1ራሔል ለያዕቆብ አንድም ልጅ እንዳልወለደችለት ባየች ጊዜ በእኅቷ ቀናች። ያዕቆብንም፣ “ልጅ ስጠኝ አለበለዚያ እሞታለሁ” አለችው።
2ያዕቆብም ራሔልን ተቆጥቶ፤ “እኔ የሆድሽን ፍሬ በነሳሽ በእግዚአብሔር ቦታ ነኝን?” አላት።
3እርሷም፣ “እነሆ፣ አገልጋዬ ባላ አለችልህ፣ ልጆች እንድትወልድልኝና እኔም ደግሞ በእርሷ አማካይነት ልጆች እንዳገኝ ከእርሷ ጋር ተኛ” አለችው።
4ስለዚህ ባላን እንደሚስት አድርጋ ሰጠችው፤ ያዕቆብም ከእርሷ ጋር የግብረ-ሥጋ ግንኙነት አደረገ።
5ባላም አረገዘችና ወንድ ልጅ ወለደችለት።
6ራሔልም፦ “እግዚአብሔር ፈረደልኝ፣ ልመናዬንም ሰምቶ ወንድ ልጅ ሰጥቶኛል” አለች። ስለዚህ ስሙን ዳን ብላ ጠራችው።
7የራሔል አገልጋይ ባላ ዳግመኛ አረገዘችና ለያዕቆብ ሁለተኛ ወንድ ልጅ ወለደች።
8ከእኅቴ ጋር ብርቱ ትግል ታግዬ አሸነፍኋት” አለች። ስለዚህ ስሙን ንፍታሌም ብላ ጠራችው።
9ልያም ልጅ መውለድ ማቆሟን እንደተረዳች፣ አገልጋይዋን ዘለፋን ሚስት እንድትሆነው ለያዕቆብ ሰጠችው።
10የልያ አገልጋይ ዘለፋም ለያዕቆብ ወንድ ልጅ ወለደችለት፣
11ልያም፣ “እንዴት የታደልሁ ነኝ!” ስትል ስሙን ጋድ ብላ ጠራችው።
12የልያም አገልጋይ ዘለፋ ለያዕቆብ ሁለተኛ ልጅ ወለደችለት፤
13ልያም፣ “እጅግ ደስ ብሎኛል፣ ከእንግዲህ ወዲያ ሴቶች ‘ደስተኛዋ’ ይሉኛል አለች፤ ስሙንም ‘አሴር’ ብላ ጠራችው።
14በስንዴ መከር ወራት ሮቤል ወደ ዱር ሄዶ እንኮይ አገኘ፤ ለእናቱ ለልያም አመጣላት፤ ራሔልም ልያን፣ “እባክሽን ልጅሽ ካመጣልሽ እንኮይ ስጪኝ” አለቻት።
15ልያም፦ “ባሌን የቀማሽኝ አነሰና የልጄን እንኮይ ደግሞ ልትወስጂ አማረሽ?” አለቻት። ራሔልም፣ “ስለልጅሽ እንኮይ ዛሬ ያዕቆብ ከአንቺ ጋር ይደር” አለቻት።
16በዚያ ምሽት ያዕቆብ ከእርሻ ሲመለስ፣ ልያ ወጥታ ተቀበለችውና፣ “በልጄ እንኮይ ስለተከራየሁህ የዛሬው አዳርህ ከእኔ ጋር ነው” አለችው። ያዕቆብም በዚያች ሌሊት ከእርሷ ጋር አደረ።
17እግዚአብሔር የልያን ጸሎት ሰማ፣ ስለዚህ አረገዘችና ለያዕቆብ አምስተኛውን ወንድ ልጅ ወለደችለት።
18ልያም፦ “አገልጋዬን ለባሌ በመስጠቴ እግዚአብሔር ደመወዜን ከፈለኝ” አለች። ስሙንም ይሳኮር አለችው።
19ልያ አሁንም ደግማ ፀነሰች፤ ለያዕቆብም ስድስተኛውን ወንድ ልጅ ወለደች።
20እርሷም፣ “እግዚአብሔር በከበረ ስጦታ አድሎኛል፣ ስድስት ወንዶች ልጆች ስለወለድሁለት ከእንግዲህ ባሌ አክብሮ ይይዘኛል” አለች፤ ስሙንም ዛብሎን አለችው።
21ከዚያም በኋላ ሴት ልጅ ወለደች ስምዋንም ዲና አለቻት።
22እግዚአብሔርም ራሔልን አሰበ፤ ጸሎትዋንም ሰምቶ ልጅ እንድትወልድ አደረጋት፤
23አርግዛም ወንድ ልጅ ወለደችና፣ “እግዚአብሔር ዕፍረቴን አስወገደልኝ” አለች፤
24ደግሞም ሌላ ወንድ ልጅ ይጨምርልኝ ስትል ስሙን ዮሴፍ ብላ ጠራችው።
25ራሔል ዮሴፍን ከወለደች በኋላ ያዕቆብ ላባን እንዲህ አለው፦ “ወደ ተወለድሁበት አገር እንድመለስ አሰናብተኝ፤
26አንተን በማገልገል ያገኘኋቸውን ሚስቶቼንና ልጆቼን ስጠኝና ልሂድ፤ ምን ያህል አገልግሎት እንዳበረከትኩልህ ታውቃለህ።”
27ላባም፣ “በአንተ ምክንያት እግዚአብሔር እንደባረከኝ በንግርት መረዳቴን ልነግርህ እወዳለሁ፤
28የምትፈልገውን ደመወዝ ንገረኝና እከፍልሃለሁ” አለው።
29ያዕቆብም እንዲህ አለው፦ “እንዴት እንዳገለገልሁህና የከብትህም መንጋ በእኔ ጠባቂነት እንዴት እንደረባልህ አንተ ታውቃለህ፤
30እኔ ከመምጣቴ በፊት ጥቂት የነበሩት መንጋዎችህ አሁን እጅግ በዝተዋል፤ በተሰማራሁበት ሁሉ እግዚአብሔር በረከቱን አብዝቶልሃል። ታዲያ፣ ለራሴ ቤት የሚያስፈልገኝን የማቀርበው መቼ ነው?”
