1የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፣
2የሰው ልጅ ሆይ፥ በእንቈቅልሽ አጫውት እንዲህም ብለህ ለእስራኤል ቤት ምሳሌ ንገራቸው ፥
3ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ታላቅ ክንፍ ረጅምም ማርገብገቢያ ያለው ላባም የተሞላ፥ መልከ ዝንጕርጕር ታላቅ ንስር ወደ ሊባኖስ መጣ፥ የዛፍ ቅርንጫፍን ጫፍ ወሰደ።
4የቅርንጫፉን ጫፍ ወደ ከነዓንም ምድር ወሰደው በነጋዶችም ከተማ ተከለው።
5ከዚያም ምድር ዘር ወሰደ በፍሬያማ እርሻም ተከለው። በብዙም ውኃ አጠገብ እንደ አኻያ ዛፍ አኖረው።
6በበቀለም ጊዜ ቁመቱ ያጠረ አረጉም ወደ እርሱ የሚመለስ ሥሩም በበታቹ የነበረ ሰፊ ወይን ሆነ።
7ታላቅ ክንፍና ብዙ ላባም ያለው ሌላ ታላቅ ንስር ነበረ። እነሆም፥ ውሀ ያጠጣው ዘንድ ይህ ወይን ሥሩን ወደ እርሱ አዘነበለ አረጉንም ከተተከለበት ከመደቡ ወደ እርሱ ሰደደ።
8አረግም ያወጣ ፍሬም ያፈራ የከበረም ወይን እንዲሆን በመልካም ላይ በብዙም ውኃ አጠገብ ተተክሎ ነበር።
9ለህዝቡም እንዲህ በል፥ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በውኑ ይከናወንለት ይሆንን? ይደርቅስ ዘንድ፥ አዲስ የበቀለውስ ቅጠሉ ይጠወልግ ዘንድ ሥሩን አይነቅለውምን? ፍሬውንስ አይለቅመውምን? የትኛውም ጠንካራ ክንድ ወይም ብዙ ህዝብ ሥሩን ሊነቅል አይችልም።
10እነሆ፥ ከተተከል በኋላስ ይከናወንለት ይሆንን? የምሥራቅ ነፋስ ባገኘው ጊዜ ፈጽሞ አይደርቅምን? በተተከለበት መደብ ላይ ይደርቃል።
11የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
12"ለዓመፀኛ ቤት፥ 'የዚህ ነገር ትርጓሜ ምን እንደ ሆነ አታውቁምን? እነሆ፥ የባቢሎን ንጉሥ ወደ ኢየሩሳሌም መጣ፥ ንጉሥዋንና መኳንንቶችዋንም ማረከ፥ ወደ እርሱም ወደ ባቢሎን ወሰዳቸው።
13ከንጉሳዊያን ዘር የሆነውን ወስዶ ቃል ኪዳን ከእርሱ ጋር አደረገ አማለውም። የምድሪቱንም ኃያላን ወሰደ
14ይኸውም ቃል ኪዳኑን በመጠበቅ እንድትጸና እንጂ መንግሥቱ እንድትዋረድና ከፍ እንዳትል ነው።
15የኢየሩሳሌም ንጉስ ግን በእርሱ ላይ ሸፈተ ፈረሶችንና ብዙንም ሕዝብ ይሰጡት ዘንድ መልእክተኞችን ወደ ግብጽ ላከ። በውኑ ይከናወንለት ይሆንን? ይህንስ ያደረገ ያመልጣልን? ቃል ኪዳንንስ አፍርሶ ያመልጣልን?
16በህያውነቴ እምላለሁ! ባነገሠውና መሐላውን በናቀበቱ፥ ቃል ኪዳኑንም ባፈረሰበቱ ንጉሥ ምድር ይሞታል። በባቢሎን መካከል ይሞታል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፦
17የባቢሎን ሠራዊት ብዙዎችን ነፍሳት ለማስወገድ አፈርን በደለደሉ ምሽግም በሠሩ ጊዜ፥ ፈርዖን ከብዙ ሠራዊቱና ከታላቁ ጉባኤው ጋር የኢየሩሳሌምን ንጉሥ በሰልፍ አይረዳውም።
18ይህም የሚሆነው መሐላውን ንቆ ቃል ኪዳኑንን በማፍረሱ ነው። ለቃል ኪዳን እጁን ዘርጋ፥ ነገር ግን እነዚህን ነገሮች አደረገ። ስለዚህ አያመልጥም።
19ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በህያውነቴ እምላለሁ የናቀው መሐላዬን ያፈረሰስ ቃል ኪዳኔን አይደለምን? ስለዚህ ቅጣትን በርሱ ላይ አመጣለሁ!
20መረቤንም በእርሱ ላይ እዘረጋለሁ በማጥመጃ መረቤም ይያዛል። ወደ ባቢሎንም አመጣዋለሁ በእኔም ላይ ስላደረገው ዓመፅ በዚያ በእርሱ ላይ እፈርዳለሁ።
21ጭፍሮቹም ሁሉ በሰይፍ ይወድቃሉ፥ የቀሩትም ሁሉ በየአቅጣጫው ይበታተናሉ። እኔም እግዚአብሔር እንደሆንኩ ይህም እንደሚሆን እንደ ተናገርሁ ታውቃላችሁ!'
22ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ 'እኔ እራሴ ከረጅሙ ዝግባ ጫፍ ላይ ቀንበጥን እወስዳለሁ ከለምለም ቅርንጫፎቹ አርቄ እተክለዋለሁ። ቀንጥቤ እኔ እራሴ በረጅምና በታላቅ ተራራ ላይ እተክለዋለሁ!
23ከፍ ባለው በእስራኤል ተራራ ላይ እተክለዋለሁ፥ ቅርንጫፎችም ያወጣል ፍሬም ያፈራል የከበረም ዝግባ ይሆናል በበታቹም በክንፍ የሚበርሩ ወፎች ሁሉ ያርፋሉ፥ በቅርንጫፎቹም ጥላ ውስጥ ጎጆአቸውን ይሰራሉ።
24በዚያን ጊዜ የዱር ዛፎች ሁሉ እኔ እግዚአብሔር እንደሆንኩ ያውቃሉ። ረጅሙን ዛፍ ዝቅ አደርጋለሁ፥ አጭሩንም ዛፍ ከፍ አድርጋለሁ! የለመለመውንም ዛፍ አደርቃለሁ፥ የደረቀውንም ዛፍ አለመልማለሁ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ይህ እንደሚሆን ተናግሬአለሁ እኔም አድርጌዋለሁ።