መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ዕዝራ 4

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1አንዳንድ የይሁዳና የብንያም ጠላቶች ከምርኮ የተመለሱት ሰዎች ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ በመሥራት ላይ መሆናቸውን ሰሙ።
2እነርሱም ወደ ዘሩባቤልና ወደ አባቶቻቸው የነገድ አለቆች መጡ። እነርሱም፥ "እንደናንተው አምላካችሁን እንፈልገዋለንና የአሶር ንጉሥ አስራዶን ወደዚህ ስፍራ ካመጣን ጊዜ ጀምሮም ስንሠዋለት ነበርና አብረናችሁ እንሥራ"አሏቸው።
3ዘሩባቤል፥ ኢያሱና የአባቶቻቸው የነገድ አለቆች ግን፥ "የአምላካችንን ቤት መሥራት የሚገባን እኛ እንጂ እናንተ አይደላችሁም፥ የፋርስ ንጉሥ እንዳዘዘው ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር የምንሠራው እኛ ነን" አሏቸው።
4ስለዚህ የምድሩ ሕዝብ የይሁዳን ሰዎች እጅ አደከሙ፤ እንዳይሠሩም የይሁዳን ሰዎች አስፈራሩ።
5ደግሞም ዕቅዳቸውን ለማጨናገፍ ለአማካሪዎች ጉቦ ሰጡ። ይህንንም በቂሮስ ዘመን ሁሉና እስከ ፋርስ ንጉሥ ዳርዮስ እስከ ነገሠበት ጊዜ ድረስ አደረጉ።
6ከዚያም አርጤክስስ መንገሥ በጀመረበት ዘመን በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ነዋሪዎች ላይ ክስ ጻፉባቸው።
7በአርጤክስስ ዘመን ቢሽላም፥ ሚትሪዳጡ፥ ጣብኤልና ተባባሪዎቻቸው ነበር ለአርጤክስስ የጻፉት። ደብዳቤውም በአረማይስጥ ቋንቋ ተጽፎ የተተረጎመ ነበር።
8አዛዡ ሬሁምና ጸሐፊው ሲምሳይ ስለ ኢየሩሳሌም ለአርጤክስስ እንዲህ ብለው ጻፉ፤
9ከዚያም ዳኞች የነበሩት ሬሁም፥ ሲምሳይና ተባባሪዎቻቸው እንዲሁም በአርክ፥ በባቢሎንና በኤላሙ ሱሳ የነበሩ ሌሎች የመንግሥት ኃላፊዎች ደብዳቤውን ጻፉ -
10እነርሱንም ታላቁና ኃያሉ አሹርባኒጳል በወንዙ ማዶ ባለው አውራጃ ከቀሩት ከሌሎቹ ጋር በሰማርያ እንዲሰፍሩ ያስገደዷቸው ሰዎች ደገፏቸው።
11ለአርጤክስስ የላኩት የደብዳቤው ግልባጭ ይህ ነው፤ "ይህንን የሚጽፉት ከወንዙ ማዶ ያሉት ሰዎች፥ አገልጋዮችህ ናቸው፤
12ካንተ ዘንድ የወጡት አይሁድ እኛን በመቃወም አመጸኛይቱን ከተማ በኢየሩሳሌም ውስጥ ለመሥራት መጀመራቸውን ንጉሡ ይወቅ። እነርሱም ቅጥሮቹን ጨርሰው መሠረቶቹን አድሰዋል።
13ይህቺ ከተማ ከተሠራችና ቅጥሯም ከተጠናቀቀ ምንም ዓይነት እጅ መንሻና ቀረጥ እንደማይሰጡና ንጉሡን እንደሚጎዱት ንጉሡ ይወቅ።
14በርግጥ የቤተመንግሥቱን ጨው ስለ በላን በንጉሡ ላይ ማናቸውም ዓይነት ውርደት ሲደርስበት ማየት አይገባንም።
15ለዚህም ነው የአባትህን መዛግብት እንድትመረምርና ነገሥታትንና አውራጃዎችን የምትጎዳ አመጸኛ ከተማ መሆኗን እንድታረጋግጥ ለንጉሡ ያስታወቅነው። በነገሥታትና በአውራጃዎች ላይ ብዙ ችግር የፈጠረች ነች። ከብዙ ዘመን ጀምሮም የአመጽ ማዕከል ነች። ከተማይቱ ተደምስሳ የነበረችውም በዚሁ ምክንያት ነበር።
16ይህቺ ከተማ ከቅጥሯ ጋር ከተሠራች ከዚህ በኋላ ከታላቁ ከኤፍራጥስ ወንዝ ማዶ ምንም የሚቀርልህ ነገር እንደማይኖር ለንጉሡ እናስታውቃለን"።
17ስለዚህ ንጉሡ ለሬሁም፥ ሲምሳይ፥ በሰማሪያ ላሉ ተባባሪዎቻቸውና ከወንዙ ማዶ ላሉት ለቀሩት ምላሽ ላከ፤ "ሰላም ይሁንላችሁ።
18የላካችሁልኝ ደብዳቤ ተተርጉሞ ተነቦልኛል።
19በመሆኑም ምርመራ እንዲደረግ አዘዝኩኝና ባለፉት ዘመናት በነገሥታት ላይ ስታምጽ የኖረች አመጸኛ መሆኗ ታውቋል።
20በኢየሩሳሌም ላይ ኃያላን ነገሥታት ገዝተዋል፥ ከወንዙ ማዶ ባለው ሁሉ ላይም ሥልጣን ነበራቸው። እጅ መንሻና ቀረጥም ይሰጣቸው ነበር።
21አሁንም እነዚህ ሰዎች ሥራውን እንዲያቆሙና እኔ እስከማዝዝ ድረስ ይህቺን ከተማ እንዳይሠሩ ትዕዛዝ ስጡ።
22ይህንን ማድረጉን ቸል እንዳትሉ ተጠንቀቁ። ነገሥታቱን የሚጎዳው ጥፋት ለምን ይጨምራል?"
23የንጉሡ የአርጤክስስ ትዕዛዝ በሬሁም፥ በሲምሳይና በተባባሪዎቻቸው ፊት በተነበበ ጊዜ በፍጥነት ወደ ኢየሩሳሌም ሄዱና አይሁድ ሥራውን እንዲያቆሙ አስገደዷቸው።
24ስለዚህ በኢየሩሳሌም ያለው የእግዚአብሔር ቤት ሥራ የፋርስ ንጉሥ ዳርዮስ እስከ ነገሠበት እስከ ሁለተኛው ዓመት ድረስ ተቋረጠ።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።