መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ሕዝቅኤል 16

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
2የሰው ልጅ ሆይ፥ ለኢየሩሳሌም ርኵሰትዋን አስታውቃት፥
3እንዲህም በል፣ "ጌታ እግዚአብሔር ለኢየሩሳሌም እንዲህ ይላል፡ ዘርሽና ትውልድሽ ከከነዓን ምድር ነው አባትሽ አሞራዊ ነበረ እናትሽም ኬጢያዊት ነበረች።
4በተወለድሽ ጊዜ እናትሽ እትብትሽን አልቆረጠችም ፣ በውኃ አላጠበችሽም ወይም በጨው አላሸችሽም፣ በጨርቅም አልጠቀለለችሽም።
5ከእነዚህ ነገሮች አንዱን እንኳ ሊያደርግልሽ ማንም አልራራልሽም! በተወለድሽበት ቀን በሜዳ ላይ ተጣልሽ።
6እኔ ግን በአንቺ ዘንድ ባለፍሁ ጊዜ በደምሽም ውስጥ ተለውሰሽ አየሁ፤ ስለዚህም በደምሽ እንዳለሽ "በሕይወት ኑሪ!" አልሁሽ።
7በእርሻ ላይ እንዳለ ቡቃያ አሳደግሁሽ። አንቺም አደግሽ ታላቅም ሆንሽ፥ በእጅጉም አጌጥሽ። ጡቶችሽም አጐጠጐጡ ጠጕርሽም አደገ፥ ነገር ግን ዕርቃንሽን ሆነሽ፥ ተራቍተሽም ነበር።
8እንደገና በአንቺ ዘንድ ባለፍሁና ባየሁሽ ጊዜ፥ እነሆ፥ ጊዜሽ የፍቅር ጊዜ ነበረ እኔም መጐናጸፊያዬን በላይሽ ዘርግቼ እራቁትነትሽን ሸፈንኩ።ከዚያም ማልሁልሽ ከአንቺም ጋር ቃል ኪዳን ገባሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፥ አንቺም ለእኔ ሆንሽ።
9በውኃም አጠብሁሽ ከደምሽም አጠራሁሽ በዘይትም ቀባሁሽ።
10በወርቅ የተንቆጠቆጠ ልብስም አለበስሁሽ ከቆዳ የተሰራ ጫማ አደረግሁልሽ፤ በጥሩ በፍታ አስታጠቅሁሽ በሐርም ከደንሁሽ።
11በጌጥም አስጌጥሁሽ በእጅሽም ላይ አንባር በአንገትሽም ላይ ድሪ አደረግሁልሽ።
12በአፍንጫሽም ቀለበት በጆሮሽም ጕትቻ በራስሽም ላይ የክብር አክሊል አደረግሁ።
13በወርቅና በብር አጌጥሽ፤ ልብስሽም ጥሩ በፍታና ሐር ወርቀ ዘቦም ነበረ፤ አንቺም መልካምን ዱቄትና ማርን ዘይትንም በላሽ እጅግ በጣም ውብ ነበርሽ ከዚያም ንግሥት ሆንሽ።
14ባንቺ ላይ ካኖርኋት ከክብሬ የተነሣ ውበትሽ ፍጹም ነበረና ዝናሽ በአሕዛብ መካከል ወጣ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፦
15ነገር ግን በውበትሽ ታምነሻል ስለ ዝናሽም አመንዝረሻል ምንዝርናሽንም ከመንገድ አላፊ ሁሉ ጋር አበዛሽ። የእነርሱም ንብረት ሆንሽ!
