1እንዲህም ሆነ በሰባተኛው ዓመት በአምስተኛው ወር ከወሩም በአሥረኛው ቀን የእስራኤል ሽማግሌዎች እግዚአብሔርን ሊጠይቁ መጥተው በፊቴ ተቀመጡ።
2የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፥
3"የሰው ልጅ ሆይ፥ ለእስራኤል ሽማግሌዎች ተናገር፥ እንዲህም በላቸው። 'ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እኔን ትጠይቁ ዘንድ መጥታችኋልን? በህያውነቴ እምላለሁ በእናንተ አልጠየቅም! ይላል ጌታ እግዚአብሔር፦
4ትፈርድባቸዋለህን? የሰው ልጅ ሆይ፥ በውኑ ትፈርድባቸዋለህን? የአባቶቻቸውን ርኵሰት አስታውቃቸው!
5እንዲህም በላቸው፥ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እስራኤልን በመረጥሁበት ለያዕቆብም ቤት ዘር እጄን አንስቼ በማልሁበት ቀን በግብጽም ምድር በተገለጥሁላቸውና። እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ ብዬ በማልሁላቸው ጊዜ፥
6በዚያ ቀን ከግብጽ ምድር በጥንቃቄ ወደመረጥኩላቸው፥ ወተትና ማር ወደምታፈስሰው፥ የምድርም ሁሉ ጌጥ ወደምትሆን ምድር እንደማወጣቸው ማልሁላቸው!
7እኔም፥ "ከእናንተ እያንዳንዱ ርኩስ ነገርንና የግብጽን ጣዖታት ከዓይኑ ፊት ያስወግድ። ራሳችሁን አታርክሱ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ።" አልኋቸው።
8እነርሱ ግን ዐመፁብኝ ሊሰሙኝም አልወደዱም። እያንዳንዱ ርኩስ ነገሮችን ከአይኑ ፊት አላስወገደም የግብጽንም ጣዖታት አልተወም በዚህም ጊዜ። በግብጽ ምድር መካከል ቍጣዬን ልፈጽምባቸው መዓቴንም ላፈስባቸው ወሰንኩ።
9ነገር ግን በመካከላቸው በሚኖሩበት ህዝብ መካከል እንዳይረክስ ስለ ስሜ ሰራሁ። ከግብጽ ምድር በማውጣት ራሴን በአይናቸው ፊት ገለጥኩላቸው።
10ከግብጽም ምድር አወጣኋቸው ወደ ምድረ በዳም አመጣኋቸው።
11ሰው ቢያደርገው በሕይወት የሚኖርበትን ሥርዓቴንም ሰጠኋቸው፥ ፍርዴንም አስታወቅኋቸው።
12ለራሴ የለየኋቸው እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቁ ዘንድ፥ በእኔና በእነርሱ መካከል ምልክት እንዲሆን ሰንበታቴን ሰጠኋቸው።
13ነገር ግን የእስራኤል ቤት በምድረ በዳ ዐመፁብኝ። በትዕዛዜም አልሄዱም፤ ይልቁኑ ሰው ቢያደርገው በሕይወት የሚኖርበትንም ፍርዴን ጣሉ። ሰንበታቴንም ፈጽመው አረከሱ፥ ስለዚህም አጠፋቸው ዘንድ ቍጣዬን በምድረ በዳ አፈስስባቸዋለሁ አልሁ።
14ነገር ግን በፊታቸው ባወጣኋቸው በአሕዛብ ፊት ስሜ እንዳይረክስ ብዬ ስለ ስሜ ሠራሁ።
15ወተትና ማርም ወደምታፈስሰው የምድር ሁሉ ጌጥ ወደምትሆን ልሰጣቸው ወዳሰብኩት ምድር አላመጣቸውም ብዬ በምድረ በዳ ማልሁባቸው።
16ይህን የማልኩት ልባቸው ጣዖቶቻቸውን ስለተከተሉ፥ ፍርዴንም ስለጣሉ ፥ በሥርዓቴም ስላልሄዱ፥ ሰንበታቴንም ስላረከሱ ነው።
17ነገር ግን ዓይኔ ራራችላቸው እኔም አላጠፋኋቸውም፥ በምድረ በዳም ፈጽሜ አልፈጀኋቸውም።
18ለወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸው በምድረ በዳ እንዲህ አልኋቸው፥ "በአባቶቻችሁ ሥርዓት አትሂዱ፤ ወጋቸውንም አትጠብቁ በጣዖቶቻቸውም አትርከሱ።
19እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ! በትእዛዜ ሂዱ ፍርዴንም ጠብቁ አድርጓትም!
