1በግብፅ እህል መኖሩን ሲሰማ፣ ልጆቹን እንዲህ አላቸው፤ “ለምን እርስ በርስ ትተያያላችሁ?”
2በግብፅ አገር እህል መኖሩን ሰምቻለሁ፤ በራብ ከመሞታችን በፊት ወደዚያ ሂድና እህል ግዙልን” አላቸው።
3ስለዚህ ዐሥሩ የዮሴፍ ወንድሞች እህል ለመግዛት ወደ ግብፅ ሄዱ።
4ነገር ግን ያዕቆብ የዮሴፍን ወንድም ብንያምን ክፉ ነገር ይደርስበታል በሚል ፍርሃት ከወንድሞቹ ጋር አልላከውም።
5ራቡ በከነዓንም በመበርታቱ፣ እህል ለመሸመት ወደ ግብፅ ከሄዱት መካከል የእስራኤል ልጆችም ነበሩ።
6በዚህ ጊዜ ዮሴፍ የምድሪቱ ገዢ ነበር፣ ለአገሩ ሰዎች ሁሉ እህል የሚሸጥላቸው እርሱ ነበር። የዮሴፍ ወንድሞችም እንደደረሱ ከፊቱ ቀርበው ወደ ምድር ለጥ ብለው ሰገዱለት።
7ዮሴፍም ወንድሞቹን ባየ ጊዜ ዐወቃቸው፣ ነገር ግን የማያውቃቸው በመምሰል በቁጣ ቃል፣ “ከየት ነው የመጣችሁት?” ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱም፣ “እህል ለመሸመት ከከነዓን ምድር የመጣን ነን" ብለው መለሱለት።
8ዮሴፍ ወንድሞቹን ቢያውቃቸውም እንኳ እነርሱ ግን አላወቁትም።
9በዚህ ጊዜ ስለወንድሞቹ ያየው ሕልም ትዝ አለውና፣ “ሰላዮች ናችሁ፣ የመጣችሁት አገራችን በየትኛው በኩል ለጥቃት የተጋለጠች መሆኗን ለመሰለል ነው” አላቸው።
10እነርሱም እንዲህ አሉት፤ “ጌታችን ሆይ፣ እንዲህስ አይደለም፤ እኛ አገልጋዮችህ የመጣነው እህል ለመሸመት ነው፤
11ሁላችንም የአንድ አባት ልጆች ነን፤ አገልጋዮችህም የታመንን ሰዎች እንጂ ሰላዮች አይደለንም።”
12እርሱም መልሶ፣ “አይደለም፣ ግብፅ በየት በኩል ለጥቃት የተጋለጠች መሆኗን ለመሰለል ነው” አላቸው።
13እነርሱ ግን መልሰው፣ “እኛ አገልጋዮችህ በከነዓን አገር ከሚኖር ከአንድ ሰው የተወለድን ዐሥራ ሁለት ወንድማማቾች ነን። ትንሹ ወንድማችን አባታችን ዘንድ ሲሆን አንዱ ወንድማችን ሞቷል።
14ዮሴፍም እንዲህ አላቸው፤ “ነገርኋችሁ እኮ፤ ሰላዮች ናችሁ
15ታናሽ ወንድማችሁ እዚህ እስካልመጣ ድረስ ከዚህ ንቅንቅ እንደማትሉ በፈርዖን ስም እምላልሁ፤ ማንነታችሁ የሚረጋገጠውም በዚህ ነው።
16ከእናንተ አንዱ ሄዶ ወንድማችሁን ያምጣ፤ የተናገራችሁትም እውነት መሆኑ ተረጋግጦ ነጻ እስክትለቀቁ ድረስ የቀራችሁት እዚሁ በእስት ቤት ትቆያላችሁ፤”
17ሁሉንም ሦስት ቀን በእስር አቆያቸው።
18በሦስተኛውም ቀን ዮሴፍ እንዲህ አላቸው፤ “እኔ እግዚአብሔርን ስለምፈራ እንዲህ በማድረግ ሕይወታችሁን አትርፉ።
19ታማኝ ሰዎች ከሆናችሁ፣ ከመካከላችሁ እንዱ እዚህ እስር ቤት ሲቆይ፣ የቀራችሁት ግን ለተራቡት ቤተ ሰቦቻችሁ እህል ትወስዱላቸዋላችሁ፤
20ታናሽ ወንድማችሁን ግን ይዛችሁ መምጣት አለባችሁ፤ በዚህም የተናገራችሁት ቃል እውነተኛነት ይረጋገጣል፤ እናንተም ከመሞት ትተርፋላችሁ።” እነርሱም ይህንኑ ለመፈጸም ተስማሙ።
21እርስ በርሳቸውም እንዲህ ተባባሉ፤ “በእርግጥ በወንድማችን ላይ ስላደረስነው በደል ቅጣታችንን እየተቀበልን ነው። እርሱ እንደዚያ ተጨንቆ ስለ ሕይወቱ ሲማጠነን፣ እኛ አልሰማነውም ነበር፤ ይህ መከራ የደረሰብንም በዚሁ ምክንያት ነው” ተባባሉ።
