1በተማረክን በሀያ አምስተኛው ዓመት በዓመቱ መጀመሪያ ከወሩ በአሥረኛው ቀን፥ ከተማይቱ ከተመታች በኋላ በአሥራ አራተኛው ዓመት፥ በዚያው ቀን የእግዚአብሔር እጅ በእኔ ላይ ነበረ እርሱም ወደዚያ ወሰደኝ።
2በእግዚአብሔር ራእይ ወደ እስራኤል ምድር አመጣኝ እጅግም በረዘመ ተራራ ላይ አኖረኝ፥ በዚያም ላይ በደቡብ ወገን እንደ ከተማ ሆኖ የተሠራ ነገር ነበረ።
3ወደዚያም አመጣኝ፥ እነሆም፥ መልኩ እንደ ናስ መልክ የመሰለ አንድ ሰው በዚያ ነበረ፥ በእጁም የተልባ እግር ገመድና የመለኪያ ዘንግ ነበረ እርሱም በከተማይቱ በር አጠገብ ቆሞ ነበር።
4ሰውዬውም፥ "የሰው ልጅ ሆይ፥ ወደዚህ ያመጣሁህ ይህን ላሳይህ ስለሆን በዓይንህ እይ በጆሮህም ስማ በማሳይህም ሁሉ ላይ ልብ በል የምታየውንም ሁሉ ለእስራኤል ቤት ንገር አለኝ።
5እነሆም፥ በቤተመቅደሱ ዙሪያው ቅጥር ነበረ፥ በሰውዬውም እጅ ርዝመቱ ስድስት ክንድ የሆነ የመለኪያ ዘንግ ነበር። እያንዳንዱም ክንድ አንድ ክንድ ከስንዝር ነበረ። ሰውዬውም ቅጥሩን ለካ፤ የቅጥሩም ስፋት አንድ ዘንግ ቁመቱንም አንድ ዘንግ ነበረ።
6ወደ ምሥራቅ ወደሚመለከተውም በር ሄዶ በደረጃዎቹ ወጣ፥ የመድረኩንም ወለል ለካ፥ ወርዱን አንድ ዘንግ ነበር።
7የዘበኞቹም ጓዳ ሁሉ ርዝመቱ አንድ ዘንግ፥ ወርዱም አንድ ዘንግ ነበረ በዘበኞቹም ጓዳዎች መካከል አምስት ክንድ ርቀት ነበረ በበሩም ደጀ ሰላም በስተ ውስጥ በኩል የሚገኝ የበሩ የመድረክ ወለል አንድ ዘንግ ነበረ።
8የበሩን መተላለፊያ ደጅ ለካ ርዝመቱም አንድ ዘንግ ነበር።
9የበሩን መተላለፊያ ደጅ ለካ፥ ጥልቀቱ አንድ ዘንግ ነበረ። የግንቡንም አዕማድ ወርድ ሁለት ክንድ ነበረ። አድርጎ ለካ ።ይህም በቤተመቅደሱ ትይዩ የሚገኘው ድጅ መተላለፊያ ነበረ።
10በበሩ አጠገብ የሚገኙት የዘበኛ ጓዳዎች በበሩ በሁለቱም በኩል ሦስት ሦስት ነበሩ፥ የሁሉም መጠን እኩል ነበረ በሁሉም አቅጣጫ የሚለያቸው ግንብም እኩል መጠን ነበረው።
11ቀጥሎም ሰውዬው የበሩን መግቢያ ወርድ ለካ አሥር ክንድ ሆነ፤ የበሩንም መግቢያ ርዝመት ለካ አሥራ ሦስት ክንድ ሆነ።
12በእያንዳንዱ በዘበኛ ጓዳ ፊት ከፍታው አንድ ክንድ የሆነ መከለያ ነበረ። የዘበኛ ጓዳዎቹም በሁሉም አቅጣጫ ስድስት ክንድ ከፍታ ነበራቸው።
13ከአንዱም የዘበኛ ጓዳ ደርብ ጀምሮ እስከ ሌላው ደርብ ድረስ የበሩን ወርድ ሀያ አምስት ክንድ ለካ ይህም ከመጀምሪያው የዘበኞች ጓዳ መግቢያ እስከ ሌላኛው መግቢያ ድረስ ነው።
14ቀጥሎም በዘበኞች ጓዳ መካከል የሚያልፈውን ግንብ ለካ፤ ስድስት ክንድም ሆነ። እስከ መግቢያው መተላለፊያ ድረስ ለካ ።
15ከበሩም መግቢያ ፊት ጀምሮ እስከ ውስጠኛው የበሩ መተላለፊያ መጨረሻ ድረስ አምሳ ክንድ ነበረ።
16በዘበኛ ጓዳዎቹም በበሩ ውስጥ በዙሪያው በነበሩትም በግንቡ አዕማድ ትንንሽ መስኮቶች ነበሩዋቸው። በበሩም ደጅ መተላለፊያ እንደዚያው ነበር። ሁሉም መስኮቶች በውስጥ በኩል ነበሩ። በግንቡም አዕማድ ሁሉ ላይ የዘንባባ ዛፍ ተቀርጾባቸው ነበር።
17ቀጥሎም ሰውዬው ወደ ውጭውም አደባባይ አመጣኝ። እነሆም፥ በአደባባዩ ዙሪያ ክፍሎችና ወለል ነበሩ። በወለሉም ላይ ሠላሳ ክፍሎች ነበሩ።
18ወለሉም እስከ በሮቹ ይደርስ ነበር ስፋቱም እንደ በሮቹ ርዝመት መጠን ነበረ። ይህም ታችኛው ወለል ነበር።
19ከታችኛውም በር ፊት ጀምሮ እስከ ውስጠኛው በር ፊት ድረስ ያለውን ርቀት ለካ፤ በምስራቅ በኩል አንድ መቶ ክንድ በሰሜኑም በኩል ተመሳሳይ ነበረ።
20ቀጥሎም ከውጭው አደባባይ በሰሜን በኩል ያለውን በር ርዝመትና ስፋት ለካ።
21በበሩ በዚህና በዚያ የዘበኛ ጓዳዎቹም ነበሩ፥ በሩና መተላለፊያው ከዋናው በር ልኬታቸው እኩል ነበር- ርዝመቱ አምሳ ክንድ ወርዱም ሀያ አምስት ክንድ ነበረ።
22መስኮቶቹም ፥መተላለፊያዎቹና የዘንባባ ዛፎቹ ወደ ምሥራቅ እንደሚመለከተው በር ጋር ይዋሰኑ ነበር። ወደ እርሱና ወደ መተላለፊያዎቹ የሚያደርሱ ሰባት ደረጃዎች ነበሩ።
23በውስጠኛውም አደባባይ በሰሜኑና በምሥራቁ በኩል በሌላው በር አንጻር በር ነበረ፤ ሰውዬውም ከአንዱ በር እስከ በር ድረስ ለካ። ርቀቱም አንድ መቶ ክንድ ነበር።
24ቀጥሎም ሰውዬው ወደ ደቡቡ መግቢያ አመጣኝ፥ እነሆም፥ ግንቡና መተላለፊያዎቹ ከሌላኛው መውጪያው በር ጋር እኩል ልኬት ነበራቸው።
25በመግቢያውና በመተላለፊያዎቹ እንደዚያኛው በር አይነት ትንንሽ መስኮቶች ነበሩዋቸው። የድቡቡ በርና መተላልፊያው ርዝመቱ አምሳ ክንድ ወርዱም ሀያ አምስት ክንድ ነበረ።
26ወደ በሩና መተላለፊያዎቹ የሚያደርሱ ሰባት ደረጃዎች ነበሩ፥ በግንቡም አዕማድ ላይ በሁለቱም ወገን የዘንባባ ዛፍ ተቀርጾባቸው ነበር።
27በደቡብ በኩል ወደ ውስጠኛው አደባባይ የሚያስገባ መግቢያ ነበረ፥ ሰውዬውም ከዚህኛው በር እስከ ደቡቡ መግቢያ ድረስ ለካ፥ ርቀቱ መቶ ክንድ ነበረ።
28ቀጥሎም ሰውዬው ከሌላኛው በር እኩል ልኬት ባለው በደቡብ በር በኩል ወደ ውስጠኛው አደባባይ አገባኝ ።
29የዘበኛ ጓዳዎቹንና የግንቡን አዕማድና መተላለፊያዎቹ ከመጀመሪያዎቹ መግቢያዎች እኩል ነበሩ፤ በመተላለፊያዎቹ ዙሪያ መስኮቶች ነበሩ።ውስጠኛው መግቢያና መተላለፊያው ርዝመቱ አምሳ ክንድ ወርዱም ሀያ አምስት ክንድ ነበረ።
30በውስጠኛው ግንብ ዙሪያውም መተላለፊያዎች ነበሩ። ርዝመታቸውም ሀያ አምስት ክንድ ወርዳቸውም አምስት ክንድ ነበረ።
31መተላለፊያዎቹም ወደ ውጭው አደባባይ ይመለከቱ ነበር በግንቡም አዕማድ ላይ የዘንባባ ዛፍ ተቀርጾ ነበር ወደ እርሱም የሚያደርሱ ስምንት ደረጃዎች ነበሩ።
32ቀጥሎም ከሌሎቹ መግቢያዎች እኩል ልኬት ባለው በምስራቁ በር በኩል ወደ ውስጠኛው አደባባይ አገባኝ።
33የዘበኛ ጓዳዎቹንና የግንቡን አዕማድ መተላለፊያዎቹ ሌኬታቸው ከሌሎቹ መግቢያዎች እኩል ነበር በዙሪያም መስኮቶች ነበሩ። መግቢያውና መተላልፊያው ርዝመቱም አምሳ ክንድ ወርዱም ሀያ አምስት ክንድ ነበረ።
