1የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
2"ስለ እስራኤል ምድር፥ 'አባቶች መራራ የወይን ፍሬ በሉ፥ የልጆችም ጥርሶች ጠረሱ' ብላችሁ የምትመስሉት ምሳሌ ምንድር ነው?
3በህያውነቴ እምላለሁ እንግዲህ ወዲህ ይህን ምሳሌ በእስራኤል የምትናገሩብት ሁኔታ አይኖርም ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
4እነሆ፥ ነፍስ ሁሉ የእኔ ነው! የአባት ነፍስ የእኔ እንደ ሆነች የልጅም ነፍስ የእኔ ናት! ኃጢአት የሚሰራ ሰው ይሞታል!
5ሰውም ጻድቅ ቢሆን ፍርድንና ቅን ነገርን ቢያደርግ፥
6በተራራም ላይ ባሉ የጣዖት አምልኮ ስፍራ ባይበላ ዓይኞቹንም ወደ እስራኤል ቤት ጣዖታት ባያነሣ የባልንጀራውንም ሚስት ባያረክስ በወር አበባ ላይ ወዳለች ሴት ባይቀርብ
7ሰውንም ባያስጨንቅ ለባለ ዕዳም መያዣውን ቢመልስ የሌባ ተቀባይ ባይሆን ከእንጀራውም ለተራበ ቢሰጥ የተራቈተውንም ቢያለብስ
8በአራጣ ባያበድር፥ የማይገባ ትርፍን ባይወስድ፥ ፍትህን ቢያደርግ፥ በሰውና በሰው መካከልም መተማመንን ቢፈጥር
9በትእዛዜም ቢሄድ፥ እውነትንም ለማድረግ ፍርዴን ቢጠብቅ፥ ይህ ሰው ጻድቅ ነው፤ ፈጽሞ በሕይወት ይኖራል! ይላል ጌታ እግዚአብሔር፦
10እርሱም ቀማኛና ደም አፍሳሽ ልጅ ከዚህም ሁሉ አንዳቸውን የሚያደርገውን ቢወልድ፥
11እርሱም ጻድቅ አባቱ የሠራውን ሁሉ ባይሠራ በተራራምላይ ባሉ የጣዖት አምልኮ ስፍራ ላይ ቢበላ የባልንጀራውንም ሚስት ቢያረክስ፥
12ድሀውንና ችግረኛውንም ቢያስጨንቅ ቢቀማም መያዣውንም ባይመልስ ዓይኖቹንም ወደ ጣዖታት ቢያነሣ ወይም ርኩስን ነገር ቢያደርግ፥
13በአራጣ ቢያበድር፥ የማይገባ ትርፍ ቢወስድ፥ በውኑ እርሱ በሕይወት ይኖራልን? በሕይወት አይኖርም! ይህን ርኵሰት ሁሉ አድርጎአልና ፈጽሞ ይሞታል ደሙም በላዩ ላይ ይሆናል።
14እነሆም፥ ልጅ ቢወልድ፥ እርሱም አባቱ የሠራውን ኃጢአት አይቶ ቢፈራ እንዲህም ባይሠራ፥
15በተራራ ባሉ የጣዖት አምልኮ ስፍራዎች ላይ ባይበላ ዓይኖቹንም ወደ እስራኤል ቤት ጣዖታት ባያነሣ የባልንጀራውንም ሚስት ባያረክስ፥
16ሰውንም ባያስጨንቅ መያዣውን ባይወስድ ባይቀማም ከእንጀራውም ለተራበ ቢሰጥ ለተራቈተውም ልብስን ቢያለብስ፥
17እጁንም ድሀን ከመበደል ቢመልስ፥ በአራጣ ባያበድር የማይገባ ትርፍንም ባይወስድ፤ ፍርዴንም ቢያደርግ በትእዛዜም ቢሄድ፥ እርሱ ፈጽሞ በሕይወት ይኖራል እንጂ በአባቱ ኃጢአት አይሞትም።
18አባቱ ግን ፈጽሞ በድሎአልና፥ ወንድሙንም ዘርፏልና፥ በሕዝቡም መካከል ክፉን ነገር አድርጎአልና እነሆ፥ እርሱ በበደሉ ይሞታል።
19እናንተ ግን፥ 'ልጅ የአባቱን ኃጢአት ስለ ምን አይሸከምም? ትላላችሁ። ልጅ ፍርድንና ቅን ነገርን ባደረገ ትእዛዜንም ሁሉ በጠበቀና ባደረገ ጊዜ ፈጽሞ በሕይወት ይኖራል!
