መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ኦሪት ዘፍጥረት 44

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ከዚህ በኋላ ዮሴፍ ለቤቱ አዛዥ እንዲህ ሲል መመሪያ ሰጠው፤ የሰዎቹ ስልቻ የሚይዘውን ያህል እህል በየስልቻቸው ሙላላቸው፤ የእያንዳንዱንም ገንዘብ በየስልቻው አፍ አስቀምጠው።
2ከዚያም የብር ዋንጫዬን በታናሹ ወንድማቸው ስልቻ አፍ ከእህሉ ዋጋ ጋር ጨምረው።” አዛዡም ዮሴፍ እንዳለው አደረገ።
3ጠዋት በማለዳ ወንድማማቾቹ አህዮቻቸውን ይዘው እንዲሄዱ ተደረገ።
4ከከተማውም ምንም ያህል ርቀው ሳይሄዱ፣ ዮሴፍ የቤቱን አዛዥ እንዲህ አለው፤ “እነዚያን ሰዎች ቶሎ ድረስባቸውና፣ ‘በመልካም ፋንታ ክፉ የመለሳችሁት ስለ ምንድን ነው?
5የጌታዬን የብር ዋንጫ የሰረቃችሁት ለምንድነው? ዋንጫው ጌታዬ የሚጠጣበትና ሁሉን ነገር መርምሮ የሚያውቅበት እንደሆነ አታውቁምን? ይህ ያደረሳችሁት በደል እጅግ ከባድ ነው’ ብለህ ነገራቸው።”
6የቤቱ አዛዥም እንደደረሰባቸው፣ ልክ እንደተባለው ተናገራቸው።
7እነርሱ ግን እንዲህ አሉት፤ “ጌታችን እንዲህ ያለ ነገር ለምን ይናገራል? እኛ አገልጋዮችህ እንዲህ ያለውን ነገር አናደርገውም።
8ከዚህ ቀደምም በየስልቾቻችን አፍ የተገኘውን ብር ከከነዓን እንኳ መልሰን አምጥተናል፤ ታዲያ አሁን ብር ወይም ወርቅ ከጌታህ ቤት እንዴት እንሰርቃለን?
9የጠፋው ዕቃ ከአገልጋዮችህ የተገኘበት ይሙት፤ የቀረነው የጌታችን ባሮች እንሁን።”
10አዛዡም መልካም ነው፤ እንዳላችሁት ይሁን፤ ጽዋው የተገኘበት ሰው ባሪያዬ ይሆናል፤ የቀራችሁት ግን ከበደል ነጻ ትሆናላችሁ” አላቸው።
11ስለዚህ በፍጥነት ስልቻዎቻቸውን አወረዱ፤ እያንዳንዱም የራሱን ስልቻ ከፈተ።
12ከዚያም አዛዡ ፍተሻውን ከታላቁ ጀምሮ እስከ ታናሹ ድረስ ቀጠለ። በመጨረሻም ጽዋው በብንያም ስልቻ ውስጥ ተገኘ።
13በዚህ ጊዜ ልብሶቻቸውን በሐዘን ቀደዱ፤ ሁሉም ስልቾቻቸውን በየአህዮቻቸው ጭነው ወደ ከተማይቱ ተመለሱ።
14ይሁዳና ወንድሞቹ ወደ ዮሴፍ ቤት ሲገቡ፣ ዮሴፍ ገና ከቤቱ አልወጣም ነበር። እነርሱም በፊቱ ተደፍተው ሰገዱ።
15ዮሴፍም፣ “ለምን እንዲህ ያለ ነገር አደረጋችሁ? እንደ እኔ ያለ ሰው ስውር ነገርን የሚያውቅበት ልዩ ጥበብ እንዳለው አታውቁምን?” ሲል ጠየቃቸው።
16ይሁዳም፣ “ከእንግዲህ ለጌታችን ምን ማለት እንችላለን? ምንስ እንመልሳለን? እንዲህ ካለው በደል ንጹሕ መሆናችንን ማስረዳትስ እንዴት ይቻለናል? ምክንያቱም እግዚአብሔር የሠራነውን በደል ገልጦታል፤ እንግዲህ ዋንጫው የተገኘበት ሰው ብቻ ሳይሆን ሁላችንም ባሪያዎችህ እንሁን” አለ።
