን የልጅ ልጆችህን በጎችህን፣ ፍየሎችህን ከብቶችህንና ያለህን ሁሉ ይዘህ በአቅራቢያዬ በጌሤም ትኖራለህ።
11ገና ወደ ፊት የሚመጣ የአምስት ዓመት ራብ ስላለ፣ በዚያ የሚያስፈልጋችሁን እኔ እሰጣችኋለሁ፤ ያለበልዚያ ግን አንተና ቤተ ስዎችህ ያንተም የሆነው ሁሉ፣ ችግር ላይ ትወድቃላችሁ።’
12ፊታችሁ ሆኜ የማናግራችሁ እኔ ዮሴፍ ራሴ መሆኔን እናንተም ሆናችሁ ወንድሜ ብንያም በዓይናችሁ የምታዩት ነው።
13በግብፅ ስላሏኝ ክብርና ስላያችሁትም ሁሉ ለአባቴ ንገሩት፣ አባቴንም በፍጥነት ይዛችሁት ኑ።
14ከዚያም በወንድሙ በብንያም አንገት ላይ ተጠምጥሞ አለቀሰ፤ ብንያምም እያለቀሰ ዮሴፍን አቀፈው።
15የቀሩትምንም ወንድሞቹን አንድ በአንድ እየሳመ አለቀሰ። ከዚያም ወንድሞቹ ከእርሱ ጋር መጨዋወት ጀመሩ።
16የዮሴፍ ወንድሞች መምጣት በፈርዖን ቤተ መንግሥት በተሰማ ጊዜ፣ ፈርዖንና ሹማምንቱ ሁሉ ደስ አላቸው።
17ፈርዖን ዮሴፍን እንዲህ አለው፤ “ለወድሞችህ እንዲህ ብለህ ንገራቸው፣ ‘እንዲህ አድርጉ እህዮቻችሁን ጭናችሁ ወደ ከነዓን ምድር ተመለሱ።
18ከዚያም አባታችሁንና ቤተ ሰባችሁን ይዛችሁ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም እጅግ ለም ከሆነው የግብፅ ምድር እሰጣችኋለሁ፤ በምድሪቱ በረከት ደስ ብሎአችሁ ትኖራላችሁ።’
19ደግሞም እንዲህ ብለህ እዘዛቸው፤ ‘ይህን አድርጉ፣ ከግብፅ ምድር ልጆቻችሁንና ሚስቶቻችሁን የምታጓጉዙባቸው ሠረገላዎች ወስዳችሁ፤ አባታችሁን ይዛችሁ ኑ።
20ስለ ንብረታችሁ ምንም አታስቡ፣ ከግብፅ ምድር እጅግ ለም የሆነው የእናንተ ይሆናልና።’”
21የእስራኤልም ልጆች ይህንኑ አደረጉ። ዮሴፍም ፈርዖን ባዘዘው መሠረት ሠረገላዎች አቀረበላቸው፤ የመንገድም ስንቅ አስያዛቸው።
22ለእያንዳንዳቸው ሁለት ሁለት የክት ልብስ ሰጣቸው፤ ለብንያም ግን ሶስት መቶ ጥሬ ብርና አምስት የክት ልብስ ሰጠው።
23ለአባቱም በግብፅ ምድር ከሚገኘው የተመረጠ ነገር በዐሥር አህዮች፣ እንደዚሁም በዐሥር እንስት አህዮች ዳቦና ሌላ ምግብ አስጭኖ ሰደደለት።
24ከዚህ በኋላ ወንድሞቹን አሰናበታቸው፤ ከእርሱም ሲሰናበቱ፣ መንገድ ላይ እንዳትጣሉ” አላቸው።
25እነርሱም ከግብፅ ወጥረው በከነዓን ምድር ወደሚኖረው ወደ አባታቸው ወደ ያዕቆብ መጡ።
26አባታቸውንም፣ እነሆ ዮሴፍ በሕይወት አለ፤ እንዲያውም በግብፅ ምድር ሁሉ ገዥ ሆኖአል” ብለው ነገሩት። ያዕቆብ ግን እጅግ ደነገጠ፤ ሊያምናቸውም አልቻለም።
27ነገር ግን ዮሴፍ ያላቸውን ሁሉ በነገሩት ጊዜና እርሱን ወደ ግብፅ የሚወስዱበትን ዮሴፍ የላከለትን ሠረገላ ባየ ጊዜ የአባታቸው የያዕቆብ መንፈስ ታደሰ።
28ከዚያም እስራኤል፣ “ልጄ ዮሴፍ በሕይወት አለ፤ ከመሞቴ በፊት ሄጄ ዐየዋለሁ” አለ።