20በእናንተና በእኔ መካከል ምልክት እንዲሆኑና እኔም እግዚአብሔር አምላካችሁ እንደ ሆንሁ እንድታውቁ ሰንበታቴን ጠብቁ።"
21ነገር ግን ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸው ዐመፁብኝ። በሥርዓቴም አልሄዱም ወይም ሰው ቢፈጽመው በሕይወት የሚኖርባትን ፍርዴን አልጠበቁም። ሰንበታቴንም አረከሱ ስለዚህም በምድረ በዳ መዓቴን ላፈስባቸው ቍጣዬንም ልፈጽምባቸው ወሰንክ።
22ነገር ግን እጄን መለስሁ፥ በፊታቸውም ባወጣኋቸው በአሕዛብ ፊት ስሜ እንዳይረክስ ብዬ ስለ ስሜ ሠራሁ።
23ደግሞም ወደ አሕዛብ ልበትናቸው ፥ በአገሮችም መካከልም ለነቀፋ ላደርጋቸው በምድረ በዳ እጄን አንስቼ ማልሁባቸው። ፍርዴን አላደረጉምና
24ሥርዓቴንም ጥሰዋልና ሰንበታቴንም አርክሰዋልና ዓይናቸውም የአባቶቻቸውን ጣዖታቶች ተከትለዋልና ይህን ላደርግባቸው ወሰንኩ።
25ደግሞም መልካም ያልሆነውን ሥርዓት በሕይወት የማይኖሩበትንም ህግ ሰጠኋቸው።
26እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ እንዲያውቁ አጠፋቸው ዘንድ፥ ማኅፀን የሚከፍተውን በኩር ሁሉ በእሳት ባሳለፉ ጊዜ፥ በመባቸው አረከስኋቸው።
27ስለዚህ፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ ለእስራኤል ቤት ተናገር፥ እንዲህም በላቸው፥ 'ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፡ በዚህም ደግሞ አባቶቻችሁ ባደረጉት ዓመፅ አስቈጡኝ።
28እሰጣቸውም ዘንድ ወደ ማልሁላቸው ምድር ባገባኋቸው ጊዜ፥ በኮረብታ ላይ ያለውን የጣዖት ማምለኪያ ሁሉና ቅጠልማውንም ዛፍ ባዩ ጊዜ፥ በዚያ መሥዋዕታቸውን ሠዉ በዚያም የሚያስቈጣኝን ቍርባናቸውን አቀረቡ። በዚያም ደግሞ ጣፋጩን ሽታቸውን አደረጉ በዚያም የመጠጥ ቍርባናቸውን አፈሰሱ።
29እኔም፥ "እናንተ ወደ እርሱ የምትሄዱበት ኮረብታማ ሥፍራ ምንድር ነው?" አልኋቸው። እስከ ዛሬም ድረስ ስሙ ባማ ተብሎ ተጠርቶአል።
30ስለዚህ ለእስራኤል ቤት እንዲህ በላቸው፥ 'ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እንደ አባቶቻችሁ ልማድ ለምን ትረክሳላችሁ? ለምን እንደአመንዝራ የሚያጸይፍ ተግባር ታከናውናላችሁ?
31ቍርባናችሁን ስታቀርቡ፥ ልጆቻችሁንም በእሳት ስታሳልፉ፥ እስከ ዛሬ ድረስ በጣዖቶቻችሁ ትረክሳላችሁ። ታዲያ የእስራኤል ቤት ሆይ፥ ከእናንተስ ዘንድ እጠየቃለሁን? በህያውነቴ እምላለሁ ከእናንተ ዘንድ አልጠየቅም-ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
32እናንተ "እንጨትና ድንጋይ እንድሚያመልኩት ወገኖች እንደ ሌሎች አሕዛብ እንሁን" ብላችሁ ያሰባችሁት ሀሳብ ይፈጸማል።
33በህያውነቴ እምላለሁ በበረታች እጅና በተዘረጋች ክንድ በእናንተ ላይ በፈሰሰችም መዓት እነግሥባችኋለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር!
