1በዚያም ወራት ይሁዳ ከወንድሞቹ ተለይቶ ሒራ ወደተባለ ዐዱላማዊ ሰው ዘንድ ሄደ፣ መኖሪያውንም
2እዚያም ሳለ፣ ይሁዳ የከነዓናዊውን የሴዋን ሴት ልጅ ዐየ፤ እርሷንም አግብቶ የግብረ ሥጋ ግንኙነት ፈጸመ።
3እርሷም አርግዛ ወንድ ልጅ ወለደችለት፤ ስሙንም ዔር ብላ ጠራችው።
4እንደገናም አረገዘችና ወንድ ልጅ ወለደችለት፤ ስሙንም አውናን አለችው።
5አሁንም ደግማ ወንድ ልጅ ወለደች፤ ስሙንም ሴሎም ብላ ጠራችው፣ እርሱንም የወለደችው ክዚብ በተባለ ቦታ ነበር።
6ይሁዳ የመጀመሪያ ልጁን ዔርን ትዕማር ከምትባል ልጃገረድ ጋር አጋባው።
7የይሁዳ የበኩር ልጅ ዔር ግን በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነበር፤ እግዚአብሔርም ቀሠፈው።
8ይሁዳ አውናንን፣ “ዋርሳዋ እንደመሆንህ ከወንድምህ ሚስት ጋር የግብረ ሥጋ ግንኙነት በመፈጸም የወንድምህን ስም የሚያስጠራለት ዘር ተካለት አለው።
9አውናን ግን የሚወለደው ልጅ የእርሱን ስም የሚያስጠራ እንደማይሆን ስላወቀ፣ ከወንድሙ ሚስት ጋር የግብረ ሥጋ ግንኙነት በፈጸመ ቁጥር የወንድሙን ስም የሚያስጠራ ልጅ እንዳይወለድ ዘሩን በምድር ላይ ያፈስ ነበር።
10ይህም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ሆኖ ስለተገኘ፣ እርሱንም እግዚአብሔር በሞት ቀሠፈው።
11ከዚያም ይሁዳ ምራቱን ትዕማርን፣ “ልጄ ሴሎም ለአካለ መጠን እስኪደርስ ድረስ ወደ አባትሽ ቤት ሄደሽ መበለት ሆነሽ ብትኖሪ ይሻላል” አላት፤ ይህን ያለውም፤ ሴሎም እንደወንድሞቹ ተቀሥፎ ይሞትብኛል ብሎ ስለፈራ ነበር። ትዕማርም እንዳላት ሄደች፤ በአባቷም ቤት ተቀመጠች።
12ከብዙ ጊዜ በኋላ የሹዓ ልጅ፣ የይሁዳ ሚስት ሞተች። ይሁዳ ከሐዘኑ ከተጽናና በኋላ ከዓዶላማዊው ከሒራ ጋር የበጎቹን ጠጉር የሚሸልቱ ሰዎች ወዳሉበት ወደተምና ሄደ።
13ሰዎቹም ለትዕማር፣ “አማትሽ የበጎቹን ጠጉር ወደሚሸልቱ ሰዎች ዘንድ ወደተምና እየሄዱ ነው” አሏት። ይህን እንድሰማች
14የመበለትነት ልብሷን አውልቃ፣ ማንነቷ እንዳይታወቅ ፊቷን በሻሽ ተከናንባ ወደ ተምና በሚወስደው መንገድ ዳር ባለች ኤናይም በተባለች ከተማ መግቢያ በር ላይ ተቀመጠች፤ ይህን ያደረገችው፣ ሴሎም ለአካለ መጠን ቢደርስም፣ እርሷን እንዲያገባ አባቱ አለመፈለጉን ስላወቀች ነው።
15ፊቷ በሻሽ ተሸፋፍኖ ሲያያት፣ ይሁዳ ዝሙት አዳሪ መሰለችው።
