መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ኦሪት ዘፍጥረት 4

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1አዳምም ከሚስቱ ከሔዋን ጋር የግብረ ሥጋ ግንኙነት ፈጸመ። እርሷም ፀነሰች። ቃየንንም ወለደች። “በእግዚአብሔር ዕርዳታ ወንድ ልጅ ወለድሁ” አለች።
2ከዚያ በኋላም ወንድሙን አቤልን ወለደች። አቤል የበግ እረኛ ሲሆን ቃየን ግን ገበሬ ሆነ።
3ከዕለታት አንድ ቀን ቃየን ከምድር ፍሬ ለእግዚአብሔር መባ አቀረበ።
4አቤል ደግሞ መጀመሪያ ከተወለዱ በጎች መካከል ስባቸውን መሥዋዕት አድርጎ አቀረበ። እግዚአብሔር በአቤልና በመሥዋዕቱ ደስ ተሰኘ፣
5በቃየንና በመሥዋዕቱ ግን ደስ አልተሰኘም። ስለዚህ ቃየን በጣም ተቆጣ፣ ፊቱም ተኮሳተረ።
6እግዚአብሔር አምላክ ቃየንን፦ “ለምን ተቆጣህ፣ ፊትህስ ለምን ተኮሳተረ?
7መልካም ብታደርግ ፊትህ ያበራ አልነበረምን? ያደረግኸው መልካም ካልሆን ግን ኃጢአት በደጅህ እያደባች ናት፣ ልትቆጣጠርህም ትፈልጋለች፣ አንተ ግን በቁጥጥርህ ሥር አድርጋት” አለው።
8ቃየን ወንድሙን አቤልን፦ “ወደ ሜዳ እንውጣ” አለው፣ በዚያም ቃየን በወንድሙ በአቤል ላይ በቁጣ ተነሳበት፣ ገደለውም።
9ከዚያ በኋላም እግዚአብሔር ቃየንን፦ “ወንድምህ አቤል ወዴት ነው?” አለው። እርሱም፦ “አላውቅም፣ እኔ የወንድሜ ጠባቂ ነኝን?” አለ።
10እግዚአብሔርም፦ “ያደረግኸው ምንድን ነው? የወንድምህ ደም ከምድር ወደ እኔ ይጮኻል” አለው።
11“አሁንም የወንድምህን ደም ከእጅህ ለመቀበል አፍዋን በከፈተች በምድር ላይ አንተ የተረገምህ ነህ።
12ምድርንም በምታርስበት ጊዜ ፍሬዋን በሙላት አትሰጥህም። በምድር ላይ ኮብላይና ተንከራታች ትሆናለህ” አለው።
13ቃየንም ለእግዚአብሔር፦ ቅጣቴ ከምችለው በላይ ነው።
14በእርግጥም ዛሬ ከምድሪቱ አባርረኸኛል፣ እኔም ከፊትህ እሸሸጋለሁ። በምድር ላይ ኮብላይና ተንከራታች እሆናለሁ፣ የሚያገኘኝም ሁሉ ይገድለኛል” አለው።
15እግዚአብሔርም፦ “ቃየንን የሚገድል ማንኛውም ሰው ሰባት እጥፍ የበቀል እርምጃ ይወሰድበታል” አለ። ከዚያ በኋላም የሚያገኘው ማንኛውም ሰው እንዳይገድለው እግዚአብሔር በቃየን ላይ ምልክት አደረገበት።
16ቃየንም ከእግዚአብሔር ፊት ወጥቶ ሄደ፣ ከኤደን በስተምሥራቅ በነበረው ኖድ በተባለው ምድር ኖረ።
17ቃየንም ከሚስቱ ጋር የግብረ ሥጋ ግንኙነት ፈጸመ፣ እርሷም ፀነሰች፣ ሄኖክንም ወለደች። ቃየን ከተማን መሠረተ፣ የመሠረታትንም ከተማ በልጁ ስም ሄኖክ ብሎ ጠራት።
18ሄኖክም አራድን ወለደ። አራድም መሑያኤልን ወለደ። መሑያኤልም መቱሳኤልን ወለደ። መቱሳኤልም ላሜክን ወለደ።
19ላሜክም ዓዳና ጺላ የተባሉ ሁለት ሚስቶችን አገባ።
20ዓዳ ያባልን ወለደች፣ እርሱም በድንኳን ለሚኖሩ ለከብት አርቢዎች አባት ነበር።
21የእርሱ ወንድም ዩባልም የበገና ደርዳሪዎችና የዋሽንት ነፊዎች አባት ነበር።
22ጺላም ከነሐስና ከብረት መሣሪያዎችን የሚሠራውን ቱባልቃይንን ወለደች። የቱባልቃይንም እህት ናዕማ ትባል ነበር።
23ላሜክ ለሚስቶቹ፦ “አዳና ጺላ ስሙኝ፣ እናንተ የላሜክ ሚስቶች የምላችሁን ስሙኝ ስለጎዳኝና ስላቆሰለኝ አንድ ሰው ገድያለሁ።
24ቃየንን የሚገድል ሰባት እጥፍ የበቀል እርምጃ የሚወሰድበት ከሆነ የላሜክ ገዳይማ ሰባ ሰባት እጥፍ የበቀል እርምጃ ይወሰድበታል” አላቸው።
25አዳም ከሚስቱ ጋር እንደገና የግብረ ሥጋ ግንኙነት ፈጸመ፣ እርሷም ወንድ ልጅ ወለደች። “ቃየን በገደለው በአቤል ፈንታ እግዚአብሔር ምትክ ሰጠኝ” በማለት ስሙን ሤት ብላ ጠራችው።
26ለሤትም ወንድ ልጅ ተወለደለት፣ ስሙንም ሄኖስ አለው። በዚያም ዘመን ሰዎች የእግዚአብሔርን ስም መጥራት ጀመሩ።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።