መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ኦሪት ዘፍጥረት 31

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1የላባ ወንዶች ልጆች፣ “ያዕቆብ የአባታችንን ሀብት እንዳለ ወስዶታል፤ ይህ ሁሉ እርሱ ያከማቸውም ሀብት ከአባታችን የተገኘ ነው” እያሉ ሲያወሩ ያዕቆብ ሰማ።
2በላባም ዘንድ እንደቀድሞ ተወዳጅ አለመሆኑን ተረዳ።
3እግዚአብሔርም ያዕቆብን፣ “ወደ አባቶችህ ወደ ዘመዶችህ አገር ተመለስ፤ እኔም ከአንተ ጋር እሆናለሁ” አለው።
4ስለዚህ ያዕቆብ መንጋዎቹ ወደ ተሰማሩበት መስክ እንዲመጡ ራሔልንና ልያን አስጠራቸው፤
5እንዲህም አላቸው፤ “አባታችሁ ስለ እኔ ያለው አመለካከት እንደ ቀድሞ አለመሆኑን ተረድቻለሁ፤ ቢሆንም የአባቴ አምላክ አልተለየኝም፤
6መቼም ባለኝ አቅም አባታችሁን ማገልገሌን እናንተ ታውቃላችሁ።
7አባታችሁ ደመወዜን ዐሥር ጊዜ እየለዋወጠ አታልሎኛል፣ ሆኖም እንዲጎዳኝ እግዚአብሔር አልፈቀደለትም።
8እርሱ፣ ‘ደመወዝህ ዝንጉርጉሮቹ ይሆናሉ ሲለኝ፣ መንጎቹ ሁሉ ዝንጉርጉር ወለዱ’፤ ደግሞም፣ ‘ደመወዝህ ሽመልመሌዎቹ ይሆናሉ ሲለኝ፣ መንጎቹ ሁሉ ሽመልመሌ መልክ ያላቸውን ወለዱ፤
9ስለዚህ እግዚአብሔር የአባታችሁን ከብቶች ወስዶ ለእኔ ሰጠኝ።
10እንስሳቱ በሚጠቁበት ወራት የሚያጠቋቸው አውራ ፍየሎች ሽመልመሌ፣ ዝንጉርጉርና ነቁጣ መሆናቸውን በሕልም አየሁ።
11በዚያው ሕልም የእግዚአብሔር መልአክ፦ ‘ያዕቆብ’ ብሎ ጠራኝ፣ እኔም ‘እነሆ አለሁ’ አልሁ።
12እርሱም እንዲህ አለኝ፦ ‘መንጋዎቹን የሚያጠቋቸው አውራ ፍየሎች ሽመልመሌ፣ ዝንጉርጉርና ነቁጣ ያለባቸው መሆናቸውን ተመልከት፣ ላባ የፈጸመብህን በደል አይቻለሁ።
13የድንጋይ ሐውልት በማቆም ዘይት ቀብተህ የተሳልህባት የቤቴል አምላክ እኔ ነኝ፤ አሁንም ይህን አገር ፈጥነህ ልቀቅ ወደ ተወለድህበትም ምድር ተመልሰህ ሂድ’ አለኝ።”
14ራሔልና ልያም እንዲህ ብለው መለሱለት፦ “ከአባታችን የምንወርሰው ድርሻ አለን?
15እርሱ እኛን የሚያየን እንደ ባዕዳን አይደለምን? ደግሞም እኮ እኛን ሽጦናል፣ የተሸጥንበትንም ዋጋ ራሱ በልቶታል።
16እግዚአብሔር ከአባታችን ወስዶ ለአንተ የሰጠው ሀብት ሁሉ የእኛና የልጆቻችን ነው፤ ስለዚህ እግዚአብሔር የነገረህን ሁሉ አድርግ።”
17ከዚያም ያዕቆብ ተነሥቶ ልጆቹንና ሚስቶቹን በግመሎች ላይ አስቀመጠ፤
18በመስጴጦምያ ካፈራው ሀብት ሁሉ ጋር ከብቶቹን በሙሉ ወደፊት አስቀደመ፣ ወደ አባቱም ወደ ይስሐቅ አገር፣ ወደ ከነዓን ምድር ጉዞውን ቀጠለ።
19ላባ በጎቹን ሊሸልት ሄዶ ስለነበር፣ እርሱ በሌለበት ራሔል ከቤት የነበሩትን የአባቷን ጣዖቶች ሰርቃ ሄደች።
20ያዕቆብ መሄዱን ለላባ ሳይገልጥለት አታሎት ሄደ፣
21የራሱ የሆነውን ሀብት ይዞ በፍጥነት ታጓዘ፤ የኤፍራጥስንም ወንዝ ተሻግሮ ወደ ኮረብታማው አገር ወደ ገለዓድ ሄደ።
22ያዕቆብ መኮብለሉን ለላባ በሦስተኛው ቀን ተነገረው።
23ከዘመዶቹ ጋር ሆኖ ያዕቆብን ተከታተለው፤ ሰባት ቀን ከተጓዙ በኋላ ገለዓድ በተባለው ተራራማ አገር ላይ ሊደርስበት ተቃረበ።
24በዚያን ሌሊት እግዚአብሔር ለላባ በሕልም ተገለጠለትና “ያዕቆብን ክፉም ሆን ደግ እንዳትናገረው ተጠንቀቅ” አለው።
25ያዕቆብ ገለዓድ በተባለው ኮረብታማ ስፍራ ድንኳኑን በመትከትል ሰፍሮ ሳለ ላባ ደረሰበት፤ ላባና ዘመዶቹም እዚያው ድንኳናቸውን ተክለው ሰፈሩ።
26ከዚህ በኋላ ላባ ያዕቆብን እንዲህ አለው፦ “ስለምን እንዲህ አድርገህ አታለልኸኝ፤ ሴቶች ልጆቼንስ በጦርነት እንደተማረኩ ያህል ይዘሃቸው ለምን ሄድህ?
