1የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፥
2"የሰው ልጅ ሆይ፥ ለሕዝብህ ልጆች ተናገር እንዲህም በላቸው፥ 'ሰይፍን በምድር ላይ ባመጣሁ ጊዜ፥ የምድር ሕዝብ ከመካከላቸው ሰውን ወስደው ለራሳቸው ጕበኛ ያድርጉ።
3ሰይፍ በመጣ ጊዜ ይመልከት ቀንደ መለከቱንም በመንፋት ህዝቡን ያስጠንቅቅ!
4ህዝቡም የመለከቱን ድምፅ ሰምተው ባይጠነቀቁ ፥ ሰይፍ መጥቶ ቢገድላቸው እያንዳንዱ ሰው ደሙ በራሱ ላይ ይሆናል።
5አንድ ሰው የመለከቱን ድምፅ ሰምቶ ባይጠነቀቅ ደሙ በራሱ ላይ ይሆናል፤ ነገር ግን ቢጠነቀቅ የራሱን ህይወት ያድናል።
6ጕበኛው ግን ሰይፍ ሲመጣ ቢያይ መለከቱንም ባይነፋ ሕዝቡንም ባያስጠነቅቅ ሰይፍም መጥቶ አንድን ሰው ቢገድል እሱ በኃጢአቱ ይሞታል፥ደሙን ግን ከጕበኛው እጅ እፈልጋለሁ።
7አንተም፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ ለእስራኤል ቤት ጕበኛ አድርጌሃለሁ፤ ከአፌ ቃሌን ስማ እኔን ወክለህ አስጠንቅቃቸው።
8ኃጢአተኛውን "ኃጢአተኛ ሆይ፥ በእርግጥ ትሞታለህ!" ባልኩት ጊዜ፥ ኃጢአተኛውን ከመንገዱ እንዲመለስ ለማስጠንቀቅ ባትናገር ያ ኃጢአተኛ በኃጢአቱ ይሞታል፥ ደሙን ግን ከእጅህ እፈልጋለሁ።
9ነገር ግን ከመንገዱ እንዲመለስ ኃጢአተኛውን ብታስጠነቅቀው እርሱ ግን ከመንገዱ ባይመለስ በኃጢአቱ ይሞታል አንተ ግን ነፍስህን አድነሃል።
10አንተም፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ የእስራኤልን ቤት እንዲህ በላቸው፥ 'እናንተ በደላችንና ኃጢአታችን በላያችን አሉ እኛም ሰልስለንባቸዋል እንዴትስ በሕይወት እንኖራለን? ብላችኋል' ።
11'እኔ ሕያው ነኝና ኃጢአተኛው ከመንገዱ ተመልሶ በሕይወት እንዲኖር እንጂ ኃጢአተኛው እንዲሞት አልፈቅድም፥ የእስራኤል ቤት ሆይ ንስሀ ግቡ! ስለ ክፉ መንገዳችሁ ንስሀ ግቡ ለምን ትሞታላችሁ ይላል ጌታ እግዚአብሔር?' በላቸው።
12አንተም፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ ህዝብህን እንዲህ በላቸው፥' ጻድቅ ቢበድል ጽድቁ አያድነውም! ኃጢአተኛም ከኃጢአቱ ቢመለስ በኃጢአቱ አይጠፋም። ጻድቁም ኃጢአት ቢስራ በጽድቁ በሕይወት ሊኖር አይችልም።
13እኔ ጻድቁን፥ "በእርግጥ በሕይወት ይኖራል!" ባልሁ ጊዜ፥ እርሱ በጽድቁ ታምኖ ኃጢአት ቢሠራ በሠራው ኃጢአት ይሞታል እንጂ ጽድቁ አላስብለትም።
14እኔም ኃጢአተኛውን። በእርግጥ ትሞታለህ ባልሁ ጊዜ፥ እርሱ ከኃጢአቱ ተመልሶ ፍርድንና ቅን ነገርን ቢያደርግ፥
15ኃጢአተኛውም የብድር መያዣን ቢመልስ የነጠቀውንም ቢመልስ ሕይወት በሚሰጡ ትእዛዛት ቢራመድ ከዚያም በኋላ ኃጢአት ባይሠራ፥ በእርግጥም በሕይወት ይኖራል እንጂ አይሞትም።
16የሠራው ኃጢአት ሁሉ አይታሰብበትም። ፍርድንና ቅን ነገርን አድርጎአል በእርግጥ በሕይወት ይኖራል።
17ነገር ግን ሕዝብህ ፥ "የጌታ መንገድ የቀና አይደለም!" ይላሉ ነገር ግን ቅን ያልሆነው የእናንተ መንገድ ነው!