34መተላለፊያዎቹም በስተ ውጭ ወዳለው አደባባይ ይመለከቱ ነበር በግንቡም አዕማድ ላይ በዚህና በዚያ ወገን የዘንባባ ዛፍ ተቀርጾ ነበር ወደ እርሱም የሚያደርሱ ስምንት ደረጃዎች ነበሩት።
35በሰሜንም ወዳለው በር አመጣኝ፥ በሩንም ለካው፤ ልኬቱም ከሌሎቹ በሮች እኩል ነበር።
36የዘበኛ ጓዳዎቹንና የግንቡን አዕማድ መተላለፊያዎቹ ልኬታቸው ከሌሎቹ በሮች እኩል ነበር በዙሪያውም መስኮቶች ነበሩ። ርዝመቱም አምሳ ክንድ ወርዱም ሀያ አምስት ክንድ ነበረ።
37መተላለፊያውም ወደ ውጭው አደባባይ ይመለከቱ ነበር በግንቡም አዕማድ ላይ በዚህና በዚያ ወገን የዘንባባ ዛፍ ተቀርጾ ነበር ወደ እርሱም የሚያደርሱ ስምንት ደረጃዎች ነበሩት።
38በእያንዳኔዱ ውስጠኛ መግቢያ በር ያላቸው ክፍሎች ነበሩ። ይህም የሚቃጠለውን መሥዋዕት የሚያጥቡበትነበር።
39የሚቃጠለውንም መሥዋዕት የኃጢአቱንና የበደሉንም መሥዋዕት ያርዱባቸው ዘንድ፥ በበሩ መተላለፊያ በዚህ ወገን ሁለት ገበታዎች፥ በዚያም ወገን ሁለት ገበታዎች ነበሩ።
40በሰሜን በኩል ባለው በር በስተ ውጭው፥ በመወጣጫው ደረጃዎች አጠገብ፥ በአንድ ወገን ሁለት ገበታዎች ነበሩ፥ በሌላውም ወገን በበሩ መተላለፊያ በኩል ሁለት ገበታዎች ነበሩ።
41በበሩ በሁለቱም ወገን አራት ገበታዎች ነበሩ፤ በስምንቱም ገበታዎች እንስሳትን ይሰው ነበር።
42ለሚቃጠለውም መሥዋዕት ርዝመታቸው አነድ ክንድ ተኩል ወርዳቸውም አንድ ክንድ ተኩል ቁመታቸውም አንድ ክንድ የሆኑ ከተጠረበ ድንጋይ የተሠሩ አራት ገበታዎች ነበሩ። በእነርሱም ላይ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና ሌላ መሥዋዕቱን የሚያርዱበትን መሳሪያ ያኖሩባቸው ነበር።
43በዙሪያውም በመተላለፊያው አንድ ጋት የሚርዝም መስቀያዎችነበሩ፥ የመስዋዕቱም ሥጋ የሆነ ክፈፍ በገበታዎቹም ላይ ይቀመጡ ነበር።
44በውስጠኛው አደባባይ ከውስጠኛው መግቢያም አጠገብ የዘማሪያን ክፍሎች ነበሩ። ከክልሎቹ አንዱ በሰሜን በኩል ነበረ፥ ሌላውም በስተደቡብ ነበረ።
45ሰውዬውም፥ "ይህ ወደ ደቡብ የሚመለከት ቤት በመቅደሱ ውስጥ ለማገልገል ተረኛ ለሆኑለሚተጉ ካህናት ነው።
46ወደ ሰሜንም የሚመለከተው ቤት በመሠዊያው ዙሪያ ለሚያገለግሉ ካህናት ነው። እነዚህ ከሌዊ ልጆች መካከል ያገለግሉት ዘንድ ወደ እግዚአብሔር የሚቀርቡ የሳዶቅ ልጆች ናቸው" አለኝ።
47ቀጥሎም አደባባዩን ለካ፥ አራት ማዕዘን ሆኖ ርዝመቱን መቶ ክንድ ወርዱንም መቶ ክንድ ነበረ መሠዊያውም በቤቱ ፊት ነበረ።
48ከዚያም ሰውዬው ወደ ቤቱ መተላለፊያ አመጣኝ፥ የግንብ አዕማዱንም ለካ፤ ወርድ በዚህ ወገን አምስት ክንድ በዚያም ወገን አምስት ክንድ ነበረ። መግቢያው ራሱ ወርዱ አሥራ አራት ክንድ ነበረ፥ በበሩም በዚህ ወገንና በዚያ ወገን የነበሩት ግንቦች ስፋት ሦስት ሦስት ክንድ ነበር።
49የቤተ መቅደሱ መተላለፊያ ርዝመት ሀያ ክንድ ወርዱም አሥራ ሁለት ክንድ ነበረ። ወደ እርሱም የሚያደርሱ ደረጃዎች በሁለቱም አቅጣጫ የቆሙ አዕማድ ነበሩ።