መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ዕዝራ 8

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1በንጉሡ አርጤክስስ የንግሥና ዘመን ከእኔ ጋር ከባቢሎን የወጡት የአባቶች ቤት አለቆች እነዚህ ናቸው፤
2ከፊንሐስ ተወላጆች ጌርሶን። ከኢታምር ተወላጆች ዳንኤል። ከዳዊት ተወላጆች ሐጡስ።
3ከሴኬንያ ተወላጆች፥ ከፋሮስ ተወላጆች ዘካርያስ። ከእርሱ ጋር የተመዘገቡት ወንዶች 150 ነበሩ።
4ከፋሐት ሞዓብ ተወላጆች የዘራእያ ልጅ ኤሊሆዔናይ። ከእርሱ ጋር የተመዘገቡት ሁለት መቶ ወንዶች ነበሩ።
5ከሴኬንያ ተወላጆች የየሕዚኤል ልጅ። ከእርሱ ጋር የተመዘገቡት ሦስት መቶ ወንዶች ነበሩ።
6ከዓዲን ተወላጆች የዮናታን ልጅ ዔቤድ። ከእርሱ ጋር የተመዘገቡት ሃምሳ ወንዶች ነበሩ።
7ከኤላም ተወላጆች የጎቶልያ ልጅ የሻያ። ከእርሱ ጋር የተመዘገቡት ሰባ ወንዶች ነበሩ።
8ከሰፋጥያስ ተወላጆች የሚካኤል ልጅ ዝባድያ። ከእርሱ ጋር የተመዘገቡት ሰማንያ ወንዶች ነበሩ።
9ከኢዮአብ ተወላጆች የይሒኤል ልጅ አብድዩ። ክእርሱ ጋር የተመዘገቡት218 ወንዶች ነበሩ።
10ከሰሎሚት ተወላጆች የዮሲፍያ ልጅ። ከእርሱ ጋር የተመዘገቡት 160 ወንዶች ነበሩ።
11ከቤባይ ተወላጆች የቤባይ ልጅ ዘካርያስ። ከእርሱ ጋር የተመዘገቡት ሃያ ስምንት ወንዶች ነበሩ።
12ከዓዝጋድ ተወላጆች የሃቃጣን ልጅ ዮሐናን። ከእርሱ ጋር የተመዘገቡት 110 ወንዶች ነበሩ።
13የአዶኒቃም ተወላጆች ዘግይተው መጡ። ስማቸው እንደሚከተለው ነው፤ ኤሊፋላት፥ ይዑኤል፥ ሸማያ። ከእነርሱ ጋር ስልሳ ወንዶች መጡ።
14ከበጉዋይ ተወላጆች ዑታይና ዘቡድ። ከእነርሱ ጋር የተመዘገቡት ሰባ ወንዶች ነበሩ።
15ዕዝራም አለ፥ "መንገደኞቹን ወደ አኅዋ በሚወርደው ወንዝ አጠገብ ሰበሰብኋቸው፥ በዚያም ሦስት ቀን ቆየን። ሕዝቡንና ካህናቱን ተመለከትኩ፥ ከሌዊ ተወላጆች ግን በዚያ አንድም አላገኘሁኝም።
16እኔም አለቆች ወደነበሩት ወደ አልዓዛር፥ አርኤል፥ ሸማያ፥ ኤልናታን፥ ያሪብ፥ ኤልናታን፥ ናታን፥ ዘካርያስ፥ ሜሱላምና አስተማሪዎች ወደነበሩት ዮያሪብና ኤልናታን መልዕክት ላክሁ።
17በመቀጠልም በካሲፍያ አለቃ ወደ ሆነው ወደ አዶ ላክኋቸው። ለአዶ፥ ለወንድሞቹና በካሲፍያ ለሚኖሩ የቤተ መቅደስ አገልጋዮች ምን ማለት እንዳለባቸው አስታወቅኋቸው፤ ይኸውም ለእግዚአብሔር ቤት አገልጋዮችን እንዲልኩልን ነበር።
18ስለዚህ በመልካሚቱ በእግዚአብሔር እጅ ምክንያት ሰራብያ ተብሎ የሚጠራውን አስተዋይ ሰው ላኩልን። እርሱም ከእስራኤል ልጅ፥ ከሌዊ ልጅ፥ ከሞሖሊ ተወላጆች አንዱ ነበር። እርሱም ከአሥራ ስምንት ወንዶች ልጆቹና ወንድሞቹ ጋር መጣ።
19ሐሸብያም ከእርሱ ጋር መጣ። ደግሞም ከሜራሪ ወንዶች ልጆች አንዱ የሆነው የሻያን ከወንድሞቹና ከወንዶች ልጆቹ ጋር በድምሩ ሃያ ወንዶች ነበሩ።
