1አንተም፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ በጎግ ላይ ትንቢትን ተናገር እንዲህም በል፥ 'ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ የሞሳሕና የቶቤል ዋነኛ አለቃ ጎግ ሆይ፥ እነሆ፥ እኔ በአንተ ላይ ነኝ
2እመልስሃለሁ፥ እነዳህማለሁ፥ ከሰሜንም ዳርቻ እጐትትሃለሁ፥ ወደ እስራኤልም ተራሮች አመጣሃለሁ።
3ከግራ እጅህም ቀስትህን አስጥልሃለሁ፥ ከቀኝ እጅህም ፍላጾችህን አስረግፍሃለሁ።
4የአንተና የጭፍሮች ሁሉ ከአንተም ጋር ያሉ ሠራዊትና ወታደሮች ሬሳ ይገኛል። ለሚናጠቁ ወፎች ሁሉና ለምድር አራዊትም መብል አድርጌ እሰጥሃለሁ።
5አንተ በምድር ፊት ላይ ትወድቃለህ እኔ ተናግሬአለሁና፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
6በማጎግም ላይ ሳይፈሩም በደሴቶች በሚቀመጡ ላይ እሳትን እሰድዳለሁ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።
7ቅዱሱም ስሜ በሕዝቤ በእስራኤል መካከል እንዲታወቅ አደርጋለሁ፥ ቅዱሱንም ስሜን ከእንግዲህ ወዲህ እንዲረክስ አልፈቅድም፤ አሕዛብም እግዚአብሔር፥ የእስራኤል ቅዱስ፥ እኔ እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።
8ያልሁት ቀን እነሆ፥ ይመጣል ይሆንማል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር ።
9በእስራኤልም ከተሞች የሚኖሩ ይወጣሉ፥ የጦር መሣሪያዎችን፥ አላባሽ ጋሻንና ጋሻን፥ ቀስትንና ፍላጻዎችን፥ ጎመድንና ጦርንም ያቃጥላሉ፥ ለሰባት ዓመት በእሳት ያቃጥሉአቸዋል።
10በጦር መሣሪያው እሳትን ያነድዳሉ እንጂ እንጨትን ከምድረ በዳ አይወስዱም ከዱርም አይቈርጡም የገፈፉአቸውንም ይገፍፋሉ የበዘበዙአቸውንም ይበዘብዛሉ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፦
11በዚያም ቀን በእስራኤል ዘንድ በባሕር ምሥራቅ የሚያልፉበትን ሸለቆ የመቃብርን ስፍራ ለጎግ እሰጣለሁ፥ የሚያልፉትንም ይከለክላል በዚያም ጎግንና ብዛቱን ሁሉ ይቀብራሉ የሸለቆውንም ስም ሐሞንጎግ ብለው ይጠሩታል።
12ምድሩንም ያጸዱ ዘንድ የእስራኤል ቤት ሰዎች ሰባት ወር ይቀብሩአቸዋል፥
13የምድሪቱም ሰዎች ሁሉ ይቀብሩአቸዋል፥ እኔ የምከብርበት የማይረሳ ቀን ይሆንላችኋል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፦
14ምድርንም ለማጽዳት በምድሩ ላይ ወድቀው የቀሩትን የሚቀብሩ፥ ዘወትር በምድሩ ላይ የሚዞሩትን ሰዎች ይመድባሉ ስራውንም ከሰባት ወርም በኋላ ይጀምራሉ።
15በምድሩ ላይ እንዲዞሩ የተመደቡት በሚያልፉብት ጊዜ የሰውን አጥንት ካዩ ፥ ቀባሪዎች መጥተው በሐሞን ጎግ ሸለቆ እስኪቀብሩት ድረስ ምልክት አድርገው ያልፋሉ።
16ስሟ ሐሞና የሚሰኝ ከተማ በዚያ ትገኛለች። በዚህ መንገድ ምድሪቱን ያጸዳሉ።
17አንተም፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ለወፎች ሁሉና ለምድር አራዊት ሁሉ እንዲህ በላቸው፥ 'ኑ፥ ተከማቹ፥ ሥጋንም ትበሉ ዘንድ ደምንም ትጠጡ ዘንድ በእስራኤል ተራሮች ላይ ወደማርድላችሁ ታላቅ መሥዋዕት፥ ከየስፍራው ሁሉ ተሰብሰቡ።
18የኃያላኑን ሥጋ ትበላላችሁ የምድርንም አለቆች፥ የአውራ በጎችንና የጠቦቶችን፥ የፍየሎችንና የወይፈኖችን፥ የባሳንን ፍሪዳዎች ሁሉ፥ ደም ትጠጣላችሁ።
19እኔም ከማርድላችሁ መሥዋዕት እስክትጠግቡ ድረስ ጮማ ትበላላችሁ እስክትሰክሩም ድረስ ደም ትጠጣላችሁ።
20በሰደቃዬም ከፈረሶችና ከፈረሰኞች፥ ከኃያላንና ከሰልፈኞች ሁሉ ትጠግባላችሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
21ክብሬንም በአሕዛብ መካከል አኖራለሁ አሕዛብም ሁሉ ያደርግሁትን ፍርዴን፥ በላያቸውም ያኖርኋትን እጄን ያያሉ።
22ከእንግዲህም ወዲያ የእስራኤል ቤት እኔ እግዚአብሔር አምላካቸው እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።
23አሕዛብም የእስራኤል ቤት እኔን ባቃለሉበት በኃጢአታቸው ምክንያት እንደ ተማረኩ ያውቃሉ፥ ስለ በደሉኝ እኔም ፊቴን ከእነርሱ ስለ ሸሸግሁ፥ በጠላቶቻቸው እጅ አሳልፌ ሰጠኋቸው፥ እነርሱም ሁሉ በሰይፍ ወደቁ።
24እንደ ርኵሰታቸውም እንደ መተላለፋቸውም መጠን አደረግሁባቸው ፊቴንም ከእነርሱ ሸሸግሁ።
25ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ አሁን የያዕቆብን ምርኮ እመልሳለሁ ለእስራኤልም ቤት ሁሉ እራራለሁ፥ ስለ ቅዱስ ስሜም እቀናለሁ።
26እፍረታቸውንና እኔን የካዱበትን ክህደት ይረሳሉ። ማንም ሳያስፈራቸው በምድራቸው ተዘልለው በተቀመጡ ጊዜ እነዚህን ነገሮች ሁሉ ይረሳሉ።
27ከአሕዛብም ዘንድ በመለስኋቸው ጊዜ ከጠላቶቻቸውም ምድር በሰበሰብኋቸው ጊዜ በብዙ አሕዛብም ፊት እቀደሳለሁ።
28እኔም ወደ አሕዛብ አስማርኬአቸዋለሁና፥ ወደ ገዛ ምድራቸውም ሰብስቤአቸዋለሁና እኔ እግዚአብሔር አምላካቸው እንደ ሆንሁ ያውቃሉ። ከእነርሱም አንድንም ሰው በአሕዛብ መካከል አልተውኩም።
29ፊቴንም ከእነርሱ ከእንግዲህ ወዲህ አልሸሽግም መንፈሴን በእስራኤል ቤት ላይ አፍስሻለሁና፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።