መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ኦሪት ዘፍጥረት 2

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1የምድር በውስጣቸው ያሉትም ሕያዋን ፍጡራን አፈጣጠር በዚህ ሁኔታ ተከናወነ።
2እግዚአብሔር ይሠራ የነበረውን ሥራ በሰባተኛው ቀን ፈጽሞ በዚሁ ቀን ከሥራው ሁሉ አረፈ።
3እግዚአብሔር የመፍጠር ሥራውን ሁሉ ፈጽሞ ያረፈው በዚህ ቀን ስለሆነ ሰባተኛውን ቀን ባረከው ቀደሰውም።
4እግዚአብሔር አምላክ ሰማይንና ምድርን በፈጠረበት ወቅት የሰማይና የምድር የአፈጣጠራቸው ታሪክ እንደዚህ ነበር።
5እግዚአብሔር አምላክ በምድር ላይ ዝናብ እንዲዘንብ ስላደረገና ምድርንም የሚያለማ ሰው ባለመኖሩ በምድር ላይ ምንም ቡቃያ አልነበረም፣ በምድር ላይ የሚበቅል ተክልም ገና አልበቀለም።
6ነገር ግን ውሃ ከመሬት እየመነጨ የምድርን ገጽ ያረሰርስ ነበር።
7እግዚአብሔር አምላክም ከምድር አፈር ሰውን አበጀው፤ በአፍንጫውም የሕይወት እስትንፋስ እፍ አለበት፤ ሰውም ሕያው ነፍስ ያለው ሆነ።
8እግዚአብሔር አምላክም በስተምሥራቅ በኩል በዔደን የአትክልት ስፍራ አዘጋጀ፣ የአበጀውንም ሰው በዚያ አኖረው።
9ከምድር ውስጥም እግዚአብሔር አምላክ ለዓይን የሚያስደስቱና ለምግብነት የሚጠቅሙ ልዩ ልዩ ዛፎች እንዲበቅሉ አደረገ። በአትክልት ስፍራው መካከልም የሕይወት ዛፍ ነበር፣ መልካሙንና ክፉውን የሚያሳውቀውም ዛፍ በዚያ ነበር።
10የአትክልት ስፍራውንም የሚያጠጣ ወንዝ ከኤደን ይፈስ ነበር። ወንዙም ከኤደን ከወጣ በኋላ አራት ወንዞች ሆኖ ይከፋፈል ነበር።
11የመጀመሪያው ፊሶን የተባለው ወንዝ ነበር፣ ይህም ወርቅ ይገኝበት የነበረውን መላውን የሐዊላ ምድር አቋርጦ የሚፈስው ወንዝ ነበር።
12የዚያ አገር ወርቅ የጠራ ወርቅ ነበር፤ በተጨማሪም በዚያ አገር ሽቶና የከበሩ ድንጋዮች ነበሩ።
13የሁለተኛው ወንዝ ስም ግዮን ይባል ነበር፣ እርሱም መላውን የኢትዮጵያ ምድር አቋርጦ ይፈስ ነበር።
14የሶስተኛው ወንዝ ስም ጤግሮስ ይባል ነበር፣ እርሱም በአሦር በስተምሥራቅ ይፈሳል። አራተኛው ወንዝ ኤፍራጥስ ነበር።
15እግዚአብሔር አምላክም የኤደንን የአትክልት ስፍራ ያለማና ይንከባከብ ዘንድ ሰውን ወስዶ በዚያ አኖረው።
16እግዚአብሔር አምላክም እንዲህ በማለት አዘዘው፣ “በአትክልቱ ስፍራ ካለው ከማንኛውም የፍሬ ዛፍ መብላት ትችላልህ።
17ነገር ግን መልካሙንና ክፉውን ከሚያሳውቀው ዛፍ አትብላ፣ ምክንያቱም ከእርሱ በበላህ ቀን በእርግጥ ትሞታለህ።”
18ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር አምላክ፦ “ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም። ስለዚህ የምትመቸውን ረዳት እፈጥርለታለሁ” አለ።
19እግዚአብሔር አምላክም ከምድር አፈር የምድር እንስሶችንና የሰማይ ወፎችን አበጀ። ምን ስም እንደሚያወጣላቸው ይመለከት ዘንድ ወደ አዳም አመጣቸው። ለእያንዳንዱ ሕያው ፍጡር አዳም ያወጣለት ስም ያ ስሙ ሆነ።
20አዳም ለሁሉም ከብቶች፣ ለሁሉም የሰማይ ወፎችና ለምድር አራዊት ሁሉ ስም አወጣላቸው። ነገር ግን ለአዳም ለራሱ የምትመች ረዳት አልተገኘለትም።
21እግዚአብሔር አምላክ በአዳም ላይ ከባድ እንቅልፍ እንዲወስደው አደረገ፣ ስለሆነም አዳም አንቀላፋ። እግዚአብሔር አምላክ አዳም አንቀላፍቶ ሳለ ከጎድን አጥንቶቹ አንዱን ወስዶ አጥንቱን የወሰደበትን ስፍራ በሥጋ ዘጋው።
22እግዚአብሔር አምላክ ከአዳም ከወሰደው የጎድን አጥንት ሴት አድርጎ ሠራት። ወደ አዳምም አመጣት።
23አዳምም፦ “አሁን ይህቺ ከአጥንቴ የተገኘች አጥንት ከሥጋዬ የተገኘች ሥጋ ናት። ከወንድ ተገኝታለችና ሴት ትባል” አለ።
24ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል ከሚስቱም ጋር ይጣመራል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ።
25አዳምና ሚስቱ ሁለቱም ራቁታቸውን ነበሩ፤ ይሁን እንጂ አይተፋፈሩም ነበር።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።