20በቤተ መቅደስ ውስጥ እንዲያገለግሉ ከተመደቡት ውስጥ ዳዊትና ሹማምንቱ ሌዋውያኑን ለማገልገል የሰጡት 220 ነበሩ፥ እያንዳንዳቸው በየስማቸው ተመደቡ።
21ራሳችንን በእግዚአብሔር ፊት ለማዋረድ፥ ለእኛ፥ ለታናናሽ ልጆቻችንና ለንብረታችን ሁሉ መንገዳችንን እንዲያቃናልን በአኅዋ ወንዝ አጠገብ ጾም አወጅኩ።
22ንጉሡን፥ 'የአምላካችን እጅ ለመልካም በሚፈልጉት ሁሉ ላይ ናት፥ ቁጣውና ኃይሉ ግን እርሱን በሚተዉት ሁሉ ላይ ነው' ብለን ስለነበር በመንገድ ላይ ከጠላቶቻችን የሚጠብቁንን ሠራዊት ወይም ፈረሰኞችን እንዲሰጠን ንጉሡን ለመጠየቅ አፈርኩኝ።
23ስለዚህ በእግዚአብሔ ፊት ጾምንና ጸለይን፥ ስለዚህም ጉዳይ ለመንነው።
24ከዚያም ከካህናቱ ዋና ዋናዎቹን ሰራብያን፥ ሐሸቢያንና አሥር ወንድሞቻቸውን፥ አሥራ ሁለት ሰዎች መረጥኩ።
25ንጉሡ፥ አማካሪዎቹ፥ አለቆቹና በዚያ የነበሩ እስራኤል ሁሉ ለእግዚአብሔር ቤት በፈቃዳቸው ያቀረቡትን ብር፥ ወርቅ፥ ቁሳቁስና መባ መዝኜ ሰጠዃቸው።
26ስለዚህ 650 መክሊት ብር፥ አንድ መቶ መክሊት የብር ዕቃዎች፥ አንድ መቶ መክሊት ወርቅ፥ አንድ ሺህ ዳሪክ የሚያወጡ
27ሃያ ጎድጓዳ የወርቅ ሳሕኖች፥ የወርቅ ያህል የከበሩ ሁለት አብረቅራቂ የነሐስ ዕቃዎች መዝኜ በእጃቸው ሰጠኋቸው።
28ከዚያም እንዲህ አልኳቸው፥ 'እናንተና እነዚህ ዕቃዎች ለእግዚአብሔር ተቀድሳችኋል። ይህ ብርና ወርቅ ለአባቶቻችሁ አምላክ ለእግዚአብሔር በፈቃደኝነት የቀረበ መባ ነው።
29በካህናቱ ኃላፊዎች፥ በሌዋውያኑና በእስራኤል የነገድ አለቆች ፊት በኢየሩሳሌም በእግዚአብሔር ቤት ክፍሎች ውስጥ እስክትመዝኑት ድረስ በጥንቃቄ ጠብቁት።
30ካህናቱና ሌዋውያኑ የተመዘነውን ብር፥ ወርቅና ቁሳቁስ ወደ ኢየሩሳሌም ወደ አምላካችን ቤት ለመውሰድ ተረከቡት።
31በመጀመሪያው ወር በአሥራ ሁለተኛው ቀን ወደ ኢየሩሳሌም ለመሄድ ከአኅዋ ወንዝ አጠገብ ተነሣን። የአምላካችን እጅ በእኛ ላይ ነበረች፤ እርሱም ከጠላቶቻችን እጅና በመንገድ ላይ አድፍጠው ሊያጠቁን ከፈለጉት አዳነን።
32ወደ ኢየሩሳሌም ደርስንና ሦስት ቀን በዚያ ቆየን።
33ከዚያም በአራተኛው ቀን ብሩ፥ ወርቁና ቁሳቁሱ በአምላካችን ቤት ውስጥ በካህኑ በኦርዮ ልጅ በሜሪሞት እጅ ተመዝነው ተሰጡ። የፊንሐስ ልጅ አልዓዛር፥ ሌዋውያኑ የኢያሱ ልጅ ዮዛባትና የቢንዊ ልጅ ኖዓድያ ከእርሱ ጋር ነበሩ።
34የሁሉም ነገር ቁጥሩና ክብደቱ ታወቀ፤ በዚያኑ ጊዜም ጠቅላላ የክብደቱ መጠን ተጻፈ።
35ተማርከው የነበሩት፥ ከምርኮም የተመለሱት ለእስራኤል አምላክ የሚቃጠል መሥዋዕት አቀረቡ፤ ለእስራኤል ሁሉ አሥራ ሁለት ወይፈኖችን፥ ዘጠና ስድስት አውራ በጎችን፥ ሰባ ሰባት ጠቦቶችንና ለኃጢአት መሥዋዕት አሥራ ሁለት አውራ ፍየሎችን አቀረቡ። ሁሉም ለእግዚአብሔር የሚቃጠል መሥዋዕት ነበር።
36ከዚያም የንጉሡን ትዕዛዝ በወንዙ ማዶ ላሉት የንጉሡ ሹማምንትና አስተዳዳሪዎች ሰጧቸው፥ እነርሱም ሕዝቡንና የእግዚአብሔርን ቤት አገዙ።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።