16ምራቱ መሆኗን ባለማወቁ፣ እርሷ ወዳለችበት ወደ መንደሩ ዳር ጠጋ ብሎ፣ “እባክሽን አብሬሽ ልተኛ” አላት። እርሷም፣ “አብሬህ ብተኛ ምን ትሰጠኛለህ?” ብላ ጠየቀችው።
17“ከመንጋዬ መካከል አንድ የፍየል ጠቦት እልክልሻለሁ” አላት። እርሷም “ጠቦቱን እስክትልክልኝ ድረስ ምን መያዣ ትሰጠኛለህ?” ብላ ጠየቀችው።
18“ታዲያ ምን መያዣ ልስጥሽ?” አላት። እርሷም፣ “የማኅተም ቀለበትህን ከነማሰሪያው፣ እንደዚሁም ይህን በትርህን ስጠኝ” አለችው። የጠየቀችውን ሁሉ ሰጣትና አብሯት ተኛ፤ እርሷም አረገዘችለት።
19ከዚያም ወደ መኖሪያዋ ተመልሳ፣ ሻሽዋን አውልቃ እንደወትሮዋ የመበለት ለብሷን ለበሰች።
20ይሁዳ በመያዣ ስም የሰጣትን ዕቃዎች ለማስመለስ የፍየሉን ጠቦት በዓዶሎማዊ ወዳጁ እጅ ላከላት፣ እርሱ ግን ሊያገኛት አልቻለም።
21“በኤናይም ከተማ መግቢያ ከመንገዱ ዳር የነበረች ያቺ ዝሙት አዳሪ የት ደረሰች?” ብሎ ዓዶሎማዊው ሰውዬ ጠየቀ። ሰዎቹም፣ “በዚህ አካባቢ እንደዚህ ያለች ዝሙት አዳሪ የለችም” አሉት።
22ስለዚህ ወደ ይሁዳ ተመልሶ ሄደና፣ “ላገኛት አልቻልሁም፤ በዚያ የሚኖሩትም ሰዎች፥ ‘እንደዚህ ያለች ዝሙት አዳሪ እዚህ የለችም’ አሉኝ” ብሎ ነገረው።
23ይሁዳም፣ “እንግዲህ መያዣውን እንደያዘች ትቅር አለዚያ መሳቂያ እንሆናለን። ለነገሩማ ይህን ፍየል ላክሁ፣ አንተም ፈልገህ አላገኘሃትም” አለ።
24ከሦስት ወር ያህል በኋላ፣ “ምራትህ ትዕማር ዘማዊ ሆናለች፤ ከዚህም የተነሣ አርግዛለች” ተብሎ ለይሁዳ ተነገረው። ይሁዳም፣ “አውጧትና በእሳት ተቃጥላ ትሙት” አለ።
25እርሷም ተይዛ በምትወሰድበት ጊዜ ለአማትዋ፣ “እኔ ያረገዝሁት የእነዚህ ዕቃዎች ባለቤት ከሆነ ሰው ነው” ስትል ላከችበት፤ ደግሞም፣ “የማኅተሙ ቀለበት ከነማንጠልጠያውና በትሩ የማን እንደሆነ እስቲ ተመልከት” አለችው።
26ይሁዳም ዕቃዎቹን አውቆ፣ “ልጄ ሴሎም እንዲያገባት ባለማድረጌ፣ እርሷ ከእኔ ይልቅ ትክክል ናት” አለ። ከዚያም በኋላ ከእርሷ ጋር አልተኛም።
27የመውለጃዋ ጊዜ እንደደረሰም ፅንሷ መንታ መሆኑ ታወቀ።
28በምትወልድበትም ጊዜ አንደኛው እጁን አወጣ፤ አዋላጂቱም፣ “ይህኛው መጀመሪያ ወጣ” ስትል በእጁ ላይ ቀይ ክር አሰረችለት፤
29ነገር ግን፣ እጁን መልሶ ሲያስገባ ወንድሙ ተወለደ። አዋላጂቱም፣ “አንተ እንዴት ጥሰህ ወጣህ!” አለች፣ ከዚያም ስሙ ፋሬስ ተባለ።
30ከዚያ በኋላ እጁ ላይ ቀይ ክር የታሰረለት ወንድሙ ተወለደ፣ ስሙም ዛራ ተባለ።