1ያዕቆብ አሻግሮ ተመለከተ፤ እነሆ፣ ዔሳው አራት መቶ ሰዎች አስከትሎ እየመጣ ነበር። ስለዚህ ያዕቆብ ልጆቹን ለልያ ለራሔልና ለሁለቱ አገልጋዮቹ አከፋፈላቸው።
2ከዚያም ሁለቱን አገልጋዮች ከነልጆቻቸው አስቀደመ፤ ልያንና ልጆቿንም አስከተለ፤ ራሔልንና ዮሴፍን ግን ከሁሉ ኋላ እንዲሆኑ አደረገ።
3እርሱ ራሱም ቀድሞአቸው ሄደ፤ ወንድሙም ዘንድ እስኪደርስ ድረስ ሰባት ጊዜ ወደ መሬት ለጥ ብሎ እጅ ነሣ።
4ዔሳው ግን ሊገናኘው ወደ እርሱ ሮጦ ሄዶ አቀፈው፤ በአንገቱም ላይ ተጠምጥሞ ሳመው፤ ሁለቱም ተላቀሱ።
5ከዚያም ዔሳው ቀና ብሎ ሲመለከት ሴቶቹንና ልጆቹን ዐየ፤ እርሱም፣ “እነዚህ አብረውህ ያሉ እነማን ናቸው?” ብሎ ጠየቀው። ያዕቆብም መልሶ፣ “እነዚህማ እግዚአብሔር በቸርነቱ ለእኔ ለአገልጋይህ የሰጠኝ ልጆች ናቸው” አለው።
6በዚህ ጊዜ ሁለቱ ሴት አገልጋዮችና ልጆቻቸው ቀርበው እጅ ነሡ፤
7ከዚያም ልያና ልጆቿ መጥተው እጅ ነሡ፤ በመጨረሻም ዮሴፍና ራሔል መጡ፤ እነርሱም ቀርበው እጅ ነሡ።
8ዔሳውም፣ “ወደ እኔ ተነድቶ የመጣው ይህ ሁሉ መንጋ ምንድነው?” አለው። ያዕቆብም፣ “ጌታዬ ሆይ፣ በአንተ ዘንድ ሞገስ ባገኝ ብዬ ነው” አለው።
9ዔሳው ግን፣ “ወንድሜ ሆይ፤ እኔ በቂ አለኝ፤ የራስህን ለራስህ አድርገው” አለው።
10ያዕቆብም፣ “የለም፣ እንዲህ አይደለም፤ በአንተ ዘንድ ሞገስ አግኝቼ እንደሆነ፣ እጅ መንሻዬን ተቀበል፤ በመልካም ሁኔታ ተቀብለኸኝ ፊትህን ማየት መቻሌ ራሱ፣ የእግዚአብሔርን ፊት የማየት ያህል እቆጥረዋለሁ።
11እግዚአብሔር በቸርነቱ አሟልቶ ስለ ሰጠኝ የሚያስፈልገኝ ሁሉ አለኝና ያቀረብሁልህን እጅ መንሻ እባክህ ተቀበለኝ” አለው። ያዕቆብ አጥብቆ ስለለመነው፣ ዔሳው እጅ መንሻውን ተቀበለ።
12ዔሳውም፣ “እንግዲህ እንሂድ፤ እኔም ከአንተ ቀድሜ እሄዳለሁ” አለው።
13ያዕቆብ ግን እንዲህ አለው፤ “ጌታዬ እንደምታየው ልጆቹ ይህን ያህል የጠኑ አይደሉም፣ ለሚያጠቡት በጎችና ጥገቶች እንክብካቤ ማድረግ አለብኝ፤ እንስሳቱ ለአንዲት ቀን እንኳ በጥድፊያ ቢነዱ በሙሉ ያልቃሉ።
14ስለዚህ ጌታዬ፣ አንተ ቀድመኸኝ ሂድ፤ እኔም በምነዳቸው እንስሳትና በልጆቹ ጉዞ አቅም ልክ እያዘገምሁ ሴይር ላይ እንገናኛለን”
15ዔሳው፣ “እንግዲያስ ከሰዎቼ ጥቂቶቹን ልተውልህ” አለው። ያዕቆብ ግን፣ “ለምን ብለህ? በአንተ ዘንድ ሞገስ ማግኘቴ ይበቃኛል” አለው።
16ስለዚህ ዔሳው በዚሁ ዕለት ወደ ሴይር ለመመለስ ተነሣ።
17ያዕቆብ ግን ወደ ሱኮት ሄደ፤ እዚያም ለራሱ መጠለያ፣ ለከብቶቹም በረት ሠራ፤ ከዚህም የተነሣ የቦታው ስም ሱኮት ተባለ።
18ያዕቆብ ከመስጴጦምያ በተመለሰ ጊዜ በከነዓን ምድር ወዳለችው ወደ ሴኬም በሰላም ደረሰ፤ በከተማይቱም ፊት ለፊት ሰፈረ።
19ድንኳኑን የተከለበትንም ቦታ የሴኬም አባት ከነበረው ከኤሞር በመቶ ጥሬ ብር ገዛው፤
20በዚያም መሠዊያ አቁሞ፤ ኤል ኤሎሄ እስራኤል ብሎ ጠራው።