22ሮቤልም መልሶ፣ “በዚህ ልጅ ላይ ክፉ ነገር እንዳታደርጉ ብዬ አልነበረምን? እናንተ ግን አልሰማችሁኝም፤ ስለዚህም ደሙ ከእጃችን ይፈለጋል” አላቸው።
23ዮሴፍ የሚያነጋግራቸው በአስተርጓሚ ስለሆነ የሚነጋገሩትን እንደሚሰማባቸው ዐላወቁም ነበር።
24ከፊታቸውም ዘወር ብሎ አለቀሰ፤ ከዚያም ወደእነርሱ ትመልሶ እንደገና አነጋገራቸው፤ ስምዖንንም ከእነርሱ ለይቶ ዓይናቸው እያየ አሰረው፤
25ዮሴፍ ለአገልጋዮቹ በስልቻዎቻቸው እህል እንዲሞሉላቸው፤ ብሩንም በያንዳንዱ ሰው ስልቻ ውስጥ መልሰው እንዲያስቀምጡና ለጉዞአቸው ስንቅ እንዲያሲዟቸው ትእዛዝ ሰጠ። ይህም ተደረገላቸው።
26እነርሱም እህላቸውን በአህዮቻቸው ጭነው ጉዞአቸውን ቀጠሉ።
27በመንገድም ለአዳር ሰፍረው ሳለ፣ ከእነርሱ አንዱ ከያዘው እህል ላይ ለአህያው ለመስጠት ስልቻውን ሲፈታ፣ በስልቻው አፍ ላይ ብሩን አገኘ።
28እርሱም ወንድሞቹን፣ “ኧረ ብሬ ተመልሶልኛል፤ ይኸው ስልቻዬ ውስጥ አገኘሁት” አላቸው። ሁሉም ልባቸው በድንጋጤ ተሞልቶ እየተንቀጠቀጡ በመተያየት፣ “እግዚአብሔር ምን ሊያመጣብን ይሆን?” አሉ።
29በከነዓን ምድር ወዳለው ወደ አባታቸው ወደ ያዕቆብ ከደረሱ በኋላ ያጋጠማቸውን ሁሉ እንዲህ ብለው ነገሩት፤
30“የግብፅ አገር አስተዳዳሪ ‘አገሬን ልትሰልሉ የመጣችሁ ናችሁ’ በማለት በቁጣ ቃል ተናገረን፤
31እኛ ግን እንዲህ አልነው፤ “እኛ የታመንን ሰዎች እንጂ ሰላዮች አይደለንም።
32እኛ የአንድ አባት ልጆች የሆንን ዐሥራ ሁለት ወንድማማቾች ነን፣ አንዱ የለም፣ ታናሽ ወንድማችን ግን ከአባታችን ጋር በከነዓን ይገኛል።’
33ከዚህ በኋላ የአገሩ ጌታ የሆነው ሰው እንዲህ አለን፣ “ታማኝ ሰዎች መሆናችሁን የማውቀው በዚህ ነው ከእናንተ መካከል አንዱን ወንድማችሁን እዚህ እኔ ዘንድ ትታችሁ የተቀራችሁት ለትራቡት ቤተ ሰቦቻችሁ እህል ይዛችሁላቸው ሂዱ።
34ነገር ግን ታናሽ ወንድማችሁን ወደ እኔ አምጡት። በዚያን ጊዜም ታማኝ ሰዎች እንጂ ሰላዮች አለመሆናችሁን ዐውቃለሁ፤ ወንድማችሁንም መልሼ እሰጣችኋለሁ፤ እናንተም በምድሪቱ እንደፈለጋችሁ እየተዘዋወራችሁ መነገድ ትችላላችሁ።
35እህሉንም ሲዘረግፉ በየስልቻቸው ውስጥ ብራቸው እንደተቋጠረ ተገኘ፤ የእያንዳንዳቸውን የተቋጠረ ብር ሲያዩም፣ እነርሱም ሆኑ አባታቸው ደነገጡ።
36አባታቸው ያዕቆብም፣ “ያለ ልጅ እኮ አስቀራችሁኝ፣ ዮሴፍ የለም፣ ስምዖንም የለም፤ አሁን ደግሞ ብንያምን ልትወስዱ ትፈልጋላችሁ፤ በዚህ ሁሉ መከራ የምሠቃየው እኔ ነኝ” አለ።
37በዚህን ጊዜ ሮቤል አባቱን፣ “ብንያምን ወደ አንተ መልሼ ባላመጣው ሁለቱን ወንዶች ልጆቼን ወስደህ ግደላቸው፣ ስለዚህ በእኔ ኃላፊነት ላከው፤ እኔም መልሼ አመጣዋለሁ” እለው።
38ያዕቆብም “ምንም ቢሆን ከእናንተ ጋር አይሄድም፤ ወንድሙ ሞቶአል፣ የቀረው እርሱ ብቻ ነው፤ በመንገድ አንድ ጉዳት ቢደርስበት በእርጅናዬ ዘመን በመሪር ሐዘን ወደ መቃብር እንድወርድ ታደርጉኛላችሁ” አላቸው።