1ያዕቆብ በጉዞ ላይ ሳለ የእግዚአብሔር መላእክት በመንገድ ተገናኙት።
2ባያቸውም ጊዜ፤ “ይህ የእግዚአብሔር ሰፈር ነው” አለ፤ የዚያንም ቦት ስም መሃናይም አለው።
3ያዕቆብም በኤዶም አገር ሴይር በተባለው ምድር ወደሚኖረው ወንድሙ ወደ ዔሳው መልእክተኞችን አስቀድሞ ላከ፤
4እንዲህም ብሎ አዘዛቸው፤ “ጌታዬን ዔሳውን እንዲህ ትሉታላችሁ፤ ‘አገልጋይህ ያዕቆብ እንዲህ ብሎአል በሉት፤ ከላባ ዘንድ ተቀምጬ እስካሁን ድረስ እዚያው ኖርሁ፤
5ከብቶች፣ አህዮች፣ የበግና የፍየል መንጎች እንደዚሁም የወንድን የሴት አገልጋዮች አሉኝ፤ አሁንም ይህን መልእክት ለጌታዬ መላኬ በአንተ ዘንድ ሞግስ አገኛለሁ በሚል ተስፋ ነው።’”
6የተላኩትም ሰዎች ወደ ያዕቆብ ተመልሰው፣ “ወደ ወንድምህ ወደ ዔሳው ሄደን ነበር፤ እርሱም ከአንት ጋር ለመገናኘት በመምጣት ላይ ነው፤ ከእርሱም ጋር አራት መቶ ሰዎች አሉ” አሉት።
7በዚህ ጊዜ ያዕቆብ እጅግ በመፍራት ተጨነቀ፤ አብረውት የነበሩትንም ሰዎች በሁለት ክፍል መደባቸው፤ እንዲሁም በጎቹን፣ ፍየሎቹን፣ ከብቶቹንና ግመሎቹን በሁለት በሁለት መደባቸው።
8ይህንንም ያደረገው፦ “ዔሳው የመጀመሪያውን ክፍል ቢያጠቃ፣ ሌላው ክፍል ሊያመልጥ ይችላል” ብሎ በማሰብ ነው።
9ያዕቆብ እንዲህ ሲል ጸለየ፤ “የአባቴ የአብርሃም አምላክ፣ የአባቴ የይስሐቅ አምላክ ሆይ፣ ‘ወደ አገርህና ወደ ዘመዶችህ ተመልስ፣ እኔም በጎ ነገር አደርግልሃለሁ’ ያልኸኝ እግዚአብሔር ሆይ፣
10እኔ ባሪይህ እስካሁን ላደረግህልኝ ቸርነትና ታማኝነት ብቁ አይደለሁም፤ ዮርዳኖስን ስሻገር በእጄ ላይ ከነበረው በትር በስተቀር ምንም አልነበረኝም፤ አሁን ግን ይኸው ሁለት ሠራዊት ሆኛለሁ።
11ከወንድሜ ከዔሳው እጅ እንድታድነኝ እለምንሃለሁ፤ መጥቶ እኔንም ሆነ እነዚህን እናቶች ከነልጆቻቸው ያጠፋናል ብዬ ፈርቻለሁኝ፤
12ነገር ግን አንተ ራስህ፣ ‘አበለጽግሃለሁ፤ ዘርህንም ሊቆጠር እንደማይችል እንደ ባሕር አሸዋ አበዛዋለሁ’ ብለኸኛል።”
13በዚያችም ሌሊት ያዕቆብ እዚያው አደረ፤ ካለው ሀብት ለወንድሙ ለኤሳው እጅ መንሻ እንዲሆኑ እነዚህን መረጠ፦
14ሁለት መቶ እንስት ፍየሎችና ሃያ አውራ ፍየሎች፣ ሁለት መቶ እንስት በጎችና ሃያ አውራ በጎች፣
15ሠላሳ የሚያጠቡ ግመሎች ከነግልገሎቻቸው፣ አርባ ላሞችና ዐሥር ኮርማዎች፣ ሃያ እንስት አህዮችና ዐሥር ተባት አህዮች።
