መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ሕዝቅኤል 8

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1በስድስተኛውም ዓመት በስድስተኛው ወር ከወሩም በአምስተኛው ቀን በቤቴ ተቀምጬ ሳለሁ የይሁዳም ሽማግሌዎች በፊቴ ተቀምጠው ሳሉ፥ በዚያ የጌታ የእግዚአብሔር እጅ እንደገና በእኔ ላይ ወደቀች።
2እኔም አየሁ፥ እነሆም፥ የሰው አምሳያ ነበረ ከወገቡም በታች እሳት ይመስል ነበረ፥ ከወገቡም በላይ የቀለጠ ብረት የሚመስል የሚያብለጨልጭ ነበር።
3ከዚያም እጅ የሚመስል ነገር ዘረጋ በራስ ጠጕሬም ያዘኝ፤ መንፈስም በምድርና በሰማይ መካከል አነሣኝ፥ በእግዚአብሔርም ራእይ ወደ ኢየሩሳሌም ወደ ሰሜን ወደሚመለከተው ወደ ውስጠኛው አደባባይ በር መግቢያ አመጣኝ በዚያም ቅንዓት የሚያነሣሣ የቅንዓት ጣዖት ተተክሎ ነበር።
4እነሆም፥ በቈላው እንዳየሁት ራእይ አይነት የእስራኤል አምላክ ክብር በዚያ ነበረ።
5እርሱም፦ "የሰው ልጅ ሆይ፥ ዓይንህን ወደ ሰሜን አንሣ አለኝ።" ዓይኔንም ወደ ሰሜን መንገድ አነሣሁ እነሆም፥ በመሠዊያው በር በሰሜን በኩል መግቢያው ላይ የቅንዓት ጣዖት ነበረ።
6የእግዚአብሔርም መንፈስ፦ "የሰው ልጅ ሆይ፥ አየህ የሚያደርጉትን? ይህ ከመቅደሴ ያርቁኝ ዘንድ የእስራኤል ቤት በዚህ የሚያደርጉት ታላቁን ርኵሰት ነው! ግን ዞረህ ስታይ ከዚህ የበለጠ ታላቅ ርኵሰት ታያለህ አለኝ!"
7ወደ አደባባዩም መግቢያ አመጣኝ ፥ በግንቡ ውስጥ ቀዳዳ እንዳለ አየሁ።
8እርሱም፦ "የሰው ልጅ ሆይ፥ ግንቡን ንደለው አለኝ ግንቡንም በነደልሁት ጊዜ መግቢያ በር አገኘሁ።
9እርሱም፦ "ግባና የሚያደርጉትን የከፋ ርኵሰት እይ አለኝ።
10እኔም ገባሁና እነሆ፥ በግንቡ ዙሪያ ላይ የሚሳብና አስቀያሚ አውሬ ምስል አየሁ! በግንቡም ዙሪያ የእስራኤል ቤት ጣዖታት ሁሉ ተስለው አየሁ።
11ሰባ እስራኤል ቤት ሽማግሌዎች በዚያ ቆመው ነበር፥ በመካከላቸውም የሳፋን ልጅ ያእዛንያ ቆሞ ነበር፥ በምስሎቹም ፊት ቆመው ነበር ። እያንዳንዱ ሰው በእጁ ጥናውን ይዞ ነበር፥ የዕጣኑም ጢስ ሽቱ ይወጣ ነበር።
12እርሱም፦ "የሰው ልጅ ሆይ፥ የእስራኤል ቤት ሽማግሌዎች በጨለማ የሚያደርጉትን አየህ? 'እግዚአብሔር አያየንም እግዚአብሔር ምድሪቱን ትቶአታል' ብለው ሁሉም ሰው ይህን የሚያድርገው በየራሱ ስውር ቦታ ከጣዖቱ ጋር ሆኖ ነው።
13እርሱም፦ "ደግሞ ወደኋላ ዙርና እያደረጉ ያለውን ከዚህ የበለጠውን ሌላ ታላቅ ርኵሰት እይ" አለኝ።
14ከዚያም ወደ በሰሜን አቅወጣጫ ወዳለው ወደ እግዚአብሔር ቤት በር መግቢያ አመጣኝ፣ እነሆም! ሴቶች ለተሙዝ እያለቀሱ በዚያ ተቀምጠው ነበር።
15እርሱም፦ "የሰው ልጅ ሆይ፥ ይህን ታያለህ? ደግሞ ተመልሰህ ከዚህ የበለጠ ርኵሰት ታያለህ አለኝ።
16ደግሞም ወደ እግዚአብሔር ቤት ወደ ውስጠኛው አደባባይ አመጣኝ፥ እነሆም፥ በእግዚአብሔር መቅደስ መግቢያ በወለሉና በመሠዊያው መካከል ሀያ አምስት የሚያህሉ ሰዎች ጀርባቸው ወደ እግዚአብሔር መቅደስ ፊታቸውም ወደ ምሥራቅ ሆኖ ሸሚሽ ለተሰኘው ጣዖት ይሰግዱ ነበር።
17እርሱም፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ ይህን ታያለህ? በዚህ የሚያደርጉት ይህ ርኵሰት ለይሁዳ ቤት እንድ ቀላል ነገር ነውን? ምድሪቱን በግፍ ሞልተዋታል ያስቈጡኝም ዘንድ ተመልሰዋል፥ ቅርንጫፎችንም ወደ አፍንጫዎቻቸው አቅርበዋል።
18ስለዚህ እኔ ደግሞ በመካከላቸው እንቀሳቀሳለሁ ዓይኔ አይራራም ፣አላዝንላቸውም። ወደ ጆሮዬም በታላቅ ድምፅ ቢጮኹ አልሰማቸውም አለኝ።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።