መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ኦሪት ዘፍጥረት 43

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1አሁንም በምድሪቱ ላይ እንደጸና ነበር፤
2ከግብፅ ያመጡትንም እህል በልተው ከጨረሱ በኋላ፣ አባታቸው፣ “እስቲ እንደገና ወርዳችሁ፣ ጥቂት እህል ሸምቱልን” አላቸው።
3ይሁዳ ግን እንዲህ አለው፤ “ ያ ሰው ወንድማችሁን ይዛችሁ ካልመጣችሁ ዳግመኛ ፊቴን ዐታዩም ብሎ በጥብቅ አስጠንቅቆናል፤
4ወንድማችን ከእኛ ጋር እንዲወርድ ከፈቀድህ ወደዚያ ሄደን እህል እንሸምትልሃለን፤
5እርሱን የማትልከው ከሆነ ግን እኛም ወደዚያ አንወርድም፤ ያም ሰው፣ ‘ወንድማችሁን ይዛችሁ ካልመጣችሁ ዳግመኛ ፊቴን ዐታዩም’ ብሎናል።”
6እስራኤልም፣ “ሌላ ወንድም አለን ብላችሁ ለዚያ ሰው በመንገር ለምን ይህን ችግር እንዲደርስብኝ አደረጋችሁ?” ሲል ጠየቃቸው።
7እነርሱም፣ “ሰውዬው ስለ ራሳችንና ስለ ቤተ ሰባችን አጥብቆ ጠየቀን፤ እንደገናም ‘አባታችሁ አሁንም በሕይወት አለ? ሌላስ ወንድም አላችሁ?’ ሲል ጠየቀን። እኛም ለጥያቄው መልስ ሰጠነው። ታዲያ፣ ‘ወንድማችሁን ይዛችሁ ወደዚህ እንድትመጡ’ እንደሚል እንዴት ማወቅ እንችል ነበር?” ብለው መለሱለት።
8ይሁዳም አባቱን እስራኤልን እንዲህ አለው፣ “ልጁን ከእኔ ጋር ስደደው፤ እኛም በቶሎ እንሂድ፣ ይህ ከሆነ አንተም፣ እኛም፣ ልጆቻችንም አንሞትም፣ እንተርፋለን።
9ስለ ልጁ ደኅንነት እኔ ራሴ ኃላፊ ነኝ፤ ስለ እርሱም በግል ተጠያቂ እሆናለሁ፤ እርሱንም በደኅና መልሼ ባላመጣውና እዚህ በፊትህ ባላቆመው ለዘላለም በደለኛ እኔ ልሁን።
10ይህን ያህል ባንዘገይ ኖሮ፣ እስካሁን ሁለት ጊዜ ደርሰን መመለስ በቻልን ነበር።”
11ከዚህ በኋላ አባታቸው እስራኤል እንዲህ አላቸው፤ “ነገሩ እንዲህ ከሆነስ ይህን አድርጉ፣ ምድሪቱ ከምታፈራቸው ምርጥ ነገሮች ጥቂት በለሳን፣ ጥቂት ማር፣ ሽቱ፣ ከርቤ፣ ተምርና ለውዝ በየስልቻችሁ ይዛችሁ ለዚያ ሰው ስጦታ ውሰዱለት።
12በየስልቾቻችሁ አፍ ላይ የተገኘውን ብር መመለስ ስላለባችሁ፣ ዕጥፍ ገንዘብ ያዙ፤ ያ በየስልቾቻችሁ ውስጥ የተገኘው ብር ምናልባት በስሕተት የመጣ ሊሆን ይችላል።
13ወንድማችሁንም ይዛችሁ ወደ ሰውዬው በቶሎ ሂዱ።
14ሌላውን ወንድማችሁንና ብንያምን ይዛችሁ ለመመለስ እንድትችሉ ሁሉን የሚችል አምላክ በምሕረቱ የዚያን ሰው ልብ ያራራላችሁ። እኔ በበኩሌ ልጆቼን ካጣሁ፣ ባዶ እጄን መቅረቴ ነው።”
15ስለዚህ ወንድማማቾቹ ገጸ በረከቱንና ዕጥፍ ገንዘብ ይዘው ከብንያም ጋር ወደ ግብፅ ለመሄድ ጉዞ ጀመሩ፤ እዚያም በደረሱ ጊዜ ዮሴፍ ፊት ቀረቡ።
16ዮሴፍ ብንያምን ከወንድሞቹ ጋር ባየው ጊዜ የቤቱን አዛዥ፣ “እነዚህን ሰዎች ወደ ቤት ይዘሃቸው ሂድ፣ ዛሬ ቀትር ላይ አብረውኝ ስለሚበሉ አንድ ከብት እረድና አዘጋጅ” አለው።
17አዛዡም ዮሴፍ የነገረውን አደረገ፣ ሰዎቹንም ወደ ዮሴፍ ቤት ወሰዳቸው።