17ዮሴፍም፣ “ይህንስ አላደርገውም፣ ዋንጫው የተገኘበት ሰው ብቻ የእኔ ባሪያ መሆን አለበት፤ ሌሎቻችሁ በሰላም ወደ አባታችሁ መመለስ ትችላላችሁ” አለ።
18ይሁዳም ወደ ዮሴፍ ቀረብ ብሎ፣ “ጌታዬ ሆይ፣ እኔ አገልጋይህ አንዲት ቃል ብቻ ልናገር፣ ምንም እንኳ የፈርዖን ያህል የተከበርክ ብትሆንም እባክህ አትቆጣኝ።
19ጌታዬ፣ ‘አባት ወይም ወንድም አላችሁ?’ ብሎ አገልጋዮቹን ጠይቆ ነበር።
20እኛም፣ ‘አዎን ሽማግሌ አባት አለን፤ አባታችንም በስተርጅና የወለደው ትንሽ ልጅ አለው፣ ወንድምዬው ሞቶአል፣ ከአንድ እናት ከተወለዱት ልጆች መካከል የተረፈው እርሱ ብቻ ነው፤ አባቱም በጣም ይወደዋል’ ብለንህ ነበር።
21ከዚያም አንተ አገልጋዮችህን፣ ‘እንዳየው ወደ እኔ አምጡት’ አልኸን።
22እኛም ለጌታዬ፣ ‘ልጁ ከአባቱ ሊለይ አይችልም፤ ከተለየው ደግሞ አባትዬው ይሞታል’ አልንህ።
23አንተ ግን እኛን አገልጋዮችህን፣ ‘ታናሽ ወንድማችሁ አብሮአችሁ ወደዚህ ካልመጣ ዳግመኛ ፊቴን ዐታዩም’ አልኸን።
24እኛም ወደ አገልጋይህ ወደ አባቴ በተመለስን ጊዜ አንተ ጌታዬ ያልኸንን ነገርነው።
25ከዚያም አባታችን፣ ‘እስቲ ተመልሳችሁ ጥቂት እህል ሸምቱልን’ ሲለን
26‘መሄድ አንችልም፤ መሄድ የምንችለው ታናሽ ወንድማችን አብሮን ሲሄድ ብቻ ነው። ታናሽ ወንድማችንን ይዘን ካልሄድን በስተቀር የሰውዬውን ፊት ማየት አንችልም’ አልነው።
27አገልጋይህ አባቴም እንዲህ አለን፤ ‘ሚስቴ ሁለት ወንዶች ልጆች እንደወለደችልኝ ታውቃላችሁ፤
28አንዱ በወጣበት በመቅረቱ በእርግጥ አውሬ በልቶት ይሆናል አልሁ፣ ከዚያ በኋላ ዐላየሁትም።
29አሁን ደግሞ ይህን ልጅ ወስዳችሁ አንዳች ጉዳት ቢደርስበት ሽበቴን በመራር ሐዘን ወደ መቃብር ታወርዱታላችሁ።’
30እንግዲህ አሁን ልጁን ሳንይዝ ወደ አገልጋይህ ወደ አባቴ ብመለስ ሕይወቱ ከልጁ ሕይወት ጋር በጥብቅ የተሳሰረ ስለሆነ፣
31የልጁን ከእኛ ጋር አለመኖር ሲያይ አባቴ ይሞታል። ከዚህም የተነሣ እኛ አገልጋዮችህ የአባታችንን ሽበት በመሪር ሐዘን ወደ መቃብር እናወርደዋለን።
32እኔ አገልጋይህ፣ “ልጅህን መልሼ ሳላመጣ ብቀር ለዘላለም በደለኛ አድርገህ ቁጠረኝ’ በማለት ስለ ልጁ ደህንነት በአባቴ ፊት ራሴን ዋስ አድርጌአለሁ።
33ስለዚህ አሁን፣ አገልጋይህ በልጁ ፋንታ የአንተ የጌታዬ ባሪያ ሆኜ እዚሁ ልቅር ልጁ ግን ከወንድሞቹ ጋር ይመለስ።
34ልጁን ሳልይዝ እንዴት ተመልሼ ወደ አባቴ እሄዳለሁ? እባክህ በአባቴ ላይ የሚደርሰውን መከራ እንዳይ አታድርገኝ።”
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።