መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ኦሪት ዘፍጥረት 35

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1እግዚአብሔር ያዕቆብን፣ “ተነሣና ወደ ቤቴል ሂድ፣ እዚያም ኑር። ከወንድምህ ከዔሳው ሸሽተህ በሄድህ ጊዜ ለተገለጠልህ አምላክ በዚያ መሠዊያ ሥራ አለው።
2ስለዚህም ያዕቆብ ለቤቱ ሰዎችና አብረውት ለነበሩት ሁሉ እንዲህ አላቸው፤ “በእናንተ ዘንድ ያሉትን ባዕዳን አማልክት አስወግዱ፤ ሰውነታችሁን አንጹ፤ ልብሳችሁንም ለውጡ።
3ተነሥተን ወደ ቤቴል እንሂድ፤ እዚያም በመከራዬ ጊዜ ለሰማኝ በሄድሁበትም ስፍራ ሁሉ ላልተለየኝ አምላክ መሠዊያ እሠራለሁ።
4ስለዚህ በእነርሱ ዘንድ የነበሩትን ባዕዳን አማልክት ሰብስበው፣ የጆሮ ጉትቾቻቸውን አውልቀው ለያዕቆብ ሰጡት። ያዕቆብም ወስዶ ሴኬም አጠገብ ካለው ዋርካ ዛፍ ሥር ቀበራቸው።
5ያንንም ቦታ ለቀው ሄዱ፤ እግዚአብሔርም በዙሪያቸው በነበሩት ከተሞች ሁሉ ላይ ፍርሃትና ድንጋጤ ስለለቀቀባቸው ያሳደዳቸው አልነበረም።
6ያዕቆብና አብረውት የነበሩት ሰዎች ሁሉ በከነዓን ወደምትገኘው፣ ቤቴል ወደተባለችው ወደ ሎዛ ደረሱ።
7ያዕቆብም በዚያ ስፍራ መሠዊያ ሠርቶ፣ ስሙን ኤል ቤቴል አለው፤ ምክንያቱም ከወንድሙ ሸሽቶ በሄደ ጊዜ እግዚአብሔር የተገለጠለት በዚህ ቦታ ነበር።
8በዚህ ጊዜ የርብቃ ሞግዚት ዲቦራ ሞተች፣ ከቤቴል ዝቅ ብሎ በሚገኘው የዋርካ ዛፍ ሥር ተቀበረች። ከዚህ የተነሣም ያ ቦታ አሉንባኩት ተባለ።
9ያዕቆብ ከመስጴጦምያ በተመለሰ ጊዜ እግዚአብሔር ዳግመኛ ተገለጠለትና ባረከው።
10እግዚአብሔርም፣ “እስካሁን ስምህ ያዕቆብ ነበር፤ ከእንግዲህ ያዕቆብ ተብለህ አትጠራም፤ ነገር ግን ስምህ እስራኤል ይባላል” አለው። ስለዚህም እስራኤል ብሎ ጠራው።
11ደግሞም እግዚአብሔር ያዕቆብን እንዲህ አለው፤ “እኔ ሁሉም ማድረግ የሚችል አምላክ ነኝ፤ ብዙ ልጆች ይኑሩህ፤ ዘርህም ይብዛ፤ የብዙ ሕዝብ አባት ሁን፤ ነገሥታትም ከአንተ ይወለዱ።
12ለአብርሃምና ለይስሐቅ የሰጠኋትን ምድር ለአንተ እሰጣለሁ፤ ከአንተም በኋላ ይህችን ምድር ለዘርህ አሰጣለሁ።”
13እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ከተነጋገረ በኋላ ከዚያ ስፍራ ወደ ላይ ወጣ።
14ያዕቆብ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር በተነጋገረበት ስፍራ የድንጋይ ሐውልት አቆመ፣ በሐውልቱ ላይ የመጠጥ ቁርባን አፈሰሰ፤ ዘይትም አፈሰሰበት።
15ያዕቆብም እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር የተነጋገረበትን ስፍራ ቤቴል ብሎ ጠራው።
16ከዚያም ከቤቴል ተነሥተው ሄዱ፤ ኤፍራታ ለመድረስ ጥቂት ሲቀራቸው ራሔልን ምጥ ያዛት፣ ምጡም ጠናባት።
17ምጧ እየበረታ በሄደ ጊዜ አዋላጅቱ፣ “አይዞሽ አትፍሪ፤ ሌላ ወንድ ልጅ ልትወልጂ ነው” አለቻት።
18እርስዋ ግን ልትሞት ታጣጥር ስለነበር ከመሞቷ በፊት ልጅዋን ‘ቤንኦኒ’ አለችው፤ አባቱ ግን ‘ብንያም’ አለው።
19ራሔል ሞተች፤ ወደ ኤፍራታ በሚወስደው መንገድ በቤተልሔም ተቀበረች።
20ያዕቆብም በራሔል መቃብር ላይ ሐውልት አቆመ፤ እስከዛሬም የራሔል መቃብር ምልክት ይኸው ሐውልት ነው።
21ያዕቆብ ጉዞውን ቀጥሎ በዔዴር ግንብ ባሻገር ድንኳን ተክሎ ሰፈረ።
22ያዕቆብ በዚያ ምድር ሲኖር ሳለ፣ ሮቤል ከአባቱ ቁባት ከባላ ጋር የግብረሥጋ ግንኙነት አደረገ፤ ያዕቆብም ይህን ነገር ሰማ ያዕቆብ ዐሥራ ሁለት ወንዶች ልጆች ነበሩት፣ እነርሱም፦
23የልያ ልጆች፦ የያዕቆብ የበኩር ልጅ ሮቤል፣ ስምዖን፣ ሌዊ፣ ይሁዳ፣ ይሳኮር፣ ዛብሎን፤
24የራሔል ልጆች፦ ዮሴፍ፣ ብንያም፤
25የራሔል አገልጋይ የባላ ልጆች፦ ዳን፣ ንፍታሌም፤
26የልያ አገልጋይ የዘለፋ ልጆች፦ ጋድ፣ አሴር፣ ናቸው። እነዚህ ወንዶች ልጆች ያዕቆብ በመስጴጦምያ ሳለ የተወለዱለት ናቸው።
27ያዕቆብ በቂርያት አርባቅ (በኬብሮን) አጠገብ መምሬ በምትባል ስፍራ ወደሚኖረው አባቱ ወደ ይስሐቅ ሄደ፤ ይህም ስፍራ አብርሃምና ይስሐቅ የኖሩበት ነው።
28ይስሐቅ መቶ ሰማንያ ዓመት ኖረ፤
29አርጅቶ ዕድሜ ጠግቦ ሞተ፤ ወደ ወገኖቹ ተሰበሰበ፤ ልጆቹም ዔሳውና ያዕቆብ ቀበሩት።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።