34ከአሕዛብም ዘንድ አወጣችኋለሁ ከተበተናችሁባትም አገር ሁሉ በበረታች እጅና በተዘረጋች ክንድ በፈሰሰችም መዓት እሰበስባችኋለሁ።
35ወደ አሕዛብም ምድረ በዳ አመጣችኋለሁ በዚያም ፊት ለፊት ከእናንተ ጋር እፋረዳለሁ።
36በግብጽ ምድረ በዳ በአባቶቻችሁ ላይ እንደፈረድኩ እንዲሁ በእናንተ ላይ እፋረዳለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
37ከበሬም በታች አሳልፋችኋለሁ ወደ ቃል ኪዳንም እስራት አገባችኋለሁ፤
38ከእናንተም መካከል ዓመፀኞችንና የበደሉኝን እለያለሁ። በእንግድነት ከኖሩባትም ምድር አወጣቸዋለሁ፥ ወደ እስራኤል ምድር ግን አይገቡም። እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ!
39ጌታ እግዚአብሔርም እንዲህ ይላል። እናንተ የእስራኤል ቤት ሆይ፥ እያንዳንዳችሁ ወደየጣዖቶቻችሁ ሂዱ፥ ከዚህም በኋላ እኔኔ መስማት ካልፈለጋችሁ እነርሱን አምልኩ። ነገር ግን ከእንግዲህ ወዲህ በቍርባናችሁና በጣዖቶቻችሁ ቅዱሱን ስሜን አታረክሱም።
40ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል- በቅዱሱ ተራራዬ፥ ከፍ ባለው በእስራኤል ተራራ ላይ፥ በዚያ የእስራኤል ቤት ሁሉ ሁላቸው በምድራቸው ያመልኩኛል። በዚያም ቍርባናችሁን በኵራታችሁንም የቀደሳችሁትንም ነገር ሁሉ በደስታ እቀበላለሁ።
41ከአሕዛብም ዘንድ ባወጣኋችሁ ጊዜ ከተበተናችሁባትም አገር ሁሉ በሰበሰብኋችሁ ጊዜ እንደ ጣፋጭ ሽታ እቀበላችኋለሁ፥ በአሕዛብም ፊት እቀደስባችኋለሁ።
42ለአባቶቻችሁም እሰጣት ዘንድ ወደ ማልሁላቸው ምድር ወደ እስራኤል አገር ባገባኋችሁ ጊዜ፥ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።
43በዚያም የረከሳችሁባትን መንገዳችሁንና ሥራችሁን ሁሉ ታስባላችሁ ስለ ሠራችሁትም ክፋት ሁሉ ራሳችሁን ትጸየፋላችሁ።
44ስለዚህም የእስራኤል ቤት ሆይ፥ እንደ ክፉ መንገዳችሁና እንደ ርኩስ ሥራችሁ ሳይሆን ስለ ስሜ ብዬ ይህን ባደረኩላችሁ ጊዜ፥ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
45የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፥
46"የሰው ልጅ ሆይ፥ ፊትህን ወደ ደቡብ አቅና በደቡብ ላይ ተናገር፤ በኔጌብ ዱር ላይ ትንቢት ተናገር
47ለኔጌብም ዱር፥ 'የእግዚአብሔርን ቃል ስማ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ በአንተ ውስጥ እሳት አነድዳለሁ። በውስጥህም ያለውን የለመለመውንና የደረቀውን ዛፍ ሁሉ ይበላል። የሚንበለበለው እሳትም አይጠፋም፤ ከደቡብም ጀምሮ እስከ ሰሜን ድረስ ያለው ገጽታ ሁሉ ይቃጠላል።
48እሳቱን ስለኩሰውና ሳይጠፋ በሚነድበት ጊዜ ሥጋ ለባሽ ሁሉ እኔ እግዚአብሔር እንደሆንኩ ያያል።'"
49እኔም፥ "ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፥ ወዮ! እነርሱ ስለ እኔ፥ "ይሄ ምሳሌን ብቻ ተናጋሪ አይደለም እንዴ?" ይላሉ አልሁ።