መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ኦሪት ዘፍጥረት 41

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ድፍን ሁለት ዓመት ካለፈ በኋላ ፈርዖን ሕልም ዐለም፤ ሕልሙም በዓባይ ወንዝ ዳር ቆሞ ነበር፤
2እነሆ፣ መልካቸው ያማረ፣ ሥጋቸው የወፈረ ሰባት ላሞች ከወንዙ ወጥተው በወንዙ ዳር የበቀለውን ሣር ይበሉ ጀመር።
3ቀጥሎም መልካቸው የከፋ አጥንታቸው የወጣ ሌሎች ሰባት ላሞች ከወንዙ ወጥተው አስቀድመው ከወጡት ላሞች አጠገብ ቆሙ።
4እነዚህ መልካቸው የከፋና አጥንታቸው የወጣ ላሞች፥ እነዚያን ያማሩና የወፈሩ ላሞች ሲውጡአቸው ዐየ፤ ከዚያም ፈርዖን ከእንቅልፉ ነቃ።
5ፈርዖንም እንደገና እንቅልፍ ወስዶት ሳለ ሌላ ሕልም ዐየ። በሕልሙም በአንድ የእህል አገዳ ላይ ሰባት የዳበሩና ያማሩ የእሸት ዛላዎች ዐየ፤
6ቀጥሎም የቀጨጩና ከበረሐ በተነሣ የምሥራቅ ነፋስ ተመትተው የደረቁ ሰባት የእሸት ዛላዎች ወጡ።
7የቀጨጩት የእሸት ዛላዎች፤ ሰባቱን የዳበሩና ያማሩ የእሸት ዛላዎች ዋጡአቸው፤ በዚህ ጊዜ ፈርዖን ከእንቅልፉ ነቃ፣ ነገሩ ሕልም ነበር።
8በነጋታውም ፈርዖን መንፈሱ ታወከበት፣ ስለዚህ በግብፅ አገር ያሉትን አስማተኞችና ጥበበኞች በሙሉ አስጠርቶ ሕልሞቹን ነገራቸው፣ ይሁን እንጂ፣ ሕልሞቹን ሊተረጉምለት የቻለ አንድም ሰው አልተገኘም።
9በዚያን ጊዜ የመጠጥ አሳላፊዎቹ አለቃ ፈርዖንን እንዲህ አለው፤ “የሠራሁት በደል ዛሬ ታወሰኝ።
10ፈርዖን ሆይ! አንተ በእኔና በእንጀራ ቤት ኃላፊው ላይ ተቆጥተህ በዘበኞች አለቃ ቤት እንድንታሰር አድርገህ ነበር፤
11በዚያ ሳለን በአንድ ሌሊት ሁለታችንም የተለያየ ሕልም ዐየን፤ የእያንዳንዳችንም ሕልም የተለያየ ትርጉም ነበረው።
12በዚያን ጊዜ የዘበኞች አለቃ አገልጋይ የሆን አንድ ዕብራዊ ወጣት ከእኛ ጋር እስር ቤት ነበር። ሕልማችንን በነገርነው ጊዜ፣ ፍቺውን ነገረን፤ ለእያንዳንዳችንም እንደ ሕልማችን ተረጎመልን፤
13ነገሩም ልክ እርሱ እንደተረጎመልን፤ እኔ ወደ ቀድሞ ሹመቴ ተመለስሁ፤ የእንጀራ ቤት አዛዡም ተሰቀለ።
14ፈርዖን ዮሴፍን እንዲያመጡት ትዕዛዝ ሰጠ፤ ከእስር ቤትም በጥድፊያ ይዘውት መጡ፤ ጠጉሩንም ከተላጨና ልብሱን ከለወጠ በኋላ ፈርዖን ፊት ቀረበ
15ፈርዖንም ዮሴፍን፣ “ሕልም ዐይቼ ነበር፣ ሕልሜን ሊተረጉምልኝ የቻለ አንድም ሰው አልተገኘም፣ አንተ ግን ሕልም ሲነገርህ የመተርጎም ችሎታ እንዳለህ ሰማሁ” አለው።
16ዮሴፍም ለፈርዖን እንዲህ ብሎ መለሰ፦ “ይህ በእኔ አይደለም፤ እግዚአብሔር ግን ለፈርዖን በበጎነት ይመልስለታል”
17ፈርዖን ዮሴፍን እንዲህ አለው፤ “ሕልሜ በዓባይ ወንዝ ዳር ቆሜ ነበር።
18ሥጋቸው የወፈረና መልካቸው የማረ ሰባት ላሞች ከወንዙ ወጥተው በወንዙ ዳር የበቀለውን ሣር ሲበሉ ዐየሁ።