16ከልብስሽም ወስደሽ በኮረብቶች ላይ በዝንጕርጕር ልብስ ያስጌጥሻቸውን መስገጆች ለራስሽ ሠራሽ በዚያም ገለሞትሽ። እንዲህም ያለ ነገር ከአሁን በፊት አልነበረም፥ ከእንግዲህም ወዲያ አይሆንም።
17ከሰጠሁሽም ከወርቄና ከብሬ የተሠራውን የክብርሽን ዕቃ ወስደሽ የወንድ ምስሎች ለራስሽ አድርገሻል አመንዝረሽባቸውማል።
18ወርቀዘቦውን ልብስሽንም ወስደሽ ደረብሽላቸው፥ ዘይቴንና ዕጣኔንም በፊታቸው አኖርሽ።
19የሰጠሁሽንም እንጀራዬን ያበላሁሽንም መልካሙን ዱቄትና ዘይቱን ማሩንም ጣፋጭ ሽታ አድርገሽ በፊታቸው አኖርሽ፥ ይህ በእርግጥ ሆኖአል! ይላል ጌታ እግዚአብሔር፦
20ለእኔም የወለድሻቸውን ወንዶችና ሴቶች ልጆችሽን ወስደሽ መብል ይሆኑ ዘንድ ለጣዖታቱ ሠዋሽላቸው። በውኑ የግልሙትና ተግባርሽ እንደ ቀላል የሚታይ ነገር ነውን?
21ልጆቼን አረድሽ ለእነርሱም የሚቃጠል መስዋዕት አድርገሽ አቀረብሽ
22በዚህ ሁሉ የርኵሰትና የግልሙትና ተግባርሽ ወቅት ዕርቃንሽን ተራቍተሽ በደምሽም ተለውሰሽ የነበርሽበትን የሕፃንነትሽን ወራት አላሰብሽም።
23ወዮ! ወዮልሽ! ይላል ጌታ እግዚአብሔር
24ከክፋትሽም ሁሉ በኋላ የጣዖት ማምለኪያ ስፍራ፥ በየአደባባዩም አጸዶችን ሠራሽ።
25በየመንገዱ ራስ ከፍ የማምለኪያ አጸዶችን ሠራሽ፥ ለመንገድ አላፊም ሁሉ እግርሽን በመግለጥና በርካታ የግልሙትና ተግባራት በመፈጸም ውበትሽን አረከስሽ ።
26እጅግ የሴሰኝነት ፍላጎት ካላቸው ከጐረቤቶችሽ ከግብጻውያን ጋር አመነዘርሽ፥ እኔንም ታስቈጭ ዘንድ ግልሙትናሽን አበዛሽ።
27ስለዚህ፥ በእጄ አደቅሻለሁ እህልንም ከአንቺ ዘንድ አጠፋለሁ። ለሚጠሉሽም ከክፉ ምኞትሽ የተነሣ ለውርደት ለሚዳርጉሽ ለፍልስጥኤም ሴቶች ልጆች ፈቃድ አሳልፌ ሰጥቼሻለሁ።
28አልጠግብ ብለሽ ከአሦራውያን ጋር ደግሞ ገለሞትሽ። ያም ሆኖ ግን አሁንም አልበቃሽም።
29እስከ ነጋዴዎች ምድር እስከ ከላውዴዎን ድረስ ግልሙትናሽን አበዛሽ። አሁንም ግን ገና አልጠገብሽም።
30የማታፍረውን የጋለሞታን ሥራ ሁሉ ሠርተሻልና ልብሽ ምንኛ ደካማ ነው? ይላል ጌታ እግዚአብሔር፦
31በየመንገዱ ራስ የምንዝርናሽን ስፍራ ሠርተሻል በየአደባባዩም ከፍ ያለውን ቦታሽን አድርገሻል። ዋጋዋን እንደምትንቅ እንደ ጋለሞታ አልሆንሽም።
32አንቺ ዘማዊ ሴት በባልሽ ፋንታ ሌሎች እንግዳ ሰዎች ተቀበልሽ።
33ሰዎች ለጋለሞቶች ሁሉ ዋጋ ገንዘብ ይከፍላሉ አንቺ ግን ለውሽሞችሽ ገንዘብ ትከፍያለሽ፥ ከአንቺም ጋር ለማመንዘር ከአካባቢው ሁሉ ወድ እንቺ እንዲምጡ ማባበያ ትሰጫቸዋለሽ።
34ግልሙትናሽ ከሌሎች ሴቶች ፈጽሞ የተለየ ነው፥ ምክንያቱም ማንም ከአንቺ ጋር ልትኛ ብሎ የሚጠይቅሽ የለም። ይልቁኑ አንቺ ትከፍያቸዋለሽ እንጂ የሚክፍልሽ የለም።
35ስለዚህ፥ ጋለሞታ ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ስሚ!
36ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ከውሽሞችሽና ከአጽያፊ ጣዖታትሽ ጋር ባደረግሽው ግልሙትና አማካኝነት ክፉ ምኞትሽን በማፍሰስሽና ኀፍረተ ሥጋሽንም በመግለጥሽ እንዲሁም ለጣዖታትሽ በሰጠሻቸው በልጆችሽ ደም ምክንያት፥
37እነሆ፥ ከእነርሱ ጋር ደስ ያለሽን የወደድሻቸውንም ውሽሞችሽና የጠላሻቸው ሁሉ ከሁሉም አቅጣጫ በአንቺ ላይ እንዲነሱ እሰበስባቸዋለሁ። እራቁትነትሽን እንዲያዩ በፊታቸው ኀፍረተ ሥጋሽን እገልጣለሁ።
38ስለምንዝርናሽና ደም ማፍሰስሽ እቀጣሻለሁ፥ በቁጣዬና በቅንዓቴ ደም መፋሰስን አመጣብሻለሁ።
39በእጃቸውም አሳልፌ እሰጥሻለሁ፥ የምንዝርናሽንም ስፍራ ያፈርሳሉ ከፍ ያለውንም ቦታሽን ይገለብጣሉ ልብስሽንም ይገፉሻል የክብርሽንም ጌጥ ይወስዳሉ፥ ዕርቃንሽን አድርገው ዕራቁትሽን ይተዉሻል።
40ህዝብንም ያስነሱብሻል በድንጋይም ይወግሩሻል፥ በሰይፋቸውም ይሰነጥቁሻል።
41ቤቶችሽንም በእሳት ያቃጥላሉ በብዙም ሴቶች ፊት ብዙ ቅጣቶችን ይፈጽሙብሻል፥ ግልሙትናሽንም አስተውሻለሁ፥ ከእንግዲህ ለእነርሱ ዋጋ አትሰጭም!
42መዓቴንም በአንቺ ላይ እጨርሳለሁ ቅንዓቴም ከአንቺ ይርቃል፥ እኔም እረካለሁ፣ከዚያ በኋላም አልቈጣም።
43በእንዚህ ነገርች ሁሉ ስታስቆጪኝ የሕፃንነትሽን ወራት አላሰብሽምና፥ ስለዚህ፥ እነሆ፥ እኔ እራሴ ለፈጸምሽው ጥፋት ቅጣትን በአንቺ ላይ አመጣለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፥ ከዚህ በኋላ በአስነዋሪ መንገድሽ በክፋት አትሄጂም።
44እነሆ፥ በምሳሌ የሚናገር ሁሉ፥ "ልክ እንደ እናቲቱ ሴት ልጂቱ እንደዛው ናት" እያለ ምሳሌ ይመስልብሻል።
45አንቺ ባልዋንና ልጆችዋን የጠላች የእናትሽ ልጅ ነሽ፤ ደግሞም ባሎቻቸውንና ልጆቻቸውን የጠሉ የእኅቶችሽ እኅት ነሽ። እናታችሁ ኬጢያዊት ነበረች አባታችሁም አሞራዊ ነበረ።
46ታላቂቱም እኅትሽ ከሴቶች ልጆችዋ ጋር በስተ ሰሜን የምትኖረው ሰማርያ ናት ታናሺቱም እኅትሽ ከሴቶች ልጆችዋ ጋር በስተ ምዕራብ የምትኖረው ሰዶም ናት።
47አንቺ ግን በመንገዳቸው አልሄድሽም እንደ ርኵሰታቸውም አላደረግሽም የእነርሱ ድርጊት ለአንቺ ጥቂት ነበረና። ይልቁኑ በመንገድሽ ሁሉ ከእነርሱ የከፋሽ ሆንሽ።
48በህያውነቴ እምላለሁ አንቺና ሴቶች ልጆችሽ ያደርጋችሁትን ክፋት ያህል ሰዶምና ሴቶች ልጆችዋ አላደረጉም! ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
