1የእግዚአብሔርም እጅ በላዬ ነበረ እግዚአብሔርም በመንፈሱ አወጣኝ አጥንቶችም በሞሉባት ሸለቆ መካከል አኖረኝ።
2ዙሪያውን በመካከላቸው እንዳልፍ አደረገኝ፥ እነሆ በሸለቆው ውስጥ እጅግ ብዙ ነበሩ፥ እነሆም፥ እጅግ ደርቀው ነበር።
3እርሱም፥ "የሰው ልጅ ሆይ፥ እነዚህ አጥንቶች እንደገና በሕይወት ሊኖሩ ይችላሉን?" አለኝ። እኔም። ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፥ ይህን የምታውቀው አንተ ብቻ ነህ!" አልሁ።
4እርሱም እንዲህ አለኝ፥ "በእነዚህ አጥንቶች ላይ ትንቢት ተናገር እንዲህም በላቸው፥ 'እናንተ የደረቃችሁ አጥንቶች ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ሰሙ።
5ጌታ እግዚአብሔር ለእነዚህ አጥንቶች እንዲህ ይላል። እነሆ፥ መንፈስን አገባባችኋለሁ በሕይወትም ትኖራላችሁ።
6ጅማትም እሰጣችኋለሁ ሥጋንም አወጣባችኋለሁ በእናንተም ላይ ቁርበትን እዘረጋለሁ ትንፋሽንም አገባባችኋለሁ በሕይወትም ትኖራላችሁ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።
7እንዳዘዘኝም ትንቢት ተናገርሁ ስናገርም ፥ እነሆ የሚያናውጥ ድምፅ ሆነ፥ አጥንቶችም አጥንት ከአጥንት ጋር ተቀራረቡ።
8እኔም አየሁ፥ እነሆም፥ ጅማት ነበረባቸው ሥጋም ወጣ ቁርበትም በላያቸው ተዘረጋ፥ ህይወት ግን አልነበራቸውም።
9እርሱም፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ ትንቢት ተናገር፥ ለነፋስ ትንቢት ተናገር፥ ለነፋስም 'ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦' መንፈስ ቅዱስ! ከአራቱ ነፋሳት ዘንድ ና፥ እነዚህም የተገደሉት በሕይወት ይኖሩ ዘንድ እፍ በልባቸው" በል አለኝ።
10እንዳዘዘኝም ትንቢት ተናገርሁ፥ የእግዚአብሔርም መንፈስ ገባባቸው ሕያዋንም ሆኑ! እጅግም ታላቅ ሠራዊት ሆነው በእግራቸው ቆሙ።
11እርሱም እንዲህ አለኝ፥ "የሰው ልጅ ሆይ፥ እነዚህ አጥንቶች የእስራኤል ቤት ሁሉ ናቸው። እነሆ! አጥንቶቻችን ደርቀዋል ተስፋችንም ጠፍቶአል ፈጽመንም ተቈርጠናል ብለዋል።
12ስለዚህ ትንቢት ተናገር እንዲህም በላቸው፥ 'ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ሕዝቤ ሆይ፥ እነሆ፥ መቃብራችሁን እከፍታለሁ ከመቃብራችሁም አወጣችኋለሁ፥ ወደ እስራኤልም ምድር እመልሳችኋለሁ!
13ሕዝቤ ሆይ፥ መቃብራችሁን በከፈትሁ ጊዜ ከመቃብራችሁም ባወጣኋችሁ ጊዜ፥ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።
14መንፈሴንም በውስጣችሁ አሳድራለሁ፥ እናንተም በሕይወት ትኖራላችሁ፥ እኔ እግዚአብሔር እንደሆንኩ ባወቃችሁ ጊዜ በገዛ ምድራችሁም እንድታርፉ አደርጋለሁ። እኔ እግዚአብሔር ተናግሬአለሁ አደርገውማለሁ ይላል እግዚአብሔር።
15የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፥
16"አንተ፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ አንድ በትር ውሰድና። 'ለይሁዳና ለባልንጀሮቹ ለእስራኤል ልጆች'ብለህ በላዩ ጻፍ። 'ሌላም በትር ውሰድና 'ለኤፍሬም በትር ለዮሴፍና ለባልንጀሮቹ ለእስራኤል ቤት ሁሉ' ብለህ በላዩ ጻፍ።
17ከዚያም በእጅህ ውስጥ አንድ እንዲሆኑ ሁልቱንም በትሮች በአንድ ላይ ያዛቸው።
18ሕዝብህም ፥ 'ይህ የምታደርገው ነገር ምን ማለት እንደሆነ አትነግረንምን? ብለው በተናገሩህ ጊዜ፥
19አንተ። 'ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ በኤፍሬም እጅ ያለውን የዮሴፍን በትር ባልንጀሮቹንም የእስራኤልን ነገዶች እወስዳለሁ፥ ከይሁዳ በትር ጋር አጋጥማቸዋለሁ አንድ በትርም አደርጋቸዋለሁ፥ በእጄም ውስጥ አንድ ይሆናሉ' በላቸው።
20የጻፍክባቸውንም በትሮች በዓይናቸው ፊት በእጅህ ያዛቸው።
21ከዚያም እንዲህ በላቸው፥ 'ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ የእስራኤልን ልጆች ከሄዱባቸው ከአሕዛብ መካከል የምወስድበት ጊዜ ደርሷል ከአካባቢው አገሮች ሁሉ እሰበስባቸዋለሁ ወደ ገዛ ምድራቸውም አመጣቸዋለሁ።
22በምድሪቱም ውስጥ በእስራኤል ተራሮች ላይ አንድ ሕዝብ አደርጋቸዋለሁ፥ አንድ ንጉሥም በሁላቸው ላይ ይነግሣል ከዚያ ወዲያ ሁለት ሕዝብ አይሆኑም፥ ከዚያ ወዲያም ሁለት መንግሥቶች ሆነው አይለዩም።
23ከዚያ ወዲያም በጣዖቶቻቸውና በርኵሰታቸው በመተላለፋቸውም ሁሉ አይረክሱም፥ ኃጢአትም ከሠሩባት ዓመፅ ሁሉ አድናቸዋለሁ አነጻቸውማለሁ ሕዝብም ይሆኑኛል እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ።
24ባሪያዬም ዳዊት በላያቸው ይነግሳል። ለሁሉም አንድ እረኛ ይሆንላቸዋል በፍርዴም ይሄዳሉ ትእዛዜንም ይጠብቃሉ ያደርጓትማል።
25አባቶቻችሁም በኖሩበት ለባሪያዬ ለያዕቆብ በሰጠኋት ምድር ይኖራሉ እነርሱና ልጆቻቸው የልጅ ልጆቻቸውም ለዘላለም ይኖሩባታል ባሪያዬም ዳዊት ለዘላለም አለቃ ይሆናቸዋል።
26ከእነርሱ ጋር የሰላምን ቃል ኪዳን አደርጋለሁ፥ ከእነርሱም ጋር የዘላለምም ቃል ኪዳን ይሆናል። እኔም አጸናቸዋለሁ አበዛቸውማለሁም መቅደሴንም ለዘላለም በመካከላቸው አኖራለሁ።
27ማደሪያዬም በእነርሱ ዘንድ ይሆናል፤ ይሆናል እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ እነርሱም ሕዝብ ይሆኑኛል።
28መቅደሴም ለዘላለም በመካከላቸው በሆነ ጊዜ፥ እኔ እስራኤልን ለራሴ የለየሁ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ አሕዛብ ያውቃሉ።