1እንዲህም ሆነ በአሥራ አንደኛው ዓመት በሦስተኛው ወር ከወሩም በመጀመሪያው ቀን የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
2የሰው ልጅ ሆይ፥ የግብጽን ንጉሥ ፈርዖንንና በዙሪያው ያሉትን አገልጋዮቹን እንዲህ በላቸው። 'በታላቅነትህ ማንን ትመስላለህ?
3እነሆ፥ አሦር ጫፉ እንደ ተዋበ፥ ችፍግነቱ ጥላ እንደ ሰጠ፥ ቁመቱም እንደ ረዘመ፥ ራሱም በደመናዎች መካከል እንደ ነበረ እንደ ሊባኖስ ዝግባ ነበረ።
4ውኆችም አበቀሉት፥ ቀላይም ግዙፍ አደረገው። ወንዞችም በተተከለበት ዙሪያ ይጐርፉ ነበር፥ መስኖዎቻቸውን በሜዳ ወዳሉ ዛፎች ይሰዳሉ።
5ቁመቱ ከምድረ በዳ ዛፍ ሁሉ ከፍ ያለ ነበር አለ፤ ቅርንጫፎቹም ከብዙ ውኆች የተነሣ ረዘሙ።
6የሰማይ ወፎች ሁሉ ጎጆቻቸውን በቅርንጫፎቹ ላይ አደረጉ፥ የምድርም አራዊት ሁሉ ከጥላው በታች ተዋለዱ። ታላላቅ ህዝቦች ከጥላውም በታች ኖሩ።
7ሥሩም በብዙ ውኃ አጠገብ ነበረና በታላቅነቱና በቅርንጫፎቹ ርዝመት የተዋበ ነበረ።
8በእግዚአብሔር ገነት የነበሩ ዝግባዎች አልተካከሉትም! ጥዶችም ቅርንጫፎቹን አይመስሉትም አስታ የሚባለውም ዛፍ ቅርንጫፎቹን አይተካከሉም! በእግዚአብሔርም ገነት ካሉ ዛፎች በውበቱ ሊተካከለው አልቻለም!
9በቅርንጫፎቹ ብዛት ውብ አደረግሁት፤ በእግዚአብሔርም ገነት በዔድን የነበሩ ዛፎች ሁሉ ቀኑበት።
10ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ቁመቱ ከፍ ከፍ ብሎአልና፥ ጫፎቹንም ከቅርንጫፎች በላይ አድርጎአልና፥
11ልቡም በቁመቱ ልክ ኰርቶአልና ከአሕዛብ ሁሉ በላይ ኃይለኛ ገዢ እጅ አሳልፌ እሰጠዋለሁ! ይህም ገዢ ይቃወመዋል እንደ ክፋቱም መጠን ያሳድደዋለሁ።
12የአህዛብ ድንጋጤ የሆኑ የሌላ አገር ሰዎች፥ አስወግዱት ፈጽሞም ጣሉት። ቅርንጫፎቹ በተራሮችና ላይና በሸለቆች ውስጥ ወደቁ፥ ቅርንጫፎቹም በምድር ፈሳሾች ሁሉ ላይ ተሰባበሩ። የምድርም አሕዛብ ሁሉ ከጥላው ወጥተው ጥለውት ሄዱ።
13የሰማይ ወፎች ሁሉ በግንዱ ላይ ይቀመጣሉ የምድርም አራዊት ሁሉ በቅርንጫፎቹ ላይ ይቀመጣሉ።
14ይህም የሆነው ወደ ጕድጓድ በሚወርዱ በሰው ልጆች መካከል ሁላቸው ለታችኛው ምድር ለሞት አልፈው ተሰጥተዋልና ውሀ ሲጠጡ ከነበሩት ዛፎች ውስጥ አንዳቸውም ረጅም ሆነው እንዳያድጉ፥ ጫፎቻቸውም ከቅጠሎች በላይ እንዳይሆኑ፥ በውኃ አጠገብ ያሉ ዛፎች ሁሉ ከእንግዲህ በቁመታቸው እንዳይረዝሙ ነው።
15ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ወደ ሲኦል በወረደበት ቀን ልቅሶን ወደ ምድር አመጣሁ። በቀላያትም ሸፈንኩት፥ የውቅያኖስ ፈሳሾቹንም ከለከልሁ። ታላላቆችም ውኆች ከለከልኩ፥ ሊባኖስንም ስለ እርሱ አሳዘንሁት! የዱርም ዛፎች ሁሉ ስለ እርሱ አለቀሱ።
16ወደ ጕድጓድ ከሚወርዱ ጋር ወደ ሲኦል በጣልሁት ጊዜ ክአውዳደቁ ድምፅ የተነሣ በአሕዛብ ላይ መንቀጥቀጥን አመጣሁ! በምድር ዝቅተኛ ቦታ የኤደን ዛፎችን ሁሉ አጽናናለሁ! እነርሱም ውኃ የሚጠጡ ፥ ምርጦችና መልካካሞች የሊባኖስ ዛፎች ናቸው።
17ክንዱም ወደ የነበሩት በአሕዛብም መካከል በጥላው ሥር የተቀመጡት፥ በሰይፍ ወደ ተገደሉት ሰዎች ወደ ሲኦል ከእርሱ ጋር ወርደዋልና።
18በክብርና በታላቅነት በዔድን ዛፎች መካከል ማን ይመስልህ ነበር? ነገር ግን ከዔድን ዛፎች ጋር ወዳልተገረዙት መካከል ወደ ታችኛው ምድር ያወርዱሃል፤ በሰይፍም ከተገደሉት ጋር ትኖራለህ! እነርሱም ፈርዖንና አገልጋዮቹ ናቸው ይላል ጌታ እግዚአብሔር!"