19ከእነርሱም በኋላ ዐቅመ ደካማ፣ መልካቸው እጅግ የከፋና አጥንታቸው የወጣ ሌሎች ሰባት ላሞች ወጡ፤ እነዚያን የመሰሉ የሚያስከፋ መልክ ያላቸው ላሞች በግብፅ ምድር ከቶ ዐይቼ አላውቅም።
20አጥንታቸው የወጣና አስከፊ መልክ ያላቸው ላሞች መጀመሪያ የወጡትን፣ ሥጋቸው የወፈረውን ሰባቱን ላሞች ዋጧቸው።
21ከዋጧቸውም በኋላ፣ ያው የበፊቱ መልካቸው ስላልተለወጠ እንደዋጧቸው ማንም ሊያውቅ አይችልም ነበር፤ ከዚያም ከእንቅልፌ ነቃሁ
22ደግሞም በአንድ የእህል አገዳ ላይ ሰባት የዳበሩና ያማሩ የእሸት ዛላዎች ዐየሁ፤
23ቀጥሎም የቀጨጩና የደረቁ ሌሎች ሰባት ዛላዎች ወጡ።
24የቀጨጩት የእሸት ዛላዎችም ሰባቱን ያማሩ የእሸት ዛላዎች ዋጧቸው፤ ያየኋቸውንም ሕልሞች ለአስማተኞች ነገርሁ፣ ነገር ግን ሕልሞቹን ማንም ሊተረጉምልኝ አልቻለም።”
25ዮሴፍም ለፈርዖን እንዲህ አለው፤ “ሁለቱም የፈርዖን ሕልሞች ተመሳሳይና አንድ ዓይነት ናቸው፤ እግዚአብሔር ወደፊት የሚያደርገውን ለፈርዖን ገልጦለታል።
26ሰባቱ የሚያምሩ ላሞች ሰባት ዓመታት ናቸው፣ ሰባቱም የሚያማምሩ የእሸት ዛላዎች ሰባት ዓመታት ናቸው፤ ሕልሙም አንድና ተመሳሳይ ነው።
27ከእነርሱም በኋላ አጥንታቸው የወጣ አስከፊ መልክ ያላቸው ሰባት ላሞች፣ ሰባት ዓመታት ናቸው፤ እንደዚሁም ፍሬ አልባ የሆኑትና በምሥራቅ ነፋስ ተመትተው የደረቁት ሰባት የእሸት ዛላዎች ሰባት የራብ ዓመታት ናቸው።
28አስቀድሜ ለፈርዖን እንደተናገርሁት እግዚአብሔር ወደፊት የሚያደርገውን ነገር ለፈርዖን ገልጦለታል።
29በመላው የግብፅ ምድር እጅግ የተትረፈረፈ ጥጋብ የሚሆንባቸው ሰባት ዓመታት ይመጣሉ።
30በዚህ በኋላ ግን በተከታታይ ሰባት የራብ ዓመታት ይሆናሉ። የራቡ ዘመን አገሪቱን እጅግ ስለሚጎዳት በግብፅ የነበረው ያለፈው የጥጋብ ዘመን ሁሉ ጨርሶ አይታወስም።
31ከጥጋብ ዓመታት በኋላ የሚመጣው የራብ ዘመን እጅግ ጽኑ ከመሆኑ የተነሣ፣ ቀደም ሲል የነበረው የጥጋብ ዘመን ፈጽሞ ይረሳል።
32ሕልሙ ለፈርዖን በድጋሚ መታየቱ፣ ነገሩ ከእግዚአብሔር ዘንድ የተቆረጠ ስለሆነ ነው፤ ይህንንም እግዚአብሔር በቅርብ ጊዜ ይፈጽመዋል፤
33እንግዲህ ፈርዖን ብልኅና አስተዋይ ሰው ፈልጎ፣ በመላው የግብፅ ምድር ላይ አሁኑኑ ይሹም።
34እንደዚሁም በሰባቱ የጥጋብ ዓመታት ከሚገኘው ምርት፣ አንድ አምስተኛው እንዲሰበሰብ የሚያደርጉ ኃላፊዎችን ይሹም።
35እነርሱም በሚመጡት የጥጋብ ዓመታት ከሚገኘው ምርት ሁሉ ይሰብስቡ፤ በፈርዖንም ሥልጣን ሥር ያከማቹ፤ ለምግብ እንዲሆኑም በየከተማው ይጠበቁ።
36የሚከማቸው እህል፣ ወደፊት በግብፅ አገር ላይ ለሚመጣው የሰባት ዓመት ራብ መጠባበቂያ ይሁን፤ በዚህም ሁኔታ አገሪቱ በራብ አትጠፋም።
37ዕቅዱም ፈርዖንና ሹማምንቱ ሁሉ መልካም ሆኖ አገኙት።
38ፈርዖንም፣ “የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት እንደዚህ ያለ ሰው ልናገኝ እንችላለን?” ብሎ ጠየቃቸው።
