1ከዚያም በኪሩቤል ራስ ላይ ወደ ነበረው ጠፈር ተመለከትኩ። በላያቸው እንደ ሰንፔር ድንጋይ ያለ እንደ ዙፋን የሚመስል መልክ ተገለጠ።
2እግዚአብሔርም በፍታም የለበሰውን ሰው "በመንኰራኵሮች መካከል ከኪሩብ በታች ግባ፥ ከኪሩቤልም መካከል ካለው እሳት ፍም እጆችህን ሙላ በከተማይቱም ላይ በትነው" አለው። ሰውዬውም እያየሁት ገባ።
3ሰውዬውም ሲገባ ኪሩቤል በቤቱ ቀኝ በኩል ቆመው ነበር፥ ደመናም ውስጠኛውን አደባባይ ሞላው።
4የእግዚአብሔር ክብርም ከኪሩቤል ወጥቶ በቤቱ መድረክ ላይ ቆመ፤ ቤቱም በደመናው ተሞላ፥ አደባባዩም በእግዚአብሔር ክብር ፀዳል ተሞላ።
5ሁሉንም የሚችል አምላክ እንደሚናገረው ያለ ጽምፅ እንዲሁ የኪሩቤል ክንፎችን ድምፅ ክውጭው አደባባይ ሰማሁ።
6እግዚአብሔርም በፍታ የለበሰውን ሰው "ከመንኰራኵሮች ከኪሩቤል መካከል እሳት ውሰድ" ብሎ ባዘዘው ጊዜ ሰውዬው ገብቶ በአንደኛው መንኰራኵር አጠገብ ቆመ።
7ኪሩብም ከኪሩቤል መካከል እጁን በኪሩቤል መካከል ወዳለው እሳት ዘርግቶ ከዚያ ወሰደ፥ በፍታም በለበሰው ሰው እጅ አኖረው እርሱም ይዞ ወጣ።
8በኪሩቤልም ከክንፎቻቸው በታች የሰው እጅን መሳይ አየሁ።
9እኔም አየሁ፥ እነሆም፥ በኪሩቤል አጠገብ አራት መንኰራኵሮች ነበሩ አንዱ መንኰራኵር በአንዱ ኪሩብ፥ አንዱ መንኰራኵር በአንዱ ኪሩብ አጠገብ ነበረ። የመንኰራኵሮቹም መልክ እንደ ቢረሌ ድንጋይ ነበረ።
10የአራቱም መልክ አንድ ይመስል ነበር፥ መልካቸውም በመንኰራኵር ውስጥ እንዳለ መንኰራኵር ነበረ።
11ሲንቀሳቀሱም ወደየትኛውም አቅጣጫ ይሄዱ ነበር፤ ፊት ለፊት ስለሚሄዱ ሲሄዱ አይገላመጡም ነበር። ሲሄዱም አይገላመጡም ነበር።
12ሰውነታቸው ሁሉ ማለትም ጀርባቸው፣ እጃቸውና ክንፋቸው በዓይን ተሞልቶ ነበር፣ አራቱ መንኰራኵሮችም ዙሪያቸውን በዓይኖች ተሞልተው ነበር።
13መንኰራኵሮችም እኔ እየሰማሁ "ተሽከርካሪዎች" ተብለው ተጠሩ።
14ለእያንዳንዱም አራት አራት ፊት ነበሩት አንደኛው ፊት የኪሩብ ፊት፥ ሁለተኛውም የሰው ፊት፥ ሦስተኛው የአንበሳ ፊት፥ አራተኛውም የንስር ፊት ነበረ።
15ከዚያም ኪሩቤል ማለትም በኮቦር ወንዝ ያየኋቸው ህያዋን ፍጥረታት ከፍ ከፍ አሉ
16።ኪሩቤል በተንቀሳቀሱ ጊዜ ሁሉ መንኰራኵሮቹ በአጠገባቸው ይሄዱ ነበር፤ ኪሩቤልም ከምድር ከፍ ከፍ ይሉ ዘንድ ክንፎቻቸውን ሲዘረጉ መንኰራኵሮች ደግሞ ከአጠገባቸው ፈቀቅ አይሉም ነበር።
17የህያዋኑ ፍጥረታት መንፈስ በመንኰራኵሮች ውስጥ ስለነበረ ኪሩቤል ሲቆሙ መንኮራኩሮችመ ይቆሙ ነበር፥ ከፍ ከፍ ሲሉም መንኮራኩሮቹም ከእነርሱ ጋር ከፍ ከፍ ይሉ ነበር።
18የእግዚአብሔርም ክብር ከቤቱ መድረክ ላይ ወጥቶ በኪሩቤል ላይ ቆመ።
19ኪሩቤልም ክንፎቻቸውን ዘረጉ እኔም እያየሁ ከምድር ከፍ ከፍ አሉ በወጡም ጊዜ መንኰራኵሮች በአጠገባቸው እንደዚያው አደረጉ። በእግዚአብሔርም ቤት በምሥራቁ በር መግቢያ ቆሙ፥ የእስራኤልም አምላክ ክብር በላያቸው ወረደ።
20እነኚህም በኮበር ወንዝ ከእስራኤል አምላክ በታች ያየኋቸው ህያዋን ፍጥረታት ስለነበሩ ኪሩቤልም እንደ ነበሩ አውቄ ነበር።
21ለእያንዳንዱ አራት አራት ