1የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
2የሰው ልጅ ሆይ፥ ትንቢት ተናገር እንዲህም በል። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ዋይ! በሉ፥ ለቀኑ ወዮ! ቀኑ ቅርብ ነው፥
3የእግዚአብሔር ቀን ቅርብ ነው፥ የደመና ቀን፥ ለአሕዛብም ክፉ ወቅት ይሆናል።
4ሰይፍ በግብጽ ላይ ይመጣል፥ የተገደሉት ሰዎች በግብጽ ውስጥ ሲወድቁ ሀብቷን ሲወስዱ መሠረትዋም ሲፈርስ በኢትዮጵያ ውስጥ ሁከት ይሆናል!
5ኢትዮጵያ፥ ፉጥና ሉድም እንግዶችም የቃል ኪዳንም ህዝቦች ከእነርሱ ጋር በሰይፍ ይወድቃሉ።
6እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ግብጽን የሚደግፉ ይወድቃሉ፥ የኃይልዋም ትምክህት ይወርዳል። ከሚግዶል ጀምሮ እስከ ሴዌኔ ድረስ ወታደሮቻቸው በሰይፍ ይወድቃሉ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር!
7ባድማም በሆኑ አገሮች መካከል ይሸበራሉ፥ ከተሞቻቸውም እንደ ፈረሱት ከተሞች ይሆናሉ።
8እሳትንም በግብጽ ባነደድሁ ጊዜ ረዳቶችዋም ሁሉ በጠፉጊዜ፥ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ!
9በዚያ ቀን መልእክተኞች ተዘልለው የሚኖሩትን ኢትዮጵያውያንን ለማስፈራት ከፊቴ በመርከብ ይወጣሉ በግብጽም ጥፋት ቀን ሁከት ይሆንባቸዋል። እነሆ፥ ይመጣልና!
10ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በባቢሎን ንጉሥ በናቡከደነፆር እጅ የግብጽን ህዝብ ፍጻሜ አመጣለሁ።
11የአህዛብ ድንጋጤ የሆኑት እርሱና ሠራዊቱ ምድሪቱን ለማጥፋት ይመጣሉ፤ ሰይፋቸውንም በግብጽ ላይ ይመዝዛሉ ምድሪቱንም በሞቱ ሰዎች ይሞላሉ!
12ወንዞችን ደረቅ መሬት አደርጋለሁ ምድሪቱንም ለክፉ ሰዎች እሸጣለሁ። ምድሪቱንና ሙላዋንም በእንግዶች እጅ ባድማ አደርጋለሁ! እኔ እግዚአብሔር ተናግሬያለሁ!
13ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ጣዖቶችን አጠፋለሁ እርባና ቢስ የሆኑትን የሜምፎስ ጣዖታት እሽራለሁ። ከእንግዲህ ወዲያ በግብጽ ምድር አለቃ አይገኝም ፥ በግብጽም ምድር ላይ ሽብርን አደርጋለሁ!
14ጳትሮስንም አፈርሳለሁ፥ በጣኔዎስም እሳትን አነድዳለሁ፥ በኖእ ላይም ፍርድን አደርጋለሁ።
15በግብጽም ምሽግ በሲን ላይ መዓቴን አፈስሳለሁ፥ የኖእንም ህዝብ አጠፋለሁ።
16ከዚያም በግብጽ እሳትን አነድዳለሁ። ሲንም ትጨነቃለች ኖእም ትሰበራለች፥ ሜምፎስም በየቀኑ ጠላቶች ይነሱባታል!
17የሄልዮቱና የቡባስቱም ወጣቶች በሰይፍ ይወድቃሉ ከተሞቻቸውም ይማረካሉ።
18በዚያ የግብጽን ቀንበር በሰበርሁ ጊዜ በጣፍናስ ቀኑ ይጨልማል የኃይልዋም ትዕቢት ይጠፋል። ደመናም ይጋርዳታል፥ ሴቶች ልጆችዋም ይማረካሉ።
19እንዲሁ በግብጽ ላይ ፍርድን አደርጋለሁ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።
20እንዲህም ሆነ በአሥራ አንደኛው ዓመት በመጀመሪያው ወር ከወሩም በሰባተኛው ቀን የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
21የሰው ልጅ ሆይ፥ የግብጽን ንጉሥ የፈርዖንን ክንድ ሰብሬያለሁ።። እነሆም፥ እንዲድን በጨርቅ አልታሰረም በመቃም አልታሰረለትም ስለዚህም ሰይፍን ለመያዝ የሚያስችል ጥንካሬ የለውም።
22ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ እኔ በግብጽ ንጉሥ በፈርዖን ላይ ተነስቻለሁ! ጠንካራውንም የተሰበረውንም ክንዱን እሰብራለሁ፥ ሰይፉንም ከእጁ አስጥላለሁ።
23ግብጻውያንንም ወደ አሕዛብ እበትናለሁ ወደ አገሮችም እዘራቸዋለሁ።
24የፈርዖንን ክንድ ለመስበር የባቢሎንን ንጉሥ ክንድ አበረታለሁ ሰይፌንም በእጁ እሰጣለሁ። በባቢሎን ንጉሥ ፊት ለሞት እንድሚያጣጥር ሰው ያጓራል።
25የባቢሎንንም ንጉሥ ክንድ አጸናለሁ የፈርዖን ክንድ ግን ይወድቃል። ሰይፌንም በባቢሎን ንጉሥ እጅ በሰጠሁ ጊዜ እርሱም በሰጠሁት ሰይፍ የግብጽን ምድር በሚመታ ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።
26ግብጻውያንንም ወደ አሕዛብ እበትናለሁ ወደ አገሮችም እዘራቸዋለሁ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።