49እነሆ፥ የእኅትሽ የሰዶም ኃጢአት ይህ ነበረ፡ በሥራ ፈትነት የበረታች፣ ስለምንም ነገር የማይሰማት ግድ የለሽት ነበረች። የችግረኛውንና የድሀውንም እጅ አላበረታችም ።
50ትዕቢተኛ ነበረች በፊቴም ርኩስ ነገርችን አደረገች፣ እንዳየሽውም አጠፋኋቸው።
51ሰማርያም የኃጢአትሽን እኵሌታ እንኳ አልሠራችም ፤ አንቺ ግን ከእኅቶችሽ ይልቅ ርኵሰትሽን አበዛሽ፥ በሠራሽውም ርኵሰት ሁሉ እህቶችሽ ካንቺ እንድሚሻሉ አሳየሽ።
52አሁንም ለእኅቶችሽ ስለ ፈረድሽ እፍረትሽን ተሸከሚ ከእነርሱ የባሰ ኃጢአት ሠርተሻልና ከአንቺ ይልቅ የተሻሉ ሆነው ታይተዋል። እህቶችሽ ካንቺ እንድሚሻሉ በማሳየትሽ እፈሪ ።
53የሰዶምና የሴቶች ልጆችዋን ምርኮ፥ የሰማርያንና የሴቶች ልጆችዋንም ምርኮ እመልሳለሁ፤ ነገር ግን የአንቺ ምርኮ በእነርሱ መካከል ይሆናል።
54በእዚህም ነገሮች ቀመር እፍረትሽን ታሳዪአለሽ ስለ አደረግሽውም ሁሉ ታፍሪያለሽ፣ በዚህም ምክንያት ለእነርሱ መጽናኛ ትሆኚያለሽ።
55እኅቶችሽም ሰዶምና ሴቶች ልጆችዋ ወደ ቀድሞ ሁኔታቸው ይመለሳሉ፥ ሰማርያና ሴቶች ልጆችዋም ወደ ቀድሞ ሁኔታቸው ይመለሳሉ። ከዚያም አንቺና ሴቶች ልጆችሽ ወደ ቀድሞ ሁኔታችሁ ትመለሳላችሁ።
56ኩሩ በነበርሽ ጊዜ ስለ እኅትሽ ሰዶም ተናግረሽ አታውቂም ነበር፥
57ክፋትሽ ከመገለጡ በፊትማለት ነው። አሁን ግን ለኤዶም ሴቶች ልጆችና በጎረቤቶችዋ ላሉ የፍሊስጤማውያን ልጆች ሁሉ፥ የውርደት ምሳሌ ሆነሻል። ሰው ሁሉ ይንቅሻል።
58ምንዝርነትሽንና ርኵስነትሽን ይገለጣል ፥ ይላል እግዚአብሔር፦
59ጌታ እግዚአብሔርም እንዲህ ይላል። ቃል ኪዳንን ለማፍረስ መሐላን በሚንቅ ሁሉ ላይ የማደርገውን በአንቺም ላይ አደርጋለሁ።
60ነገር ግን በሕፃንነትሽ ወራት ከአንቺ ጋር ያደረግሁትን ቃል ኪዳኔን እኔ እራሴ አስባለሁ የዘላለምንም ቃል ኪዳን ከአንቺ ጋር እገባለሁ።
61እኅቶችሽንም ታላቂቱንና ታናሺቱን በተቀበልሽ ጊዜ መንገድሽን ታስቢያለሽ ታፍሪማለሽ። ለአንቺም ልጆች ይሆኑ ዘንድ እሰጣቸዋለሁ፥ ይህን የማደርገው ግን ስለ ቃል ኪዳንሽ አይደለም።
62ቃል ኪዳኔን ከአንቺ ጋር አጸናለሁ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቂያለሽ!
63በዚህም ምክንያት ስላደረግሽውም ሁሉ ይቅር ባልሁሽ ጊዜ፥ ያደርግሽውን ሁሉ አስበሽ ታፍሪያለሽ ከዚያም ወዲያ ለምናገር አፍሽን አትከፍቺም፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፦
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።