18ጻድቅ ከጽድቁ ተመልሶ ኃጢአትን ቢሠራ በኃጢአቱ ይሞታል!
19ኃጢአተኛውም ከኃጢአቱ ተመልሶ ፍርድንና ቅን ነገርን ቢያደርግ ባደረጋቸው ነገሮች ምክንያት በሕይወት ይኖራል።
20እናንተ ግን፥ "የጌታ መንገድ የቀና አይደለም!" ትላላችሁ። የእስራኤል ቤት ሆይ፥ በእያንዳንዳችሁ ላይ እንደ መንገዳችሁ እፈርድባችኋለሁ።
21እንዲህም ሆነ በተማረክን በአሥራ ሁለተኛው ዓመት በአሥረኛው ወር ከወሩም በአምስተኛው ቀን ከኢየሩሳሌም ያመለጠ አንድ ሰው ወደ እኔ መጥቶ "ከተማይቱ ተያዘች!"አለኝ።
22ሰውዬው ከመምጣቱ በፊት ባለው ምሽት የእግዚአብሔር እጅ በእኔ ላይ ነበረች፥ ሰውዬው በምሽት ወደ እኔ በመጣ ጊዜ አፌ ተከፍቶ ነበር። ስለዚህም አፌ ተከፍቶ ነበር ከዚያም በኋላ እኔ ዲዳ አልሆንሁም።
23የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
24የሰው ልጅ ሆይ፥ በእስራኤል ምድር ባሉ በባድማ ስፍራዎች የተቀመጡ፥ 'አብርሃም ብቻውን ሳለ ምድሪቱን ወረሰ እኛም ብዙዎች ነን ምድሪቱም ርስት ሆና ለእኛ ተሰጥታለች' ይላሉ።
25ስለዚህ እንዲህ በላቸው፥'ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ከደም ጋር ትበላላችሁ፥ ዓይናችሁንም ወደ ጣዖቶቻችሁ ታነሣላችሁ፥ የስዎችንም ደም ታፈስሳላችሁ። በውኑ ምድሪቱን ትወርሳላችሁን?
26በሰይፋችሁ ተማምናችሁ፥ ርኩስ ነገርን ታደርጋላችሁ፥ የባልንጀሮቻችሁንም ሚስቶች ታስነውራላችሁ። በውኑ ምድሪቱን ትወርሳላችሁን?
27እንዲህም በላቸው፥ 'ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እኔ ሕያው ነኝና በባድማ ስፍራዎች ያሉ በሰይፍ ይወድቃሉ፥ በምድረ በዳ ያለውን ለአራዊት መብል አድርጌ እሰጣለሁ፥ በአምባዎችና በዋሾች ያሉ በቸነፈር ይሞታሉ።
28ምድሪቱንም ባድማና ውድማ አደርጋታለሁ በኃይሏም መመካቷ ይቀራል፥ የእስራኤልም ተራሮች ማንም የማያልፍባቸው በረሀ ይሆናሉ፥ ።
29ስላደረጉትም ርኵሰት ሁሉ ምድሪቱን ባድማና ውድማ ባደርግሁ ጊዜ፥ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።
30አንተም፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ ሕዝብህ በቅጥር አጠገብና በቤት ደጆች ውስጥ ስለ አንተ ይናገራሉ፥ እርስ በርሳቸውም፥ አንዱ ከአንዱ ጋር፥ 'ወደ ነቢዩ እንሂድና እግዚአብሔር ያለው ቃል ምን እንደ ሆነ እንስማ!' እያሉ ይነጋገራሉ።
31ስለዚህ ሕዝቤ ብዙ ጊዜ እንደሚያደርጉት መጥተው በፊትህ ይቀመጣና ቃልህንም ይሰማሉ ነገር ግን አያደርጉትም። ትክክለኛው ቃል በፍቸው ነው ፥ ልባቸው ግን ቅንነት የሌለበትን ትርፍ ትከተላለች።
32እነሆ፥ አንተ መልካም ድምፅ እንዳለው እንደሚወደድ መዝሙር ማለፊያም አድርጎ እንደሚጫወቱት በገና ሆነህላቸዋል ስለዚህም ቃልህን ይሰማሉ ነገር ግን አንዳቸውም አያደርጉትም።
33እነሆ፥ ይህ ይመጣል በመጣም ጊዜ እነርሱ ነቢይ በመካከላቸው እንደ ነበረ ያውቃሉ።"