31ላባም፣ “ታዲያ ምን ያህል ልክፈልህ?” ብሎ ጠየቀው። ያዕቆብም እንዲህ ሲል መለሰ፦ “እኔ የምልህን አንድ ነገር ብቻ ብታደርግልኝ መንጋህን ማሰማራቴንና መጠበቄን እቀጥላልሁ፤
32ዛሬ በመንጋዎችህ መካከል ልለፍና ዝንጉርጉርና ነቁጣ ጥቁርም የሆኑትን በጎች ሁሉ ልለይ፤ እንዲሁም ነቁጣና ዝንጉርጉር የሆኑትን ፍየሎች እመርጣለሁ፤ እነርሱም ደመወዜ ይሆናሉ፤
33ወደፊት ደመወዜን ለመቆጣጠር በምትመጣበት ጊዜ ታማኝነቴ ይታወቃል፤ ደመወዜን ለመቆጣጠር ስትመጣ ዝንጉርጉር ያልሆነ ወይም ነቁጣ የሌለበት ፍየል ብታገኝ፣ እንዲሁም ጥቁር ያልሆነ በግ ብታገኝ የተሰረቀ መሆኑን መረዳት ትችላልህ” አለው።
34ላባም፣ “እሺ አንተ ባልከው እስማማለሁ” አለ።
35ነገር ግን በዚያኑ ዕለት ከተባት ፍየሎች ሽመልመሌ የሆኑትን ወይም ነቁጣ ያለባቸውን ሁሉ እንዲሁም ከእንስት ፍየሎች ነቁጣ ያለባቸውን ዝንጉርጉር የሆኑትን ሁሉ መረጠ፤ ደግሞም ጥቋቁር የሆኑትንም በጎች ሁሉ ለየና ወንዶች ልጆቹን አስጠበቃቸው።
36ከዚህ በኋላ ላባ መንጋውን ነድቶ የሦስት ቀን መንገድ ያህል ከያዕቆብ ርቆ ሄደ፤ ያዕቆብም የቀሩትን የላባን መንጋዎች መጠበቁን ቀጠለ።
37ያዕቆብም ልብን፣ ለውዝና ኤርሞን ከሚባሉ ዛፎች እርጥብ በትሮችን ወሰደ፤ በበትሮቹ ያለው ነጭ እንዲታይ ሽመልመሌ አድርጎ ላጣቸው፤
38መንጋዎቹ ውሃ ለመጠጣት ሲመጡ ከፊት ለፊት እንዲያዩአቸው የተላጡትን በትሮች በውሃ ማጠጫዎቹ ውስጥ አደረጋቸው። መንጎቹም ስሜታቸው ሲነሣሣና ውሃ ለመጠጣት ሲመጡ፣
39በትሮቹን ፊት ለፊት እያዩ ይሳረሩ ነበር፤ ሽመልመሌ፣ ዝንጉርጉርና ነቁጣ የጣለባቸውንም ግልገሎች ወለዱ።
40ያዕቆብ እነዚህን ግልገሎች ለብቻ ለየ፤ የቀሩትን ግን ዝንጉርጉርና ጥቁር በሆኑት በላባ መጋዎች ፊት ለፊት አቆማቸው፤ በዚህ ዓይነት የራሱን መንጋ ከላባ መንጋ ጋር ሳይቀላቅል ለብቻ አቆማቸው።
41ያዕቆብም ብርቱ እንስቶች አውራ ፈልገው በሚቅበጠበጡበት ጊዜ በትሮቹ አቅራቢያ እንዲጠቁ በትሮቹን በውሃ ገንዳዎች ውስጥ ፊት ለፊታቸው ያስቀምጥ ነበር፤
42ደካማ በሆኑት እንስቶች ፊት ግን በትሮቹን አያስቀምጥም ነበር፤ ስለዚህ ደካሞቹ ለላባ ሲሆኑ፣ ብርቱዎቹ ለያዕቆብ ሆኑ።
43በዚህም ሁኔታ ያዕቆብ እጅግ ባለጸጋ ሆነ፤ ብዙ መንጋዎች፤ ሴቶችና ወንዶች አገልጋዮች፣ ብዙ ግመሎችና አህዮችም ነበሩት።