39ፈርዖን ዮሴፍን እንዲህ አለው፣ “እግዚአብሔር ይህን ሁል ገለጠለህ እንዳንተ ያለ አስተዋይና ብልህ ሰው የለም።
40አንተ በቤተ መንግሥቴ የበላይ ትሆናለህ፤ ሕዝቤም ሁሉ ለሥልጣንህ ይገዛል፤ እኔ ከአንተ የምበልጠው በዙፋኔ ብቻ ይሆናል።”
41ከዚያም፣ ፈርዖን ዮሴፍን፣ “በመላይቱ የግብፅ ምድር ላይ ኃላፊ አድርጌሃለሁ” አለው።
42ፈርዖንም ባለማኅተሙን ቀለበት ከጣቱ አውልቆ በዮሴፍ ጣት ላይ አደረገው፤ እንዲሁም ከጥሩ የተልባ እግር የተሠራ ልብስ አለበሰው፤ በአንገቱም የወርቅ ሐብል አጠለቀለት።
43በማዕረግ ከእርሱ ሁለተኛ ሰው አድርጎ በሠረገላ ላይ አስቀመጠው። ሰዎችም በፊቱ፣ “እጅ ንሡ” እያሉ ይጮኹ ነበር፤ በዚህ ሁኔታም በግብፅ ምድር ሁሉ ላይ ሾመው።
44ከዝህ በኋላ ፈርዖን ዮሴፍን፣ “እኔ ፈርዖን ነኝ፤ ሆኖም በመላይቱ ግብፅ ያለ አንተ ፈቃድ ማንም ሰው እጁን ወይም እግሩን ማንቀሳቀስ አይችልም” አለው።
45ፈርዖን ዮሴፍን ጸፍናት ፐዕናህ ብሎ ስም አወጣለት። እንዲሁም አስናት ተብላ የምትጠራውን ኦን ተብሎ የሚጠራው ከተማ ካህን የጶጢፌራን ልጅ በሚስትነት ሰጠው።
46ዮሴፍ የግብፅ ንጉሥ ፈርዖንን ማገልገል ሲጀምር፣ ዕድሜው ሠላሳ ዓመት ነበር። ዮሴፍም ከፈርዖን ፊት ወጥቶ የግብፅን ምድር በሙሉ ዞረ።
47በሰባቱም የጥጋብ ዓመታት ምድሪቱ የተትረፈረፈ ሰብል ሰጠች።
48በእነዚያ ሰባት የጥጋብ ዓመታት፣ ዮሴፍ በግብፅ አገር የተገኘውን ምርት ሰብስቦ በየከተሞቹ አከማቸ፣ በእያንዳንዱ ከተማ ከየአቅራቢያው የተመረተውን እህል እንዲከማች አደረገ።
49ዮሴፍ ብዛቱ እንደ ባሕር አሸዋ የሚሆን የእህል ሰብል አከማቸ፤ ሰብሉ እጅግ ከመብዛቱ የተነሣ ልኩን መስፈርና መመዝገብ አልቻለም ነበር።
50ሰባቱ የራብ ዓመታት ከመምጣታቸው በፊት የኦን ከተማ ካህን የጶጢፌራ ልጅ አስናት ለዮሴፍ ሁለት ወንድ ልጆች ወለደችለት።
51ዮሴፍም፣ “እግዚአብሔር መከራዬን ሁሉ የአባቴንም ቤት እንድረሳ አድርጎኛል” በማለት የመጀመሪያ ልጁን ስም ምናሴ አለው።
52እንደዚሁም “መከራ በተቀበልሁበት ምድር እግዚአብሔር ፍሬያማ አደረገኝ” ሲል ሁለተኛ ልጁን ኤፍሬም አለው።
53በግብፅ ምድር የነበረው ሰባቱ የጥጋብ ዘመን አለፈና
54ዮሴፍ አስቀድሞ እንደተናገረው የሰባቱ ዓመት የራብ ዘመን ጀመረ። ሌሎች አገሮች ሁሉ ሲራቡ፣ በመላው የግብፅ ምድር መስፋፋት ሲጀመር፣
55ሕዝቡ ምግብ ይሰጠን በማለት ወደ ፈርዖን ጮኸ። ፍርዖንም ግብፃውያኑን፣ “ወደ ዮሴፍ ሂዱና የሚላችሁን አድርጉ” አላቸው።
56ራቡ በአገሩ ላይ እየተስፋፋ ስለሄደ፣ ዮሴፍ ጎተራዎቹን ከፍቶ እህሉ ለግብፃውያን እንዲሸጥ አደረገ፤ ምክንያቱም ራቡ በመላይቱ ግብፅ ጸንቶ ነበር።
57ራቡ በመላው ዓለም ጸንቶ ስለነበር፣ የየአገሩ ሰዎች ሁሉ ከዮሴፍ ዘንድ እህል ለመሸመት ወደ ግብፅ ምድር መጡ።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።