መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ሕዝቅኤል 29

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1በአሥረኛው ዓመት በአሥረኛው ወር ከወሩም በአሥራ ሁለተኛው ቀን የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
2የሰው ልጅ ሆይ፥ ፊትህን በግብጽ ንጉሥ በፈርዖን ላይ አድርግ፥ በእርሱና በግብጽ ሁሉ ላይም ትንቢት ተናገር፥
3እንዲህም በል። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በወንዞች መካከል የምትተኛና። ወንዙ የእኔ ነው ለራሴም ሠርቼዋለሁ የምትል ታላቅ የባህር ውስጥ ፍጥረት፥ የግብጽ ንጉሥ ፈርዖን ሆይ፥ እነሆ፥ በአንተ ላይ ነኝ።
4በመንጋጋህ መቃጥን አገባብሃለሁ፥ የወንዞችህንም ዓሦች ወደ ቅርፊትህ አጣብቃለሁ በቅርፊትህ ላይ ከተጣበቁ ዓሦች ሁሉ ጋር ከወንዞችህም መካከል አወጣሃለሁ።
5አንተንና የወንዞችህን ዓሦች ሁሉ ወደ ምድረ በዳ እጥላለሁ፥ በምድርም ፊት ላይ ትወድቃለህ እንጂ አትከማችም አትሰበሰብም። መብልም አድርጌ ለምድር አራዊትና ለሰማይ ወፎች እሰጥሀለሁ።
6ለእስራኤል ቤት የሸንበቆ በትር ሆነዋልና በግብጽም የሚኖሩ ሁሉ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።
7በእጅ በያዙህ ጊዜ ተሰበርህና ተሰነጣጥቅህ ትከሻቸውን ትወጋለህ፤ በተደገፉብህም ጊዜ እግራቸውን ትሰባብራለህ ወገባቸውንም እንዲንቀጠቀጥ ታደርጋለህ።
8ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ ሰይፍ አመጣብሃለሁ፥ ሰውንና እንስሳንም ከአንተ ዘንድ አጠፋለሁ።
9የባህር ጭራቁ "ወንዙ የእኔ ነው የሠራሁትም እኔ ነኝ" ብሏልና የግብጽ ምድር ባድማና ውድማ ትሆናለች፥ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ አንተ።
10ስለዚህ፥ እነሆ፥ በአንተና በወንዞችህ ላይ ነኝ፥ የግብጽንም ምድር ከሚግዶል ጀምሮ እስከ ሴዌኔና እስከ ኢትዮጵያ ዳርቻ ድረስ ውድማና ባድማ አደርጋታለሁ።
11የሰው እግር አያልፍባትም የእንስሳም ኮቴ አያልፍባትም፥ እስከ አርባ ዓመትም ድረስ ማንም አይኖርባትም።
12ባድማም በሆኑ ምድሮች መካከል የግብጽን ምድር ባድማ አደርጋታለሁ፥ በፈረሱትም ከተሞች መካከል ከተሞችዋ አርባ ዓመት ፈርሰው ይቀመጣሉ ግብጻውያንንም ወደ አሕዛብ እበትናቸዋለሁ በአገሮችም እዘራቸዋለሁ።
13ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ከአርባ ዓመት በኋላ ግብጻውያንን ከተበተኑባቸው አሕዛብ ዘንድ እሰበስባለሁ
14የግብጽንም ምርኮ እመልሳለሁ፥ ወደ ተወለዱባትም ምድር ወደ ጳትሮስ እመልሳቸዋለሁ በዚያም የተዋረደች መንግሥት ይሆናሉ።
15ከሌሎች መንግሥታት ሁሉ ይልቅ የተዋረደች ትሆናለች ከእንግዲህ ወዲያ ከአሕዛብ መካከል ከፍ አትልም።ከእንግዲህም በአሕዛብም ላይ እንዳይገዙ አሳንሳቸዋለሁ።
16ግብጻውያን ከእንግዲህ ለእስራኤል ቤት የትምክህት ምክንያት አይሆኑም። ይልቁኑ እስራኤል ለእርዳታ ፊቷን ወደ ግብጽ ባዞረች ጊዜ የፈጸመችውን በደል የሚያሳስቡ ይሆናሉ።እኔም ጌታ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።
17እንዲህም ሆነ በሀያ ሰባተኛው ዓመት በመጀመሪያው ወር ከወሩም በመጀመሪያው ቀን የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
18የሰው ልጅ ሆይ፥ የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር በጢሮስ ላይ ጽኑ ሥራ ለማሰራት ሠራዊቱን ሰበሰበ። ራስ ሁሉ ተላጭቶ ጫንቃም ሁሉ ተልጦ ነበር፥ ነገር ግን በላይዋ ስላገለገለው አገልግሎት እርሱና ሠራዊቱ ምንም አይነት ደመወዝ ከጢሮስ አልተቀበሉም።
19ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ የግብጽን ምድር ለባቢሎን ንጉሥ ለናቡከደነፆር እሰጠዋለሁ፥ ብዛትዋንም ይወስዳል ምርኮዋንም ይማርካል ብዝበዛዋንም ይበዘብዛል ይህም ለሠራዊቱ ደመወዝ ይሆናል።
20ለእኔ ለሠሩት ሥራ ደመወዝ አድርጌ የግብጽን ምድር ሰጥቼዋለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፦
21በዚያ ቀን ለእስራኤል ቤት ቀንድን አበቅላለሁ፥ በመካከላቸውም ለአንተ የተከፈተ አፍን እሰጣለሁ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።