18ሰዎቹም ወደ ዮሴፍ ቤት በመወሰዳቸው ፈሩ፤ እነርሱም፣ “ወደዚህ የመጣነው ቀደም ሲል እዚህ መጥተን ስንመለስ በየስልቾቻችን ውስጥ ተመልሶ በተጨመረው ብር ሰበብ ነው። ሰውዬው ሊያስረንና ባሪያዎች ሊያደርገን አህዮቻችንንም ሊወስድ ይችላል።”
19ወደ ዮሴፍ ቤት አዛዥ ቀርበው፣ በቤቱ መግቢያ ላይ አነጋገሩት፤
20እንዲህም አሉት፤ “ለመጀመሪያ ጊዜ እህል ለመሸመት ወደዚህ መጥተን ነበር፤
21ነገር ግን ለአዳር በሰፈርንበት ቦታ የየስልቾቻችንን አፍ ስንከፍት እያንዳንዳችን በስልቾቻችን አፍ ላይ ብራችንን ሙሉውን አገኘነው። ገንዘቡንም ይኸው መልሰን ይዘን መጥተናል።
22አሁንም እህል መሸመት የሚሆነን ተጨማሪ ብር ይዘን መጥተናል፤ በዚያን ጊዜ ገንዘቡን በየስልቾቻቸን ውስጥ ማን መልሶ እንዳስቀመጠው ግን አናውቅም” አሉት።
23የቤቱ አዛዥም፣ “አይዞአችሁ አትፍሩ፣ በየስልቾቻችሁ ውስጥ ያገኛችሁትን ገንዘብ የሰጣችሁ የእናንተም የአባቶቻችሁም አምላክ ነው፤ እኔ እንደሆንሁ ብሩን ተቀብያለሁ” አላቸው። ከዚያም ስምዖንን አውጥቶ አገናኛቸው።
24የቤቱ አዛዥ ሰዎቹን ወደ ዮሴፍ ቤት አስገብቶ እግራቸውን የሚታጠቡበት ውሃ አቀረበላቸው፤ ለአህዮቻቸውም የሚበሉት ገፈራ ሰጣቸው።
25ምሳ በዚያ እንደሚበሉ ተነገሯቸው ስለነበር፣ ዮሴፍ በቀትር ከመግባቱ በፊት እጅ መንሻዎቻቸውን ለማበርከት ተዘጋጁ።
26ዮሴፍም ወደ ቤቱ ሲገባ የመጧቸውን ስጦታዎች አበረከቱለት፤ ወደ መሬት ዝቅ ብለውም እጅ ነሡት።
27ዮሴፍም ስለ ደኅንነታቸው ጠየቃቸው፣ ከዚያም፣ “ሽማግሌ አባት እንዳላችሁ ነግራችሁኝ ነበር፤ ደኅና ነው? አሁንም በሕይወት አለ?” አላቸው።
28እነርሱም መልሰው፣ “አገልጋይህ አባታችን አሁንም በሕይወት አለ፤ ደኅና ነው” በማለት ወደ መሬት ዝቅ ብለው እጅ ነሡት።
29ዮሴፍ በዓይኑ ሲቃኝ የእናቱን ልጅ ብንያምን ዐየና፣ “ያ የነገራችሁኝ ታናሽ ወንድማችሁ ይህ ነው?” ብሎ ጠየቃቸው። ብንያምንም፣ “ልጄ እግዚአብሔር ይባርክህ” አለው።
30ዮሴፍ ወንድሙን በማየቱ ስሜቱ በጥልቅ ስለተነካ፣ ፈጥኖ ከፊታቸው ገለል አለ፤ ሰውር ያለ ቦታም ፈልጎ፣ ዕልፍኙ ውስጥ አለቀሰ።
31ፊቱንም ከታጠበ በኋላ ወጣ፤ ስሜቱንም በመቆጣጠር ምሳ እንዲቀርብ አዘዘ።
32ለዮሴፍ ለብቻው ቀረበለት ለወንድሞቹም ለብቻቸው ቀረበላቸው፤ እንዲሁም ከእርሱ ጋር ለሚበሉት ግብፃውያን ደግሞ ሌላ ገበታ ቀረበላቸው፤ ምክንያቱም ግብፃውያን ከዕብራውያን ጋር አብሮ መመገብን እንደጸያፍ ይቆጥሩት ነበር።
33ወንድማማቾቹ ከታላቁ አንስቶ እስከታናሹ እንደየዕድሜአቸው በዮሴፍ ፊት በተርታ ተቀምጠው ነበር፤ በመገረምም እርስ በርሳቸው ተያዩ።
34ከዮሴፍ ገበታ ላይ እየተነሣ ለእያንዳንዳቸው ምግብ ሲቀርብ የብንያም ድርሻ ከሌሎቹ አምስት ዕጥፍ ነበር። እነርሱም እንዲህ ባለ ሁኔታ አብረውት ተደሰቱ እስኪረኩም ጠጡ።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።