1የእስራኤል ሕዝብ በኢየሩሳሌም እንደ አንድ ሰው ሆነው በሚሰበሰቡበት ጊዜ ወደ ከተሞቻቸው ከመጡ ሰባት ወር ሆኗቸው ነበር።
2የኢዮሴዴቅ ልጅ ኢያሱና ካህናት ወንድሞቹ፥ የሰላትያል ልጅ ዘሩባቤልና ወንድሞቹ ተነሥተው በእግዚአብሔር ሰው በሙሴ ሕግ እንደታዘዘው የሚቃጠለው መሥዋዕት የሚቀርብበትን የእስራኤልን አምላክ መሠዊያ ሠሩ።
3ከዚያም በምድሪቱ ከሚኖሩ ሰዎች የተነሣ ሥጋት ስለነበረባቸው መሠዊያውን በሥፍራው አቆሙት። የሚቃጠለውንም መሥዋዕት በጠዋትና በማታ ለእግዚአብሔር አቀረቡ።
4ደግሞም የዳሱን በዓል እንደተጻፈው አከበሩ፥ ለየዕለቱ እንደታዘዘው የሚቃጠለውን መሥዋዕት ዕለት በዕለት አቀረቡ።
5እንዲሁም በበጎ ፈቃድ ከሚቀርበው መባ ሁሉ ጋር ለዕለት፥ ለወርና ለተደነገጉት የእግዚአብሔር በዓላት ሁሉ መሥዋዕት ይቀርብ ነበር።
6የቤተ መቅደሱ መሠረት ባይጣልም በሰባተኛው ወር የመጀመሪያ ቀን የሚቃጠለውን መሥዋዕት ለእግዚአብሔር ማቅረብ ጀመሩ።
7እንዲሁም ለድንጋይ ጠራቢዎችና ለአናጺዎች ብር ሰጧቸው፤ የፋርስ ንጉሥ ቂሮስ እንዳዘዘላቸው የዝግባ ዛፎችን ከሊባኖስ በባህር ወደ ኢዮጴ እንዲልኩላቸው ለጢሮስና ለሲዶና ሰዎች ምግብ፥ መጠጥና ዘይት ሰጧቸው።
8ከዚያም ዘሩባቤል፥ የኢዮሴዴቅ ልጅ ኢያሱ፥ የቀሩት ካህናቱ፥ ሌዋውያኑና ከምርኮ ወደ ኢየሩሳሌም የተመለሱት በኢየሩሳሌም ወዳለው ወደ እግዚአብሔር ቤት በመጡ በሁለተኛው ዓመት በሁለተኛው ወር ሥራውን ጀመሩ። ሃያ ዓመትና ከዚያም በላይ የሆኑትን ሌዋውያን የእግዚአብሔርን ቤት ሥራ እንዲቆጣጠሩ መደቧቸው።
9ኢያሱም ወንዶች ልጆቹንና ወንድሞቹን፥ ቀድምኤልና ወንዶች ልጆቹን፥ እንዲሁም የይሁዳን ተወላጆች የእግዚአብሔርን ቤት የሚሠሩትን ሰዎች ላእንዲቆጣጠሩ ደለደላቸው። ከእነርሱም ጋር የኤንሐዳድ ተወላጆች፥ ደግሞም ተወላጆቻቸውና ባልደረቦቻቸው ሌዋውያን ነበሩ።
10ግንበኞቹ የእግዚአብሔርን ቤት መሠረት ጣሉ። ይህ ካህናቱ ልብሰ ተክህኗቸውን ለብሰውና መለከቶችን ይዘው እንዲቆሙና ሌዋውያኑ የአሳፍ ወንዶች ልጆች በእስራኤል ንጉሥ በዳዊት እጅ እንደታዘዘው በጸናጽል እግዚአብሔርን ለማመስገን አስቻላቸው።
11እነርሱም፥ "ቸር ነው! ለእስራኤልም የቃል ኪዳን ታማኝነቱ ለዘላለም ነው" እያሉ በምስጋናና በውዳሴ ለእግዚአብሔር ዘመሩ። የቤተ መቅደሱ መሠረት ስለተጣለ ሕዝቡ ሁሉ እግዚአብሔርን እያመሰገኑ በታላቅ የደስታ ድምጽ እልል አሉ።
12ነገር ግን በርካታ ካህናት፥ ሌዋውያን፥ የአባቶች አለቆችና የመጀመሪያውን ቤት ያዩ አዛውንቶች የዚህኛው ቤት መሠረት ሲጣል ባዩ ጊዜ በታላቅ ድምጽ አለቀሱ። ብዙዎቹ ግን የመደነቅና የደስታ ጩኸት ይጮሁ ነበር።
13ሰዎች የደስታውንና የሐሴቱን ድምጽ ክሕዝቡ የልቅሶ ድምጽ ለመለየት አልቻሉም፥ ሕዝቡ በታላቅ ደስታ ይጮኹ ስለነበር ድምጻቸው ከሩቅ ተሰማ።