1የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፥
2"የሰው ልጅ ሆይ፥ ፊትህን ወደ ሴይር ተራራ አድርግ፥ ትንቢትም ተናገርበት፥
3እንዲህም በለው 'ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የሴይር ተራራ ሆይ፥ እነሆ፥ በአንተ ላይ ነኝ፥ በእጄ እመታሀለሁ ባድማና ድንጋጤ አደርግሃለሁ።
4ከተሞችህንም አፈራርሳቸዋለሁ፥ አንተም ባድማ ትሆናለህ፥ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃለህ።
5ለእስራኤልን ህዝብ ሁል ጊዜ ጥላቻ ስላለህ በመከራቸውም ጊዜ በጽኑ ቅጣት በተቀጡበት ጊዜ የእስራኤልን ልጆች በሰይፍ እጅ ጥለሃቸዋልና
6ስለዚህ እኔ ሕያው ነኝና ለደም መፋሰስ አሳልፌ እሰጥሃለሁ ደም መፋሰስም ያሳድድሃል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር ደም መፋሰስን ስላልጠላህ ደም መፋሰስ ያሳድድሃል።
7በእርሱ የሚያልፈውንም ሆነ ወደ እርሱ የሚመለስ እንዳይኖሬ በማድረግ የሴይርን ተራራ ውድማ አደርገዋለሁ ።
8ተራሮቹንም በተገደሉት ሰዎች እሞላለሁ በኮረብቶችህና በሸለቆችህ በፈሳሾችህም ሁሉ ላይ በሰይፍ የተገደሉት ሁሉ ይወድቃሉ።
9ለዘላለምም ባድማ አደርግሃለሁ ከተሞችህም ሰው የማይኖርባቸው ይሆናሉ፥ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።
10አንተ፥ "እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋሬ ቢሆንም እነዚህ ሁለቱ ሕዝቦች እነዚህም ሁለቱ አገሮች ለእኔ ይሆናሉ እኛም እንወርሳቸዋለን" ብለሃል።
11ስለዚህ እኔ ሕያው ነኝና እንደ ቍጣህ መጠን እነርሱንም ጠልተህ እንዳደረግኸው እንደ ቅንዓትህ መጠን እኔ አደርግብሀለሁ፥ በፈረድሁብህም ጊዜ በእነርሱ ዘንድ የታወቅሁ እሆናለሁ ይላል ጌታ እግዚአብሔር ።
12ስለዚህም እኔ እግዚአብሔር እንደሆንኩ ታውቃለህ። በእስራኤል ተራሮች ላይ "ፈርሰዋል! መብልም ሆነው ለእኛ ተሰጥተዋል" ብለህ የተናገርኸውን ስድብ ሁሉ ሰምቻለሁ።
13በአፋህም በእኔ ላይ የተናገርከውን ትምክህት የተሞላ ንግግር ሰምቻለሁ፤ በኔ ላይ ብዙ ነገሮችን ተናገርክ።፥ እኔም ሰምቼዋለሁ።
14ጌታ እግዚአብሔርም እንዲህ ይላል። ምድር ሁሉ ደስ ሲላት አንተን ባድማ አደርግሃለሁ።
15የእስራኤል ቤት ርስት ባድማ ስለ ሆነ አንተ ደስ እንዳለህ፥ እንዲሁ አደርግብሃለሁ። የሴይር ተራራ ሆይ፥ አንተና ኤዶምያስ ሁሉ ሁለንተናውም ባድማ ትሆናላችሁ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።