1በዚህ ጊዜ ያህዌ አብራምን እንዲህ አለው፤ “አገርህን፣ ወገንህንና የአባትህን ቤተ ሰብ ትተህ እኔ ወደማሳይህ ምድር ሂድ፤
2ታላቅ ሕዝብ አደርግሃለሁ፤ እባርክሃለሁ፤ ስምህን ገናና አደርገዋለሁ፤ ለሌሎችም በረከት አደርግሃለሁ።
3የሚባርኩህን እባርካለሁ፤ የሚረግሙህንና የሚያዋርዱህን እረግማለሁ። በአንተ አማካይነት በምድር የሚኖሩ ሰዎች ሁሉ ይባረካሉ።”
4ስለዚህ አብራም ያህዌ እንዳዘዘው ወጣ፤ ሎጥም አብሮት ሄደ። አብራም ከካራን ተነሥቶ ሲሄድ፣ የሰባ አምስት ዓመት ሰው ነበር።
5አብራም ሚስቱ ሦራን፣ የውንድሙ ልጅ ሎጥን አስከትሎ በካራን ያፈሩትን ሀብትና የነበራቸውን አገልጋዮች ይዞ በመጓዝ፣ ከነዓን ምድር ገቡ።
6አብራም በሞሬ ያለው ግዙፍ የወርካ ዛፍ እስካለበት እስከ ሴኬም ዘልቆ ሄደ። በዚያ ዘመን ከነሻናውያን በዚህ ምድር ይኖሩ ነበር።
7ያህዌ ለአብራም ተገልጦ፣ “ይህችን ምድር ለዘርህ እሰጣለሁ” አለው። ስለዚህ አብራም ለተገለጠለት ለያህዌ በዚያ መሠዊያ ሠራ።
8ከዚያ በመነሣት ከቤቴል በስተ ምሥራቅ ወዳለው ተራራማ አገር ሄደ፤ ቤቴል በስተ ምዕራብ፣ ጋይ በስተ ምዕራብ ባለችበት ቦታ ድንኳኑን ተከለ። እዚያ ለያህዌ መሠዊያ ሠራ፤ የያህዌንም ስም ጠርቶ ጸለየ።
9አብራም ከዚያ ተነሥቶ ወደ ኔጌብ መጓዙን ቀጠለ።
10በዚያ ምድር ጽኑ ራብ ስለ ነበር አብራም እዚያ ጥቂት ጊዜ ለመቆየት ወደ ግብፅ ሄደ።
11ግብፅ በመግባት ላይ እያለ አብራም ሚስቱ ሦራን እንዲህ አላት፤ “መቼም አንቺ ቆንጆ ሴት መሆንሽን አውቃለሁ።
12ግብፃውያን ሲያዩሽ ‘ይህች ሚስቱ ናት’ ይላሉ፤ እኔን ይገድሉኛል፤ አንቺን ግን ይተዉሻል።
13ስለዚህ በአንቺ ምክንያት ለእኔ መልካም እንዲሆልኝ ሕይወቴም እንዲተርፍ እኅቱ ነኝ’ በዪ አላት።
14አብራም ወደ ግብፅ ሲገባ፣ ሦራ ምን ያህል ቆንጆ እንደ ሆነች ግብፃውያኑ አዩ።
15የፈርሾን ሹማምንት ባዩአት ጊዜ እርሷን እያደነቁ ለፈርዖን ነገሩት፤ ወደ ቤተ መንግሥትም ተወሰደች።
16በእርሷ ምክንያት ፈርኦን አብራምን በክብር አስተናገደው፤ በጎች፣ በሬዎች፣ ወንድ አህዮች ወንድና ሴት ባሪያዎች፣ ሴት አህዮችና ግመሎች ሰጠው።
17በአብራም ሚስት በሦራ ምክንያት ያህዌ ፈርዖንና ቤተ ሰቡን በታላቅ መቅሠፍት መታ።
18ፈርዖን አብራምን አስጠርቶ እንዲህ አለው፤ “ለመሆኑ ምን እያደረግህብኝ ነው? ሚስትህ መሆንዋን ለምን አልነገርከኝም?
19ለምን እኅቴ ናት አልከኝ? እኅቴ ናት ስላልከኝ ሚስቴ ላደርጋት ነበር። አሁንም ሚስትህ እቻት፤ ይዘሃት ሂድ”
20ከዚያም ፈርዖን አብራምን በተመለከተ ለባለሟሎቹ ትእዛዝ ሰጠ፤ እነርሱም አብራምን ከሚስቱና ከንብረቱ ሁሉ ጋር አሰናበቱት።