20ኃጢአትን ያደረገ ሰው ይሞታል። ልጅ የአባቱን ኃጢአት አይሸከምም፥ አባትም የልጁን ኃጢአት አይሸከምም። የጻድቁ ጽድቅ በራሱ ላይ ይሆናል፥ የኃጢአተኛውም ኃጢአት በራሱ ላይ ይሆናል።
21ኃጢአተኛውም ካደረጋት ኃጢአት ሁሉ ቢመለስ ትእዛዜንም ሁሉ ቢጠብቅ ፍርድንና ቅን ነገርንም ቢያደርግ ፈጽሞ በሕይወት ይኖራል እንጂ አይሞትም።
22የበደለው በደል ሁሉ አይታሰብበትም በሠራው ጽድቅ በሕይወት ይኖራል።
23በውኑ ከመንገዱስ ቢመለስና በሕይወት ቢኖር እንጂ በኃጢአተኛ ሞት እደሰታለሁን? ይላል ጌታ እግዚአብሔር
24ጻድቁ ግን ከጽድቁ ቢመለስ ኃጢአትንም ቢሠራ ኃጢአተኛውም እንደሚያደርገው ርኵሰት ሁሉ ቢያደርግ፥ በሕይወት ይኖራልን? የሠራት ጽድቅ ሁሉ አትታሰብለትም ባደረገው ዓመፅና በሠራት ኃጢአት በዚያች ይሞታል።
25እናንተ ግን፥ 'የጌታ መንገድ የቀናች አይደለችም' ትላላችሁ። የእስራኤል ቤት ሆይ፥ እንግዲህ ስሙ! በውኑ መንገዴ የቀናች አይደለችምን? ይልቅስ የእናንተ መንገድ ያልቀናች አይደለችምን?
26ጻድቁ ከጽድቁ ቢመለስ፥ ኃጢአትንም በሠራ ጊዜ፥ በዚያም ቢሞት፥ እርሱ ባደረገው በደል ይሞታል።
27ኃጢአተኛውም ከሠራው ኃጢአት ቢመለስ ፍርድንና ቅን ነገርንም ቢያደርግ ነፍሱን ያድናል።
28አስቦ ከሠራው በደል ሁሉ ተመልሶአልና ፈጽሞ በሕይወት ይኖራል እንጂ አይሞትም።
29ነገር ግን የእስራኤል ቤት፥ 'የጌታ መንገድ የቀናች አይደለችም!' ይላል። የእስራኤል ቤት ሆይ፥ መንገዴ የቀናች ያልሆነው እንዴት ነው? የእናንተ መንገድስ የቀናች የሆነችው እንዴት ነው?
30የእስራኤል ቤት ሆይ፥ ስለዚህ በመካከላችሁ በእያንዳንዱ ሰው እንደ መንገዱ እፈርድበታለሁ! ይላል ጌታ እግዚአብሔር። ንስሐ ግቡ ኃጢአትም ዕንቅፋት እንዳይሆንባችሁ ከኃጢአታችሁ ሁሉ ተመለሱ።
31የበደላችሁትን በደል ሁሉ ከእናንተ ጣሉ አዲስ ልብና አዲስ መንፈስም ለእናንተ አድርጉ። የእስራኤል ቤት ሆይ፥ ስለ ምን ትሞታላችሁ?
32የምዋቹን ሞት አልፈቅድምና፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር ስለዚህ ተመለሱና በሕይወት ኑሩ።