1የዕቆብ አባቱ በኖረበት በከነዓን ምድር ተቀመጠ።
2የያዕቆብ ትውልድ ታሪክ ይህ ነው። ዮሴፍ የዐሥራ ሰባት ዓመት ወጣት በነበረ ጊዜ፣ ከአባቱ ሚስቶች ከባላቅና ከዘለፋ ከተወለዱት ወንድሞቹ ጋር የአባቱን በጎችና ፍየሎች ይጠብቅ ነበር። እርሱም ስለወንድሞቹ ድርጊት ለአባቱ መጥፎ ወሬ ይዞለት መጣ።
3እስራኤል ዮሴፍን በስተርጅናው ስለወለደው፣ ከልጆቹ ሁሉ አብልጦ ይወደው ነበር፣ በኅብረ ቀለማት ያጌጠ እጀ ጠባብም ሰፋለት።
4ወንድሞቹም አባታቸው ከእነርሱ አብልጦ የሚወደው መሆኑን ሲያዩ ዮሴፍን ጠሉት፤ በቅን አንደበት ሊያናግሩት አልቻሉም።
5ዮሴፍ ሕልም አለመ፤ ሕልሙንም ለወንድሞቹ ሲነግራቸው የባሰ ጠሉት፤
6እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “ያየሁትን ሕልም ልንገራችሁ አድምጡኝ”
7‘እኛ ሁላችን በእርሻ ውስጥ ነዶ እናስር ነበር፤ የእኔ ነዶ ተነሣና ቀጥ ብሎ ቆመ፤ የእናንተ ነዶዎች ዙሪያውን ተሰብስበው ለእኔ ነዶ ሰገዱለት’”
8ወንድሞቹም፣ “ታዲያ በእኛ ላይ ንጉሥ ሆነህ ልትገዛን ታስባለህን?” ብለው ጠየቁት። ስለ ሕልሙና ስለተናገረው ቃል ከፊት ይልቅ ጠሉት።
9እንደ ገናም ሌላ ሕልም አለመ፤ ለወንድሞቹም እነሆ፣ ሌላ ሕልም አለምሁ፣ ፀሐይና ጨረቃ፣ ዐሥራ አንድ ክዋክብትም ሲሰግዱልኝ ዐየሁ” ብሎ ነገራቸው።
10ይህንኑ ለወንድሞቹ የነገራቸውን ሕልም ለአባቱም በነገረው ጊዜ፣ አባቱ፣ “ይህ ምን ዐይነት ሕልም ነው? እኔና እናትህ ወንድሞችህም በፊትህ ወደ ምድር ተጎንብሰን በርግጥ ልንሰግድልህ ነው?” ሲል ገሠጸው።
11ወንድሞቹ ቀኑበት፤ አባቱ ግን ነገሩን በልቡ ያዘው።
12አንድ ቀን የዮሴፍ ወንድሞች የአባታቸውን መንጋዎች ይዘው ወደ ሴኬም ተሰማሩ፤
13እስራኤልም ዮሴፍን፣ “እንደምታውቀው ወንድሞችህ መንጎቹን በሴኬም አካባቢ አሰማርተዋል፤ በል ተነሥ፣ ወደ እነርሱ ልላክህ” አለው። ዮሴፍም፣ “እሺ እሄዳለሁ” አለ።
14አባቱም፣ “በል እንግዲህ ሄድና የወንድሞችህንና የመንጋዎቹን ደኅንነት አይተህ ንገረኝ” አለው። በዚህ ዓይነት እስራኤል ዮሴፍን ከኬብሮን ሸለቆ ላከው። ዮሴፍም ሴኬም በደረሰ ጊዜ፣
15ሜዳ ላይ ወዲያ ወዲህ ሲባዝን አንድ ሰው አግኝቶት፣ “ምን እየፈለግህ ነው?” ሲል ጠየቀው።
16ዮሴፍም፣ “ወንድሞቼን እየፈለግኋቸው ነው፤ መንጎቻቸውን የት እንዳሰማሩ ልትነግረኝ ትችላለህ?” አለው።
17ሰውዬውም፣ “ከዚህ ሄደዋል፤ ደግሞም ‘ወደ ዶታይን እንሂድ’ ሲሉ ሰምቻቸዋለሁ” አለው። ከዚያም ዮሴፍ ወንድሞቹን ፍለጋ ሄደ፣ በዶታይን አቅራቢያም አገኛቸው።
