መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ዕዝራ 9

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1"እነዚህ ነገሮች በተደረጉ ጊዜ አለቆቹ ወደ እኔ መጥተው፥ 'የእስራአል ሕዝብ፥ ካህናቱና ሌዋውያኑ ራሳቸውን ከሌላው ምድር ሕዝብ፤ ከከነዓናውያን፥ ኬጢያውያን፥ ፌርዛውያን፥ ኢያቡሳውያን፥ አሞናውያን፥ ሞዓባውያን፥ ግብፃውያንና አሞራውያን እና ከርኩሰቶቻቸው አልለዩም።
2ከወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸው ጋር በመጋባት ቅዱሱን ሕዝብ ከሌላው ምድር ሕዝብ ጋር ደባልቀዋል። በዚህ እምነት የለሽነት ቀዳሚዎቹ ሹማምንቱና አለቆቹ ናቸው።'
3ይህንን በሰማሁ ጊዜ፥ ልብሴንና ካባዬን ቀደድሁ፥ ከራሴና ከፂሜም ላይ ፀጉሬን ነጨሁ። አፍሬም ተቀመጥኩ።
4ከእስራኤል አምላክ ከእግዚአብሔር ቃል የተነሣ ስለዚህ እምነት የለሽነት በፍርሃት የተንቀጠቀጡ ሁሉ እስከ ምሽቱ መሥዋዕት ማቅረቢያ ጊዜ ድረስ በእፍረት ተቀምጬ ሳለሁ ወደ እኔ መጡ።
5የምሽት መሥዋዕት በማቅረቢያ ጊዜ ግን የተቀደደ ልብሴንና ካባዬን ለብሼ በእፍረት ከተቀመጥኩበት ተነሣሁ፥ ተንበርክኬም እጆቼን ወደ አምላኬ ወደ እግዚአብሔር ዘረጋሁ።
6እንዲህም አልኩ፥ 'አምላኬ ሆይ፥ ኃጢአታችን በራሳችን ላይ በዝቷል፥ በደላችንም እስከ ሰማያት ደርሷልና ፊቴን ወደ አንተ ለማቅናት እፈራለሁ፥ እጅግም አፍራለሁ።
7ከአባቶቻችን ዘመን ጀምሮ እስካሁን ድረስ በታላቅ በደል ውስጥ አለን። ዛሬ እንደሆነብን ሁሉ በበደላችን ምክንያት ነገሥታቶቻችንና ካህናቶቻችን በዚህ ዓለም መንግሥታት እጅ ለሰይፍ፥ ለምርኮ፥ ለመበዝበዝና ለእፍረት ፊት ተሰጡ።
8አሁንም ገና ለጥቂት ጊዜ የተረፍነው እኛ ጥቂቶቹ በሕይወት እንድንኖርና በዚህም ቅዱስ ሥፍራ የእግር መቆናጠጫ ሊሰጠን ከእግዚአብሔር ከአምላካችን ቸርነት መጥቶልናል። ዓይኖቻችንን ለማብራትና በባርነት እያለን ጥቂት እረፍት ሊሰጠን ይህ የአምላካችን ሥራ ነበር።
9ባሪያዎች ነንና፥ አምላካችን ግን የቃል ኪዳን ታማኝነቱን ለእኛም አስረዘመልን እንጂ አልረሳንም። ፍርስራሹን እንድናነሣና የአምላካችንን ቤት እንደገና መሥራት እንድንችል አዲስ ጉልበት ሊሰጠን በፋርስ ንጉሥ ፊት ይህንን አድርጓል። በኢየሩሳሌምና በይሁዳ የመከላከያ ቅጥር ሊሰጠን ይህንን አደረገ።
10አሁን ግን አምላካችን ሆይ፥ ከዚህ በኋላ ምን ማለት እንችላለን? ትዕዛዝህን እረስተናል፥
11የረሳነውም፤ "ልትወርሷት የምትገቡባት ይህቺ ምድር የረከሰች ምድር ናት። በምድሪቱ በሚኖሩት ሰዎች እርኩሰት ረክሳለች። ከአንደኛው ጫፍ እስከ ሌላኛው ጫፍ ድረስ በእርኩሰታቸው ሞልተዋታል።
12አሁንም፥ እንድትበረቱና የምድሪቱን ፍሬ እንድትበሉ፥ ለልጆቻችሁም ለዘላለም እንድታወርሷቸው ሴቶች ልጆቻችሁን ለወንዶች ልጆቻቸው አትስጡ፤ ለወንዶች ልጆቻችሁም ሴቶች ልጆቻቸውን አትውሰዱ፥ ሰላምና ደኅንነታቸው እንዲቀጥልም አትፈልጉ ብለህ ለአገልጋዮችህ ለነቢያት የሰጠኸውን ትዕዛዝ ነው።"
13ይሁን እንጂ በክፉ ሥራችንና በብዙ በደላችን ምክንያት ከደረሱብን ነገሮች በኋላ አንተ አምላካችን ለኃጢአታችን የሚገባውን ተውክልንና የተረፍነውን በሕይወት እንድንኖር ፈቀድክ።
14ታዲያ እንደገና ትዕዛዝህን መጣስና ከእነዚህ ከረከሱ ሕዝቦች ጋር በጋብቻ መደባለቅ ነበረብን? አንተስ አንድም የሚቀር ወይም የሚያመልጥ እስከማይኖር ድረስ ታጠፋን ዘንድ ልትቆጣን አይገባህምን?
15የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፥ አንተ ጻድቅ ነህ፥ እኛም ጥቂቶች ተርፈን በሕይወት አለን። እነሆ፥ ከበደላችን ጋር በፊትህ ነን፥ ከዚህ የተነሣ በፊትህ ለመቆም የሚችል ማንም የለም።"
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።