27ሳትነግረኝ ተሰውረህ በመሄድ ለምን አታለልኽኝ? ነግረኸኝ ቢሆን በከበሮና በመስንቆ እየተዘፈነ በደስታ በሸኘሁህ ነበር።
28ልጆቼንና የልጅ ልጆቼን በመሳም እንድሰናበታቸው ባለማድረግህ የሞኝነት ተግባር ፈጽመሃል።
29ጉዳት ሳደርስብህ እችል ነበር፣ ነገር ግን ባለፈው ሌሊት የአባትህ አምላክ፣ ‘ያዕቆብን ክፉም ሆነ ደግ አንድ ቃል እንዳትናገረው’ ብሎ አስጠነቀቀኝ፣
30ወደ ትውልድ አገርህ ለመመለስ ባለህ ብርቱ ፍላጎት እንደተለየኸኝ አውቃለሁ፣ ታዲያ የቤቴን ጣዖቶች የሰረቅኽብኝ ለምንድነው?”
31ለላባ እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “ሴቶች ልጆችህን በኃይል ነጥቀህ ታስቀርብኛለህ ብዬ ስለ ፈራሁ ነው በድብቅ የሄድኩት።
32ነገር ግን ከእኛ መካከል የአንተን የጣዖት ምስል የሰረቀ ሰው ካለ ይሙት። የአንተ የሆነ አንዳች ነገር ከኔ ዘንድ ቢገኝ፣ አንተው ራስህ ዘመዶቻችን ባሉበት ፈልግና ውሰድ።” እንደዚህ ሲል ራሔል የጣዖታቱን ምስል መስረቋን ያዕቆብ አያውቅም ነበር።
33ላባም ወደ ያዕቆብ ድንኳንና ወደ ልያ ድንኳን እንዲሁም ወደ ሁለቱ ደንገጡሮቹ ድንኳን ገባ፤ ነገር ግን ምንም አላገኘም። ከልያ ድንኳን ከወጣ በኋላ ወደ ራሔል ድንኳን ገባ።
34ራሔል ግን ጣዖቱቹን ወስዳ በግመሉ ኮርቻ ሥር በመሰወር በላያቸው ተቀምጣባቸው ነበር። ላባ በድንኳኑ ውስጥ ያለውን ጓዝ ሁሉ በርብሮ ምንም ነገር አላገኘም።
35ራሔልም አባቷን፦ “በፊትህ ተነሥቼ መቆም ስላልቻልሁ፣ ጌታዬ አትቆጣ የወር አበባዬ መጥቶ ነው” አለችው፤ ስለዚህ በረበረ፤ የጣዖቱን ምስል ግን ማግኘት አልቻለም።
36በዚህ ጊዜ ያዕቆብ ተቆጣ፤ ላባንም እንዲህ ሲል ወቀሰው፦ “እስቲ ወንጀሌ ምንድን ነው? ይህን ያህል የምታሳድደኝ ኃጢአቴ ምን ቢሆን ነው?
