1ከዚህም በኋላ የግብፅ ንጉሥ የመጠጥ አሳላፊውና የእንጀራ ቤት ኃላፊው ንጉሡን የሚያሳዝን በደል ፈጸሙ።
2ፈርዖንም በመጠጥ አሳላፊዎቹ አለቃና በእንጀራ ቤቱ አዛዡ፣ በሁለቱም ሹማምንቱ ላይ እጅግ ተቆጣ፤
3በዘበኞቹ አለቃ ቤት ወዳለው ዮሴፍ ወደታሠረበት እስር ቤት አስገባቸው።
4የዘበኞቹም አለቃ እስረኞቹን ለዮሴፍ አስረከባቸው፤ በእስር ቤትም ለጥቂት ጊዜ ቆዩ።
5ታስረው የነበሩት የግብፅ ንጉሥ የመጠጥ አሳላፊዎች አለቃና የእንጀራ ቤቱ አዛዥ፣ በአንድ ሌሊት የየራሳቸውን ሕልም ዐዩ፤ የሁለቱም ሕልም ለየራሱ የተለየ ፍቺ ነበረው።
6በማግስቱ ጥዋት ዮሴፍ እነርሱ ወዳሉበት ክፍል በገባ ጊዜ ተክዘው አገኛቸውና፤
7“ዛሬ በፊታችሁ ላይ ሐዘን የሚታየው ለምንድን ነው?” አላቸው።
8እነርሱም፣ “ሁለታችንም ሕልም ዐየን፤ ነገር ግን የሚተረጉምልን ሰው አጣን” ሲሉ መለሱለት። ዮሴፍም፣ “ሕልም የመተርጎም ችሎታ የሚሰጥ እግዝአብሔር ነው፣ ስለዚህ የእያንዳንዳችሁን ሕልም ንገሩኝ” አላቸው።
9ስለዚህ የመጠጥ አሳላፊዎቹ አለቃ እንዲህ ሲል ሕልሙን ለዮሴፍ ነገረው፤ “ከፊት ለፊቴ አንዲት የወይን ተክል ዐየሁ፤
10ተክሏም ሦስት ሐረጎች ነበሯት፤ ወዲያው እቆጥቁጣ አበበች፤ የወይን ዘለላውም ወዲያው በሰለ።
11የፈርዖንንም ጽዋ ይዤ ነበር፣ የወይኑን ፍሬ ለቅሜ በጽዋው ውስጥ ጨምቄ ጽዋውን በእጁ ሰጠሁት።”
12ዮሴፍም እንዲህ አለው፤ “እንግዲህ የሕልሙ ትርጓሜ ይህ ነው፤ ሦስቱ ሐረግ ሦስት ቀን ነው፤
13በሦስት ቀን ውስጥ ፈርዖን ከእስር ቤት ያወጣሃል፣ ወደ ቀድሞ ሹመትህም ይመልስሃል፤ በፊት የመጠጥ አሳላፊ በነበርህበት ጊዜ ታደርግ እንደነበረው ኡሉ የፈርዖንን ጽዋ በእጁ ትሰጠዋለህ።
14እንግዲህ፣ በጎ ነገር በገጠመህ ጊዜ፣ እኔን አስበህ ቸርነት አድርግልኝ፣ ስለ እኔም ለፈርዖን ንገርልኝ፤ ከዚህም እስር ቤት አስወጣኝ፤
15ከዕብራውያን ምድር ወደዚህ የመጣሁት በአፈና ነው፤ አሁንም ቢሆን እዚህ እስር ቤት የተጣልሁት አንዳች ጥፋት ኖሮብኝ አይደለም።”
16የእንጀራ ቤት አዛዡም፣ ለመጠጥ አሳላፊዎቹ አለቃ ሕልም የተሰጠው ፍቺ ደስ የሚያሰኝ መሆኑን ሲሰማ፣ የራሱን ሕልም ለዮሴፍ እንዲህ ሲል ነገረው፤ “እኔም ደግሞ ሕልም አይቻለሁ፣ ሦስት መሶቦች በራሴ ላይ ተሸክሜ ነበር፤
17በላይኛው መሶብ ውስጥ ለፈርዖን የተዘጋጀ የተለያየ ምግብ ነበረበት፣ ነገር ግን ወፎች ምግቡን ከመሶቡ እያነሱ የበሉት ነበር።”
18ዮሴፍም እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “የሕልሙ ፍቺ ይህ ነው፤ ሦስቱ መሶብ ሦስት ቀን ነው፤
19በሦስት ቀን ውስጥ ፈርዖን ራስህን ካስቆረጠ በኋላ በእንጨት ላይ ይሰቅልሃል፤ ወፎችም ሥጋህን የበሉታል።”
20በሦስተኛው ቀን የፈርዖን ልደት በዓል ስለነበር ለመኳንንቱ ሁሉ ግብዣ አደረገ፤ በዚያኑ ዕለትም የመጠጥ አሳላፊዎቹን አለቃና የእንጀራ ቤት አዛዡን ሹማምንቱ ካሉበት ከእስር ቤት አወጣቸው።
21የመጠጥ አሳላፊዎቹን አለቃ ወደ ቀድሞ ሹመቱ መለሰው፤ እርሱም እንደ ቀድሞው ጽዋውን ለፈርዖን በእጁ ይሰጠው ጀመር፤
22የእንጀራ ቤት አዛዡን ግን ልክ ዮሴፍ እንደተረጎመላቸው ሰቀለው።
23የሆነው ሆኖ፣ የመጠጥ አሳላፊዎቹ አለቃ ዮሴፍን አላስታወሰውም፤ ረሳው።