መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ኦሪት ዘፍጥረት 3

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1እግዚአብሔር በምድር ላይ ከፈጠራቸው ማናቸውም ሌሎች አራዊቶች ሁሉ ይልቅ እባብ ተንኮለኛ ነበር። እርሱም ሴቲቱን፦ “በእርግጥ እግዚአብሔር ‘በአትክልቱ ስፍራ ካለው ከማንኛውም ዛፍ አትብሉ’ ብሎአልን?” ብሎ ጠየቃት።
2ሴቲቱም ለእባቡ፦ “በአትክልቱ ስፍራ ካሉት የዛፎች ፍሬዎች መብላት እንችላለን፤
3ነገር ግን በአትክልቱ ስፍራ መካከል ስለሚገኘው ዛፍ እግዚአብሔር “እንዳትሞቱ ከእርሱ አትብሉ አትንኩትም” ብሎአል።
4እባብም ለሴቲቱ፦ “በፍጹም አትሞቱም።
5ከእርሱ በበላችሁ ቀን ዓይኖቻችሁ እንደሚከፈቱ እንደ እግዚአብሔርም መልካሙንና ክፉውን የምታውቁ እንደምትሆኑ እግዚአብሔር ስለሚያውቅ ነው አላት።”
6ሴቲቱም ዛፉ ለመብላት መልካም፣ ሲያዩት ደስ የሚያሰኝና ጥበብንም ለማግኘት የሚያጓጓ እንደሆነ ተመልክታ ከፍሬው ወስዳ በላች፤ ከእርሷ ጋር ለነበረውም ለባሏ ከፍሬው ሰጠችው፣ እርሱም በላ።
7የሁለቱም ዓይኖች ተከፈቱ፣ ራቁታቸውን እንደነበሩም አወቁ። የበለስ ቅጠሎችንም በማጋጠም ከሰፉ በኋላ ለራሳቸው መሸፈኛ ግልድም ሠሩ።
8ቀኑ ወደ ምሽት ሲቃረብ በአትክልት ስፍራው ሲመላለስ የእግዚአብሔር አምላክን ድምፅ ሰሙ፤ ስለዚህ አዳምና ሚስቱ ከእግዚአብሔር አምላክ ፊት በመሸሽ በአትክልቱ ስፍራ በነበሩት ዛፎች መካከል ተሸሸጉ።
9እግዚአብሔር አምላክ አዳምን ጠራውና፣ “የት ነህ?” አለው።
10አዳምም፣ “በአትክልቱ ስፍራ ውስጥ ድምፅህን ሰማሁና ራቁቴን ስለነበርሁ ፈራሁ፤ በዚህም ምክንያት ተሸሸግሁ።”
11እግዚአብሔርም፦ “ራቁትህን እንደሆንክ ማን ነገረህ? ከእርሱ እንዳትበላ ብዬ ካዘዝኩህ ከዛፉ ፍሬ በላህን?” አለው።
12አዳምም፦ “አብራኝ እንድትሆን የሰጠኸኝ ሴት ከዛፉ ፍሬ ሰጠችኝ፣ እኔም በላሁት” አለ።
13እግዚአብሔር አምላክም ሴቲቱን፦ “ምንድነው ያደረግሽው?” አላት። ሴቲቱም፦ “እባቡ አታለለኝና በላሁ” አለች።
14እግዚአብሔር አምላክም ለእባቡ፦ “ይህንን በማድረግህ ከእንስሳት ሁሉና ከምድር አራዊት ሁሉ ተለይተህ የተረገምህ ትሆናለህ። በደረትህ እየተሳብክ ትሄዳለህ፣ በሕይወት ዘመንህም ሁሉ አፈር ትበላለህ።
15በአንተና በሴቲቱ፣ በዘርህና በዘሯ መካካል ጠላትነትን አደርጋለሁ። የእርሷ ዘር ራስህን ይቀጠቅጣል፣ አንተም ተረከዙን ትነክሳለህ” አለው።
16ለሴቲቱም እንዲህ አላት፦ “በምጥ ጊዜ ጭንቅሽን አበዛለሁ፤ በስቃይም ትወልጃለሽ። ፈቃድሽ ወደ ባልሽ ይሆናል፣ እርሱም ገዢሽ ይሆናል።”
17ለአዳምም እንደዚህ አለው፦ “የሚስትህን ቃል ሰምተህ ‘ከእርሱ እንዳትበላ’ ብዬ ካዘዝሁህ ከዛፉ ፍሬ ስለበላህ ከአንተ የተነሳ ምድር የተረገመች ትሁን፤ በሕይወትህ ዘመን ሁሉ በከባድ ድካም ምግብህን ከእርሷ ታገኛለህ።
18ምድር እሾህና አሜኬላ ታበቅልብሃለች፤ የምድርንም ቡቃያ ትበላለህ።
19ከተገኘህበት አፈር እስክትመለስ ድረስ በላብህ እንጀራን ትበላለህ። አፈር ነህና ወደ አፈር ተመልሰህ ትሄዳለህ”።
20የሕያዋን ሁሉ እናት በመሆኗ አዳም ለሚስቱ ‘ሔዋን’ የሚል ስም አወጣላት።
21እግዚአብሔር አምላክ ከቆዳ ልብስ አዘጋጅቶ አዳምንና ሚስቱን አለበሳቸው።
22እግዚአብሔር አምላክ፦ “መልካምንና ክፉውን ለይቶ በማውቅ ረገድ አሁን ሰው ከእኛ እንደ አንዱ ሆኖአል። ስለዚህ አሁን እጁን ዘርግቶ ከሕይወት ዛፍ ፍሬ ቀጥፎ እንዳይበላ ለዘላለምም እንዳይኖር ሊፈቀድለት አይገባም” አለ።
23በዚህም ምክንያት የተገኘባትን ምድር እንዲያለማ እግዚአብሔር አዳምን ከኤደን የአትክልት ስፍራ አስወጣው።
24ስለዚህ እግዚአብሔር አዳምን ከአትክልት ስፍራው አባረረው፣ ወደ ሕይወት ዛፍ የሚወስደውንም መንገድ ይጠብቁ ዘንድ ከኤደን የአትክልት ስፍራ በስተቀኝ በኩል ኪሩቤልን እንደዚሁም በየአቅጣጫው የምትገለባበጥ ነበልባላዊ ሰይፍ አኖረ።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።