37ዕቃዬን አንድ በአንድ በርብረሃል፤ ታዲያ የአንተ ሆኖ ያገኘኸው ዕቃ የትኛው ነው? ካለ፣ እስቲ በአንተም በእኔም ዘመዶች ፊት አቅርብና እነርሱ ያፋርዱን።
38ሃያ ዓመት አብሬህ ኖሬአለሁ፤ በጎችህና ፍየሎችህ አልጨነገፉም፤ ከመንጋህም አንድ ጠቦት እንኳ አልበላሁም።
39አውሬ የሰበረውንም ቢሆን እተካ ነበር፣ በቀንም ሆነ በሌሊት የተሰረቁትን ሁሉ ስታስከፍለኝ ኖረሃል።
40ብዙ ጊዜ በቀን ሐሩርና በሌሊት ቁር እሠቃይ ነበር፤ በቂ እንቅልፍ ያገኘሁበት ጊዜ አልነበረም።
41ሃያ ዓመት በቤትህ የኖርሁት በዚህ ሁኔታ ነበር፤ ዐሥራ አራት ዓመት ለሁለቱ ልጆችህ ብዬ አገለገልሁ፤ ስድስት ዓመት ስለመንጋዎችህ ስል አገለገልሁ፤ ይህም ሆኖ ደመወዜን ዐሥር ጊዜ ለዋውጠኽብኛል።
42የአባቴ አምላክና እርሱም የሚፈራው የአብርሃም አምላክ ከእኔ ጋር ባይሆን ኖሮ ባዶ እጄን ሰድደኸኝ ነበር፤ እግዚአብሔር ግን መከራዬን ዐይቶ፣ ልፋቴን ትመልክቶ ትናንት ሌሊት ገሠጸህ።”
43ላባም ለያዕቆብ እንዲህ ሲል መለሰ፤ “እነዚህ ሴቶች የእኔው ልጆች ናቸው፤ ልጆቻቸውም የእኔ ናቸው፤ እነዚህም መንጋዎች የእኔ ናቸው፤ ይህ የምታየው ሁሉ የራሴ ነው፤ ታዲያ በእነዚህ ሴቶች ልጆቼና በወለዷቸው ልጆቻቸው ላይ ዛሬ ምን ማድረግ እችላለሁ?
44በል አሁን ቃል ኪዳን እንጋባ፤ ኪዳኑም በአንተና በእኔ መካከል ምስክር ይሁን።”
45ያዕቆብም ድንጋይ ውስዶ ሐውልት አድርጎ አቆመው፤
46ከዚያም ዘመዶቹን “ድንጋይ ሰብስቡ” አላቸው። እነርሱም ድንጋይ እያመጡ ከመሩ፤ በክምሩም አጠገብ ምግብ በሉ።
47ላባም ክምር ድንጋዩን ይጋርሠሀዱታ ብሎ ጠራው፤ ያዕቆብ ደግሞ ገለዓድ አለው።
48ላባም “ይህ ክምር ድንጋይ በእኔና በአንተ መካከል ዛሬ ምስክር ነው” አለው። ገለዓድ ተብሎ የተጠራውም በዚሁ ምክንያት ነው፤
49ደግሞም ምጽጳ ተባለ ምክንያቱም ላባ እንዲህ ብሎአልና፤ “እንግዲህ ከዚህ በምንለያይበት ጊዜ እግዚአብሔር እኔንና አንተን ይጠብቀን፤
50ልጆቼን ብትበድላቸው ወይም ሌሎችን በላያቸው ብታገባ፣ ማንም ከእኛ ጋር ባይኖርም እንኳ እግዚአብሔር በአንተና በእኔ መካከል ምስክር መሆኑን አትርሳ።”
51ላባም ያዕቆብን እንዲህ አለው፦ “ክምር ድንጋዩ እነሆ፤ በአንተና በእኔ መካካል ያቆምሁትም ሐውልት እነሆ፤
52ይህን ክምር ድንጋይ አልፌ አንተን ለማጥቃት ላልመጣ፣ አንተም ይህን ክምር ድንጋይና ይህን ሐውልት አልፈህ እኔን ለማጥቃት ላትመጣ፤ ይህ ክምር ድንጋይ ምስክር ነው፤ ይህም ሐውልት ምስክር ነው።
53የአብርሃም አምላክ፣ የናኮር አምላክ፣ የአባታቸውም አምላክ በመካከላችን ይፍረድ።” ስለዚህ ያዕቆብ አባቱ ይስሐቅ በሚፈራው በእግዚአብሔር ማለ።
54ያዕቆብ በኮረብታማው አገር ላይ መሥዋዕት አቀረበ፤ ዘመዶቹንም ምግብ እንዲበሉ ጋበዛቸው፤ እነርሱም ከበሉ በኋላ እዚያው አደሩ።
55በማግስቱም ማለዳ ላባ የልጅ ልጆቹን እንዲሁም ሴቶች ልጆችን ስሞ መረቃቸው፤ ከዚያም ወደ አገሩ ተመለሰ።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።