መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ሕዝቅኤል 28

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
2የሰው ልጅ ሆይ፥ የጢሮስን ገዥ እንዲህ በለው፥ 'ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ልብህ ኰርቶአል፥ አንተም "እኔ አምላክ ነኝ! በባሕር መካከል በአማልክት ወንበር ላይ እቀመጣለሁ!" ብለሃል። ነገር ግን አንተ ሰው እንጂ እግዚአብሔር ባትሆንም ልብህን እንደ አምላክ ልብ አደረግህ።
3እነሆ፥ ከዳንኤል ይልቅ ጥበበኛ እንደሆንክ ምንም ሚስጢር ከአንተ እንደማይሰወር አሰብክ።
4በጥበብና በማስተዋል ራስህን አበልጽገሀል፥ ወርቅና ብርም በግምጃ ቤትህ ውስጥ ሰብስበሃል!
5በታላቅ ጥበብና በንግድህ ብልጥግናህን አብዝተሃል ከብልጥግናህም የተነሳ ልብህ ኰርቶአል!
6ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ልብህን እንደ አምላክ ልብ አድርገሃልና
7ስለዚህ፥ እነሆ፥ እንግዳ ሰዎችን፥ የአሕዛብን ጨካኝ ሰዎችን አመጣብሃለሁ! ሰይፋቸውንም በጥበብህ ውበት ላይ ይመዝዛሉ፥ ክብርህንም ያዋርዳሉ!
8ወደ ጕድጓድ ያወርዱሃል፥ በባህር ልብ ውስጥ የሞቱትን ሰዎች ሞት ትሞታለህ።
9በውኑ በገዳይህ ፊት፥ "እኔ አምላክ ነኝ" ትላለህን? አንተ ሰው ነህ እንጂ አምላክ አይደለህም፥ በሚቆራርጡህ እጅ ትወድቃለህ።
10በእንግዶች ሰዎች እጅ ያልተገረዙትን ሰዎች ሞት ትሞታለህ እኔ ተናግሬአለሁና፥ ይላል እግዚአብሔር!"
11የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
12የሰው ልጅ ሆይ፥ በጢሮስ ንጉሥ ላይ ሙሾ አሞሽተህ እንዲህ በለው፥ 'ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፡ጥበብን የተሞላህ የፍጽምና መደምደሚያ በውበትህም ፍጹም ነበርክ!
13በእግዚአብሔር ገነት በዔድን ነበርህ! በከበረ ዕንቍስ ሁሉ፥ ሰርድዮን፥ ቶጳዝዮን፥ አልማዝ፥ ቢረሌ፥ መረግድ፥ ኢያስጲድ፥ ሰንፔር፥ በሉር፥ የሚያብረቀርቅ ዕንቍ፥ ወርቅ፥ ተሽፍነህ ነበረ። እነዚህ የከበሩ ድንጋዮች በወርቅ ዕቃ በፊትህ ተቀምጠው ነበር። አነዚህም በተፈጠርህበት ቀን እንድትለብሳቸው ተዘጋጅተው ነበር!
14የሰውን ዘር እንዲጋርድ እንደቀባሁት ኪሩብ በተቀደሰው በእግዚአብሔር ተራራ ላይ አኖርሁህ! ትመላለስባቸው በነበሩ የእሳት ድንጋዮች መካከል ነበርክ።
15ከተፈጠርህበት ቀን ጀምረህ በደል እስኪገኝብህ ድረስ በመንገድህ ፍጹም ነበርህ።
16በንግድህ ብዛት በአምጽ ተሞላህ ስለዚህም ኃጢአትን ሠራህ! ስለዚህ እንደ ርኩስ ነገር ከእግዚአብሔር ተራራ ጣልሁህ የምትጋርድ ኪሩብ ሆይ፥ ከእሳት ድንጋዮች መካከል አጠፋሁህ።
17በውበትህ ምክንያት ልብህ ኰርቶአል፤ ከክብርህ የተነሣ ጥበብህን አረከስህ! ወደ ምድርም ጣልሁህ! ያዩህም ዘንድ በነገሥታት ፊት አስቀመጥኩህ።
18በበደልህ ብዛት ቅን ባልሆነው ንግድህም ቅዱስ ስፍራህን አረከስህ! ስለዚህ እሳትን ከውስጥህ አውጥቻለሁ እርስዋም ትበላሀለች። በሚያዩህም ሁሉ ፊት በምድር ላይ አመድ አደርግሀለሁ።
19በአሕዛብም ውስጥ የሚያውቁህ ሁሉ ይደነቁብሃል፤ ይደነግጣሉ ፥ አንተም እስከ ዘላለምም አትገኝም።
20የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፥
21"የሰው ልጅ ሆይ፥ ፊትህን ወደ ሲዶና አቅንተህ ትንቢት ተናገርባት! እንዲህም በል፥
22'ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ሲዶና ሆይ፥ እነሆ፥ በአንቺ ላይ ነኝ፥ ፍርድን በውስጥሽ በማደርግበት ጊዜ ህዝብሽ እኔ እግዚአብሔር እንድሆንኩ እንዲያውቁ በመካከልሽ ክብሬን እገልጣለሁ። ቅዱስ መሆኔም ይገለጣል።
23ቸነፈርንም በአንቺ ላይ፥ ደምንም በጎዳናሽ ላይ እሰድዳለሁ፥ በሰይፍ የታረዱ በመካከልሽ ይወድቃሉ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቂያለሽ!
24እኔ ጌታ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ እንዲያውቁ ከእንግዲህም ወዲያ ለእስራኤል ቤት የሚወጋ እሾህ፥ በዙሪያቸውም ካሉ ከናቋቸው ሁሉ የሚያቈስል ኵርንችት አይሆንም
25ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የእስራኤልን ቤት ከተበተኑባቸው አሕዛብ ዘንድ በሰበሰብሁ ጊዜ፥ በአሕዛብም ፊት በተቀደስሁባቸው ጊዜ፥ ለባሪያዬ ለያዕቆብ በሰጠኋት ምድራቸው ይቀመጣሉ።
26በውስጧም ተዘልለው ይቀመጡባታል ቤቶችንም ይሠራሉ ወይኑንም ይተክላሉ በዙሪያቸውም ባሉ በሚንቋቸው ሁሉ ላይ ፍርድን ባደረግሁ ጊዜ ተዘልለው ይቀመጣሉ እኔም እግዚአብሔር አምላካቸው እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።