1የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፥
2"የሰው ልጅ ሆይ፥ በእስራኤል እረኞች ላይ ትንቢት ተናገር፥ እረኞችንም እንዲህ በላቸው፥ 'ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ራሳቸውን ለሚያሰማሩ ለእስራኤል እረኞች ወዮላቸው! እረኞች በጎችን ያሰማሩ ዘንድ አይገባቸውምን?
3ጮማውን ትበላላችሁ ጠጕሩንም ትለብሳላችሁ! ከመንጋው መካከል የወፈሩትን ታርዳላችሁ! በጎቹን ግን ፈጽሞ አታሰማሩም።
4የደከመውን አላጸናችሁትም የታመመውንም አላከማችሁትም የተሰበረውንም አልጠገናችሁትም የባዘነውንም አልመለሳችሁትም የጠፋውንም አልፈለጋችሁትም በኃይልና በጭቈናም ገዛችኋቸው።
5ያለ እረኛም በማጣት ተበተኑ፥ ከተበተኑም በኋላ ለምድር አራዊት ሁሉ መብል ሆኑ።
6በጎቼ በተራሮች ሁሉና በረዘሙ ኮረብቶች ሁሉ ላይ ተቅበዝብዘዋል፥ በምድርም ፊት ሁሉ ላይ ተበትነዋል። የሚፈልጋቸውም የለም።
7ስለዚህ፥ እረኞች ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ
8ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እኔ ሕያው ነኝና እረኛ ስለሌለ እረኞቼም በጎቼን ስላልፈለጉ እረኞችም ራሳቸውን እንጂ በጎቼን ስላላሰማሩ፥ በጎቼ ንጥቂያና፥ ለምድር አራዊት ሁሉ መብል ሆነዋልና
9ስለዚህ፥ እረኞች ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ
10ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ በእረኞች ላይ ነኝ፥ በጎቼንም ከእጃቸው እፈልጋለሁ፥ በጎቼንም ከማሰማራት አስተዋቸዋለሁ። ከዚያም ወዲያ እረኞች ራሳቸውን አያሰማሩም በጎቼንም ከአፋቸው አድናለሁ፥ መብልም አይሆኑላቸውም።
11ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና። እነሆ፥ እኔ ራሴ በጎቼን እሻለሁ አሰማራቸውማለሁ።
12እረኛ በተበተኑት በጎች መካከል ባለ ጊዜ መንጋውን እንደሚፈልግ፥ እንዲሁ በጎቼን እፈልጋለሁ በደመናና በጨለማ ቀን ከተበተኑት ስፍራ ሁሉ አድናቸዋለሁ።
13ከአሕዛብም መካከል አወጣቸዋለሁ ከአገሮችም እሰበስባቸዋለሁ፥ ወደ ገዛ አገራቸውም እሰበስባቸዋለሁ። በእስራኤልም ተራሮች ላይ በፈሳሾችም አጠገብ በምድርም ላይ ሰዎች በሚኖሩበት ስፍራ ሁሉ አሰማራቸዋለሁ።
14በመልካም ማሰማርያ እሰማራቸዋለሁ የእስራኤል ረጃጅም ተራሮች የግጦሽ ቦታቸው ይሆናል። በዚያ በለመለመ መስክ በመልካምም የግጦሽ ሥፍራ ያርፋሉ፥ በእስራኤልም ተራሮች ላይ ይግጣሉ።
15እኔ ራሴ በጎቼን አሰማራለሁ አስመስጋቸውማለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፦
16የጠፋውንም እፈልጋለሁ የባዘነውንም እመልሳለሁ የተሰበረውንም እጠግናለሁ የደከመውንም አጸናለሁ የወፈረውንና የበረታውንም አጠፋለሁ! በመልካም አሰማራለሁ።
17ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እናንተም መንጋዬ ሆይ፥ እነሆ፥ በበግና በበግ መካከል፥ በአውራ በግና በአውራ ፍየልም መካከል፥ እፈርዳለሁ።
18የቀረውን ማሰማርያችሁን በእግራችሁ የረገጣችሁት፥ በመልካሙ ማሰማርያ መሰማራታችሁ አልበቃ ብሏችሁ ነው? የቀረውንስ ውኃ በእግራችሁ ያደፈረሳችሁት፥ ጥሩውን ውኃ መጠጣታችሁ አልበቃ ብሏችሁ ነው?
19በጎቼም በእግራችሁ በረገጣችሁት ይሰማራሉ በእግራችሁም ያደፈረሳችሁትን ይጠጣሉ።
20ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላቸዋል፥ እነሆ፥ እኔ በወፈሩት በጎችና በከሱት በጎች መካከል እፈርዳለሁ።
21ይህም እስክትበትኑአቸው ድረስ በእንቢያና በትከሻ ስለምትገፉአቸው የደከሙትንም ሁሉ በቀንዳችሁ ስለምትወጉአቸው ነው።
22ስለዚህ መንጋዬን አድናለሁ፥ ከእንግዲህ ወዲህም ለንጥቂያ አይሆኑም። በበግና በበግ መካከልም እፈርዳለሁ።
23በላያቸውም አንድ እረኛ አቆማለሁ እርሱም ያሰማራቸዋል፥ እርሱም ባሪያዬ ዳዊት ነው! ያሰማራቸዋል እረኛም ይሆናቸዋል።
24እኔም እግዚአብሔር አምላክ እሆናቸዋለሁ ባሪያዬም ዳዊት በመካከላቸው አለቃ ይሆናል እኔ እግዚአብሔር ተናግሬአለሁ።
25የሰላምን ቃል ኪዳን ከእነርሱ ጋር እገባለሁ ክፉዎችንም አራዊት ከምድሪቱ አጠፋለሁ፥ በጎቼም ተጠብቀው በምድረ በዳ ይኖራሉ በዱርም ውስጥ ይተኛሉ።
26በእነርሱና በዙሪያ ባሉ ኮረብቶቼ በረከቴን አፈሳለሁ፥ ዝናቡንም በጊዜው እልካለሁ። ይህም የበረከት ዝናብ ይሆናል።
27የምድረ በዳም ዛፍ ፍሬውን ይሰጣል ምድርም ቡቃያዋን ትሰጣለች፥ በጎቼ በምድራቸው ተዘልለው ይኖራሉ የቀንበራቸውንም ማነቆ በሰበርሁ ጊዜ ከሚገዙአቸውም እጅ ባዳንኋቸው ጊዜ፥ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።
28እንግዲህም ለአሕዛብ ንጥቂያ አይሆኑም የምድርም አራዊት አይበሉአቸውም ተዘልለውም ይቀመጣሉ የሚያስፈራቸውም የለም።
29መልካም የእርሻ ቦታ አዘግዝጅላቸዋልሁ፥ ከእንግዲህም ከራብ የተነሣ በምድሪቱ አያልቁም አሕዛብም ከእንግዲህ ወዲህ አይሰድቧቸውም።
30እኔ እግዚአብሔር አምላካቸው ከእነርሱ ጋር እንዳለሁ ያውቃሉ። የእስራኤል ቤት ሕዝቤ እነርሱ ህዝቤ ናቸው ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
31እናንተም በጎቼ፥ የማሰማርያዬ በጎች፥ ህዝቤ ናችሁ እኔም አምላካችሁ እሆናለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር"