1በዘጠነኛው ዓመት በአሥረኛው ወር ከወሩም በአሥረኛው ቀን የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
2"የሰው ልጅ ሆይ፥ በዚህ ቀን የባቢሎን ንጉሥ ኢየሩሳሌምን ከቧልና የዚህን ቀን፥ የዛሬን ቀን ስም ጻፍ ።
3ለዓመፀኛውም ቤት ምሳሌን ተናገር እንዲህም በላቸው፥ 'ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ድስቱን ጣድ! ጣደው! ውኃም ጨምርባት!
4የምግብ ፍራፍሬዎችን በውስጡ ጨምር፥ ጭኑንና ወርቹን በእርስዋ ውስጥ ሰብስብ፥ የተመረጡትንም አጥንቶች ሙላባት!
5ከመንጋው የተመረጠውን ውሰድ፥ አጥንቶቹም እንዲበስሉ እንጨት በበታችዋ ማግድ አጥንቶቹም በውስጥዋ ቀቅል።
6ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ዝገት ላለባት ዝገትዋም ለማይለቃት ምንቸት፥ ለደም ከተማ ወዮላት! ጥቂት ጥቂት ከውስጡ ውሰድ፥ ነገር ግን ዕጣ አታውጣላት።
7ደምዋ በውስጥዋ አለና! በተራቈተ ድንጋይ ላይ አደረገችው እንጂ በአፈር ይከደን ዘንድ በመሬት ላይ አላፈሰሰችውም
8ይህም መዓትን አመጣባት። ደምዋም እንዳይከደን በተራቈተ ድንጋይ ላይ አፈሰስኩት!
9ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ለደም ከተማ ወዮላት! እኔ ደግሞ የማገዶውን ክምር አሳድጋለሁ።
10እንጨቱን ጨምር! እሳቱን አንድድ! ሥጋውን ቀቅል መረቁን አጣፍጠው! አጥንቶቹም በደንብ ይቃጠሉ።
11እንድትሞቅና እንድትግል በውጧ ያለው ርኵሰትዋ በውስጥዋ ይቀልጥ ዘንድ ዝገትዋም ይጠፋ ዘንድ ባዶዋን ድስት በፍም ላይ ጣዳት።
12በከንቱ ደከመች ሆኖም ዝገትዋ በእሳት ስንኳ አልለቀቀም።
13አሳፋሪው ተግባርሽ በርኵሰትሽ ውስጥ ነው። እኔ ባነጻሽም አልነጻሽም። መዓቴን በላይሽ እስክጨርስ ድረስ ከርኵሰትሽ አትነጺም።
14እኔ እግዚአብሔር ይሆናል ብዬ ተናግሬአለሁ ፥ እኔም አደርገዋለሁ! አልመለስም፥ ፥ አልጸጸትምም። እንደ መንገድሽና እንደ ሥራሽ ይፈርዱብሻል! ይላል ጌታ እግዚአብሔር።"
15የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፥
16"የሰው ልጅ ሆይ፥ እነሆ፥ የዓይንህን አምሮት በመቅሠፍት እወስድብሃለሁ አንተም ማዘንም ሆነ ማልቀስ የለብህም እንባህንም አታፍስስ።
17በቀስታ ተክዝ። ለምዋቾችም የቀብር ሥርዓትም አታዘጋጅ። መጠምጠሚያህን በራስህ ላይ አድርግ፥ ጫማህንም በእግርህ አጥልቅ፥ ጢምህን አትሸፍን ወይም ሚስቶቻቸው በመሞታቸው ምክንያት እያዘኑ ያሉ ሰዎችን እንጀራ አትብላ።
18እኔም በማለዳ ለሕዝቡ ተናገርሁ፥ ምሽት ላይም ሚስቴ ሞተች። በነጋውም እንደ ታዘዝሁ አደረግሁ።
19ሕዝቡም፥ "ይህ የምታደርገው ነገር ምን እንደ ሆነ አትነግረንምን?" አሉኝ።
20እኔም እንዲህ አልኋቸው፥ "የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፥
21ለእስራኤል ቤት ተናገር እንዲህም በል፥ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ የኃይላችሁ ትምክሕት፥ የዓይናችሁ አምሮት፥ ክፉ ምኞታችሁ መቅደሴን አርክሰዋል! ያስቀራችኋቸውም ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁ በሰይፍ ይወድቃሉ።
22እኔም እንዳደረግሁ እናንተ ታደርጋላችሁ ጢማችሁን አትሸፍኑም የኃዘንተኛ ሰዎችንም እንጀራ አትበሉም!
23ይልቁኑ መጠምጠሚያችሁም በራሳችሁ ጫማችሁም በእግራችሁ ይሆናል፤ አታዝኑም ወይም አታለቅሱምም በኃጢአታችሁም ትሰለስላላችሁና እያንዳንዱ ሰው ስለወንድሙ ያቃስታል።
24ይህ በሚሆንባችሁ ጊዜ ሕዝቅኤልም ምልክት ይሆናችኋል እርሱ እንዳደረገ ሁሉ እናንተ ታደርጋላችሁ። ከዚያም እኔ ጌታ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።
25አንተም የሰው ልጅ ሆይ፥ ደስታቸው፥ ትምክህታቸው የሆነውን መቅደሳቸውንና የሚያዩትና የተመኙትን በያዝኩ ጊዜ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን በወሰድሁባቸው ቀን፥
26በዚያ ቀን ያመለጠ ሰው ይህን ሊነግርህ ይመጣል።
27በዚያ ቀን አፍህ አምልጦ ለመጣው ይከፈታል፥ አንተም ትናገራለህ ከዚያ ወዲያም ዝም አትልም። ምልክትም ትሆናቸዋለህ፥ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።