16እነዚህንም በየመንጋው ለይቶ፣ የሚነዱአቸውን ጠባቂዎች መደበላቸው፤ ጠባቂዎችንም እናንተ ቀድማችሁ ሂዱ፣ መንጋዎቹንም አራርቃችሁ ንዱአቸው” አላቸው።
17ቀድሞ የሚሄደውንም እንዲህ ሲል አዘዘው፤ ዔሳው አግኝቶህ ‘የማን ነህ? ወዴትስ ትሄዳለህ? የምትነዳውስ ይህ ሁሉ ከብት የማን ነው?’ ብሎ ቢጠይቅህ፣
18‘የአገልጋይህ የያዕቆብ ናቸው፤ ለጌታዬ ለዔሳው እጅ መንሻ የሰደዳቸው ናቸው፤ እርሱም ከበስተኋላችን እየመጣ ነው’ ብለህ ንገረው
19እንዲሁም ሁለተኛውን፣ ሦስተኛውንና መንጎቹን የሚነዱትን ሌሎቹንም ሁሉ እንዲህ ሲል አዘዛቸው፤ ‘ዔሳውን ስታገኙት ይህንኑ ትነግሩታላችሁ፤
20በተጨማሪም ‘አገልጋይህ ያዕቆብ ከኋላችን እየመጣ ነው’ በሉት። ይህንንም ያዘዘው፣ ‘ዔሳው ከእኔ ጋር ከመገናኘቱ በፊት እጅ መንሻዬ አስቀድሞ ቢደርሰው ምናልባት ልቡ ይራራና በሰላም ይቀበለኛል’ ብሎ ስላሰበ ነበር።
21ስለዚህ የያዕቆብ እጅ መንሻ ከእርሱ አስቀድሞ ተላከ፤ እርሱ ራሱ ግን እዚያው በሰፈሩ ቦታ አደረ።
22በዚያኑ ሌሊት ያዕቆብ ተነሣ ሁለቱን ሚስቶቹን፣ ሁለቱን ሴት አገልጋዮቹንና ዐሥራ አንዱን ልጆቹን ይዞ የያቦቅን ወንዝ ተሻገረ።
23ወንዙን አሻግሮ ከሸኛቸው በኋላ፣ ጓዙን ሁሉ ሰደደ።
24ያዕቆብም ብቻውን እዚያ ቀረ፤ አንድ ሰውም እስኪነጋ ድረስ ሲታገለው አደረ።
25ያም ሰው ያዕቆብን ታግሎ ማሸነፍ እንዳቃተው በተረዳ ጊዜ፣ የጭኑን ሹልዳ መታው፣ ያዕቆብም በሚታገልበት ጊዜ ጭኑ ከመገጣጠሚያው ላይ ተለያየ፤
26በዚያን ጊዜ ሰውዬው፣ “እንግዲህ መንጋቱ ስለሆን ልቀቀኝና ልሂድ” አለው። ያዕቆብም፣ “ካልባረክኸኝ አልለቅህም” አለው።
27ሰውዬውም፣ “ስምህ ማን ነው?” አለው። እርሱም፣ “ያዕቆብ ነው” አለ።
28ሰውዬውም፣ “ከእግዚአብሔርም ከሰዎችም ጋር ታግለህ አሸንፈሃልና ከእንግዲህ ስምህ እስራኤል እንጂ ያዕቆብ አይባልም” አለው።
29ያዕቆብም፣ “እባክህ ስምህን ንገረኝ” ብሎ ጠየቀው። ሰውዬውም፣ “ስሜን ለማወቅ ለምን ፈለግህ?” አለው፤ በዚያም ስፍራ ባረከው።
30ስለዚህ ያዕቆብ “እግዚአብሔርን ፊት ለፊት ዐይቼ እንኳ ሕይወቴ ተርፋለች” ሲል የዚያን ቦታ ስም ጵኒኤል አለው።
31ጵኒኤልንም እንዳለፈ ፀሐይ ወጣችበት፣ እርሱም በጭኑ ምክንያት ያነክስ ነበር።
32ከዚህም የተነሣ የእስራኤል ልጆች ሹልዳን ከጭኑ ጋር የሚያገናኘውን ሥጋ አይበሉም፤ ምክንያቱም ያዕቆብ ከሰውዬው ጋር ሲታገል ሰውዬው ሹልዳውን መትቶት ስለነበር ነው።