መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ኦሪት ዘፍጥረት 34

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ልያ ለያዕቆብ የወለደችለት ሴት ልጅ ዲና፤ አንድ ቀን የዚያን አገር ሴቶች ለማየት ወጣች።
2የአገሩ ገዥ የኤዊያዊ የኤሞር ልጅ ሴኬም ባያት ጊዜ ያዛት በማስገደድም ክብረ ንጽሕናዋን ደፈረ።
3ልቡ በያዕቆብ ልጅ በዲና ተማረከ፤ ልጅቷንም በጣም ወደዳት፤ በጣፈጠም አንደበት አናገራት።
4ሴኬምም አባቱን ኤሞርን፣ “ይህችን ልጅ አጋባኝ” አለው።
5ያዕቆብ የልጁን የዲናን ክብረ-ንጽሕና ሴኬም እንደደፈረ ሰማ፤ ነገር ግን ወንዶች ልጆቹ የከብት መንጋ ይዘው ተሰማርተው ስለነበር፣ እነርሱ እስኪመጡ ዝም ብሎ ቆየ፤
6ከዚያም የሴኬም አባት ኤሞር፣ ያዕቆብን ሊያነጋግረው ወጣ።
7የያዕቆብ ወንዶች ልጆችም የተፈጸመውን ድርጊት እንደሰሙ ወዲያውኑ ከመስክ መጡ፤ ሴኬም መደረግ የማይገባውን አስነዋሪ ነገር በእስራኤል ላይ በመፈጸም የያዕቆብን ልጅ ስለደፈረ አዘኑ እጅግም ተቆጡ።
8ኤሞር ግን እንዲህ አላቸው፤ “ልጄ ሴኬም ልጃችሁን በጣም ወዶአታል፤ ስለዚህ እንዲያገባት ፍቀዱለት፤
9በጋብቻ እንተሳሰር፣ ሴት ልጃችህን ስጡን፣ የእኛንም ሴቶች አግቡ።
10አብራችሁንም መኖት ትችላላችሁ፤ አገራችን አገራችሁ ናት፣ ኑሩባት፤ ነግዱባት፣ ሀብት ንብረትም አፍሩባት።
11ሴኬም ደግሞ የዲናን አባትን ወንድሞች እንዲህ አላቸው። “በእናንተ ዘንድ ሞገስ ላግኝ እንጂ የተጠየቅሁትን ሁሉ እሰጣለሁ፤
12ለሙሽራዋም ጥሎሽ የፈለጋችሁትን ያህል ጠይቁኝ፤ እርሷን እንዳገባ ፍቀዱልኝ እንጂ፣ የፈለጋችሁትን ሁሉ ለመጠት ዝግጁ ነኝ።”
13ሴኬም እኅታቸውን ዲናን አስነውሮ ስለነበር የያዕቆብ ልጆች ለእርሱና ለአባቱ በተንኮል እንዲህ ሲሉ መለሱላቸው፣
14እንዲህ አሉአቸው፤ “እኅታችንን ላልተገረዘ ሰው ብንሰጥ ውርደት ስለሚሆንብን፣ እንዲህ ያለውን ነገር አናደርገውም።
15ሆኖም የምንስማማበት አንድ መንገድ ብቻ አለ፤ ይኸውም አንተና በእናንተ ዘንድ ያሉት ወንዶች ሁሉ እንደኛ የተገረዛችሁ እንደሆነ ነው።
16እንዲህ ከሆነ እናንተ የእኛን ሴቶች ልጆች ታገባላችሁ፣ እኛም የእናንተን ሴቶች ልጆች እናገባለን፣ አንድ ሕዝብ ሆነንም አብረን እንኖራለን።
17ዐሳባችንን ባትቀበሉና ባትገረዙ ግን እኅታችንን ይዘን እንሄዳለን።
18ያቀረቡትም ዐሳብ ለኤሞርና ለልጁ ለሴኬም መልካም መስሎ ታያቸው።
19ከአባቱ ቤተሰብ ሁሉ እጅግ የተከበረው ይህ ወጣት የያዕቆብን ልጅ እጅግ ወዶአት ስለነበር፣ ያሉትን ለማድረግ ጊዜ አልወሰደበትም።
20ስለዚህ ኤሞርና ልጁ ሴኬም ይህንኑ ለወገኖቻቸው ለመንገር ወደ ከተማቸው በር ሄዱ፤
21እንዲህም አሏቸው፤ “እነዚህ ሰዎች ከእኛ ጋር የሚኖሩት በሰላም ነው፣ በምድሪቱ ላይ አብረው ይቀመጡ፣ ተዘዋውረውም እንዲነግዱ እንፍቀድላቸው፤ ምድሪቱ እንደሆን ለእኛም ለእነርሱም ትበቃለች። ሴቶች ልጆቻቸውን እናገባለን፤ እነርሱም የእኛን ሴቶች ልጆች ያገባሉ፤
22ሆኖም ሰዎቹ ከእኛ ጋር እንደ አንድ ሕዝብ ሆነው አብረውን ለምኖር ፈቃደኞች የሚሆኑት፣ የእኛ ወንዶች እንደ እነርሱ የተገረዙ እንደሆነ ብቻ ነው።
23ታዲያ እንዲህ ብናደርግ ከብታቸው ንብረታቸው፣ እንስሶቻቸውም ሁሉ የእኛው ይሆኑ የለምን? ስለዚህ ባሉት እንስማማ፣ እነርሱም አብረውን ይኑሩ።”
24የከተማይቱ ነዋሪዎች ሁሉ ኤሞርና ሴኬም ባቀረቡት ዐሳብ ተስማምተው ወንዶቹ ሁሉ ተገረዙ።
25በሦስተኛውም ቀን የሁሉም ቁስል ገና ትኩስ ሳለ ከያዕቆብ ልጆች ሁለቱ፣ የዲና ወንድሞች ስምዓንና ሌዊ፣ ሰይፋቸውን መዘው ሳይታሰብ ወደ ከተማይቱ ገብተው ወንዶቹን በሙሉ ገደሏቸው።
26ኤሞርንና ሴኬምንም በሰይፍ ገድለው፣ እኅታቸውን ዲናን ከሴኬም ቤት አውጥተው ይዘዋት ተመለሱ።
27የቀሩትም የያዕቆብ ልጆች እኅታቸውን ስለደፈሩባቸው ወደ ሞቱት ሰዎች ቤት እየገቡ ከተማይቱን በሙሉ ዘረፉ።
28የበግና የፍየል መንጎቻቸውን፣ ከብቶቻቸውንና አህዮቻቸውን እንዲሁም በከተማይቱና በአካባቢው የሚገኘውን ንብረታቸውን ሁሉ ወሰዱባቸው፤
29ሀብታቸውን ሁሉ ዘርፈው ሴቶቻቸውንና ሕፃናቶቻቸውን ሁሉ ማርከው በየቤቱ ያገኙትን ሁሉ ይዘው ሄዱ።
30ያዕቆብ ስምዖንና ሌዊን እንዲህ አላቸው፤ “በእኔ ላይ ከባድ ችግር አመጣችሁብኝ፤ እነሆ፣ በዚህ ድርጊት የተነሣ በዚህች ምድር የሚኖሩ ከነዓናውያንና ፌርዛውያን ይጠሉኛል፤ እኛ በቁጥር አነስተኞች ነን፣ እነርሱ ተባብረው ቢያጠቁን እኔና ቤተሰቤ እንጠፋለን።”
31ስምዖንና ሌዊ ግን፣ “ታዲያ ሴኬም እኅታችንን እንደዝሙት አዳሪ ይድፈራትን?” አሉት።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።