18ወንድሞቹም ዮሴፍ ወደ እነርሱ ሲመጣ በሩቅ ዐዩት፣ ወደ ነበሩበትም ስፍራ ከመድረሱ በፊት ሊገድሉት ተማከሩ።
19እነርሱ እንዲህ ተባባሉ፦ “ያ ሕልም አላሚ መጣ፤
20ኑ እንግደለውና ከጉድጓዶቹ በአንዱ ውስጥ እንጣለው፤ ከዚያም፣ ‘ክፉ አውሬ ነጥቆ በላው’ እንላለን፤ እስቲ ሕልሞቹ ሲፈጸሙ እናያለን።”
21ሮቤል ግን ይህን ምክር ሲሰማ ከእጃቸው ሊያድነው ፈለገ እንዲህም አለ፤ “አንግደለው፤
22የሰው ደም አታፍስሱ፣ ከምትገድሉት ይልቅ በዚህ በበረሃ ባለው ጉድጓድ ውስጥ ጣሉት” አላቸው። ሮቤል ይህን ያለው ሕይወቱን ከእጃቸው አትርፎ ወደ አባቱ ሊመልሰው ዐስቦ ነበር።
23ዮሴፍ ወደ ወንድሞቹ እንደደረሰ፣ የለበሳትን በኅብረ ቀለማት የጌጠች እጀ ጠባቡን ገፈፉት፤
24ይዘውም ወደ ጉድጓድ ጣሉት፤ ጉድጓዱም ውሃ የሌለበት ደረቅ ነበር።
25ምግባቸውን ለመብላት ተቀመጡ፤ አሻግረው ሲመለከቱም ከገለዓድ የሚመጡ እስማኤላውያን ነጋዴዎች ጓዛቸውን በግመሎች ላይ ጭነው ተመለከቱ። ነጋዴዎቹ ሽቶ፣ በለሳን፣ ከርቤ በግመሎቻቸው ጭነው ወደ ግብፅ የሚወርዱ ነበሩ።
26ይሁዳም ወንድሞቹን እንዲህ አላቸው፤ “ወንድማችንን መግደልና አሟሟቱን መደበቅ ምን ይጠቅመናል?
27ከዚህ ይልቅ ለእስማኤላውያን ነጋዴዎች እንሽጠው፤ እጃችንን ግን በእርሱ ላይ አናንሳ። ምንም ቢሆን የሥጋ ወንድማችን ነው” ወንድሞቹም በሃሳቡ ተስማሙ።
28የምድያም ነጋዴዎች የሆኑ እስማሴላውያን በዚያ በኩል ያልፉ ነበር፤ ስለዚህ ወንድሞቹ ዮሴፍን ከጉድጓድ ጎትተው በማውጣት ለእነዚህ እስማኤላውያን በሃያ ብር ሸጡላቸው፣ እነርሱም ወደ ግብፅ ይዘውት ሄዱ።
29ሮቤል ወደ ጉድጓዱ ተመልሶ ሲያይ፣ ዮሴፍን በማጣቱ ልብሱን በሐዘን ቀደደ።
30ወደ ወንድሞቹም ተመልሶ፣ “እነሆ፣ ልጁ እዚያ የለም! እንግዲህ እኔ ወዴት ብሄድ ይሻለኛል?” አለ።
31ከዚህ በኋላ አንድ ፍየል አረዱና የዮሴፍን ልብስ በደም ነከሩት።
32በኅብረ ቀለማት ያጌጠችውን እጀ ጠባብ ወደ አባታቸው ወስደው፣ “ይህን ወድቆ አገኘነው፤ የልጅህ እጀ ጠባብ መሆን አለመሆኑን እስቲ እየው” አሉት።
33እርሱ የልጁ ልብስ መሆኑን ተረድቶ፣ “ይህማ የልጄ እጀ ጠባብ ነው! ፤ ክፉ አውሬ በልቶታል፣ በእርግጥም ዮሴፍ ተቦጫጭቆአል” አለ።
34ከዚህ በኋላ ያዕቆብ ልብሱን ቀደደ፤ ማቅም ለብሶ ስለ ልጁ ብዙ ቀን አለቀሰ፤
35ወንዶችና ሴቶች ልጆቹም ሁሉ ሊያጽናኑት መጡ፤ እርሱ ግን ሊጽናና አልቻለም፣ “በሐዘን እንደተኮራመትሁ ልጄ ወዳለበት መቃብር እወርዳለሁ” አለ። ስለ ልጁም አለቀሰ።
36በዚህ ጊዜ የምድያም ነጋዴዎች ዮሴፍን ወደ ግብፅ ወስደው፣ ከፈርዖን ሹማምንት አንዱ ለነበረው ለዘበኞች አለቃ፣ ለጲጥፋራ ሸጡት።