1ስለዚህ ንጉሥ ዳርዮስ በባቢሎን ባሉት ቤተ መዛግብት ምርመራ እንዲደረግ አዘዘ።
2በሜዶን አገር ቅጥር ባላት ኤክባታና ከተማ አንድ የመጽሐፍ ጥቅልል ተገኝ፥ ጽሑፉም የሚለው እንዲህ ነበር፤
3"ንጉሡ ቂሮስ በነገሠ በመጀመሪያው ዓምት በኢየሩሳሌም ስላለው የእግዚአብሔር ቤት ቂሮስ እንዲህ የሚል ትዕዛዝ ሰጥቷል፤ የመሥዋዕቱ ቤት ይሠራ። ቅጥሩም ስልሳ ክንድ ከፍታ፥ ስልሳ ክንድ ወርድ ተደርጎ
4በሦስት ዙር ትላልቅ ድንጋዮችና በአንድ ዙር አዲስ እንጨት ይሠራ። ወጪውም በንጉሡ ቤት ይሸፈን።
5ደግሞም ናቡከደነፆር ከኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ወደ ባቢሎን ቤተ መቅደስ ያመጣቸውን የእግዚአብሔር ቤት የወርቅና የብር ዕቃዎች መልሱላቸው። በኢየሩሳሌም ወዳለው ቤተ መቅደስ ላኩና በዚያ በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ ይቀመጥ።
6አሁንም በወንዙ ማዶ ያላችሁት ተንትናይ፥ ሰተር ቡዝናይና ተባባሪዎቻችሁ ከእነርሱ ራቁ።
7ይህንን የእግዚአብሔር ቤት ሥራ ለእነርሱ ብቻ ተዉሏቸው። ይህንን የእግዚአብሔር ቤት አስተዳዳሪውና የአይሁድ አለቆች በዚያው ሥፍራ ላይ ይሠሩታል።
8ለእነዚህ የእግዚአብሔርን ቤት ለሚሠሩት ይህንን እንድታደርጉላቸው አዝዣለሁ፤ ሥራቸውን እንዳያስተጓጉሉ በወንዙ ማዶ ካሉት ለንጉሡ ከሚሰበሰበው ገቢ ላይ ወጪ እየተደረገ ይከፈላቸው።
9ለሰማይ አምላክ ለሚቃጠለው መሥዋዕት የሚፈለገው ሁሉ ወይፈኖችን፥ አውራ በጎችን ወይም ጠቦቶችን እንዲሁም በኢየሩሳሌም ባሉት ካህናት ትዕዛዝ መሠረት ስንዴ፥ ጨው፥ ወይን ወይም ዘይት እነዚህን ነገሮች ሳታቋርጡ በየዕለቱ ስጧቸው።
10ለሰማይ አምላክ መሥዋዕት እንዲያቀርቡና ለእኔ ለንጉሡና ለልጆቼም እንዲጸልዩ ይህንን አድርጉላቸው።
11ይህንን ትዕዛዜን የሚተላለፍ ማንም ቢሆን የቤቱ ምሶሶ ተነቅሎ እርሱ እንዲሰቀልበት አዝዣለሁ። በዚህ ምክንያት መኖሪያ ቤቱ የቆሻሻ መጣያ ይሁን።
12በኢየሩሳሌም የሚገኘውን የእግዚአብሔር ቤት ለማፍረስ የሚነሳውን ንጉሥና ሕዝብ በዚያ የሚኖረው አምላክ ያጥፋው። እኔ ዳርዮስ ይህንን አዝዣለሁ። ሙሉ በሙሉ ይፈጸም።
13ከዚያም ተንትናይ፥ ሰተር ቡዝናይና ተባባሪዎቻቸው ንጉሡ ዳርዮስ ያዘዘውን ሁሉ ፈጸሙ።
14ስለዚህ የአይሁድ አለቆች ሐጌና ዘካርያስ በትንቢት በነገሯቸው መሠረት ሥራውን ሠሩ። እነርሱም በእስራኤል አምላክ በእግዚአብሔር እና በፋርስ ነገሥታት በቂሮስ፥ በዳርዮስና በአርጤክስስ ትዕዛዝ መሠረት ሠሩ።
15ቤቱም ንጉሡ ዳርዮስ በነገሠ በስድስተኛው ዓመት አዳር በሚባለው ወር በሦስተኛው ቀን ተጠናቀቀ።
16የእስራኤል ሕዝብ፥ ካህናቱ፥ ሌዋውያኑና የቀሩት ምርኮኞች የዚህን የእግዚአብሔር ቤት ምረቃ በደስታ አከበሩ።
17እነርሱም ለእግዚአብሔር ቤት ምረቃ አንድ መቶ ወይፈኖችን፥ ሁለት መቶ አውራ በጎችንና አራት መቶ ጠቦቶችን አቀረቡ። ለእያንዳንዱ የእስራኤል ነገድ አንድ፥ ለእስራኤል ሁሉ የኃጢአት መሥዋዕት አሥራ ሁለት ወንድ ፍየሎች ቀረቡ።
18ደግምም ካህናቱና ሌዋውያኑ በሙሴ ሕግ እንደተጻፈው በኢየሩሳሌም ያለውን የእግዚአብሔር ቤት አገልግሎት በየተራቸው እንዲፈጽሙ ተመደቡ።
19እንዲሁም በምርኮ የነበሩት በመጀመሪያው ወር በአሥራ አራተኛው ቀን የፋሲካን በዓል አከበሩ።
20ካህናቱና ሌዋውያኑ ሁሉ ራሳቸውን አነጹና እራሳቸውን ጨምሮ በምርኮ ለነበሩት ሁሉ የፋሲካውን መሥዋዕቶች አረዱ።
21የፋሲካውን ሥጋ ከበሉት እስራኤላውያን ውስጥ አንዳንዶቹ ከምርኮ የተመለሱና ራሳቸውን ከሚኖሩበት ምድር ሰዎች እርኩሰት በመለየት የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን የሚፈልጉ ነበሩ።
22እግዚአብሔር ደስታን ስለ ሰጣቸውና በቤቱ፥ በእስራኤል አምላክ ቤት ሥራ ላይ እጆቻቸውን እንዲያበረቱ የአሶር ነገሥታትን ልብ መልሶላቸው ስለነበረ የቂጣውን በዓል ለሰባት ቀናት በደስታ አከበሩ።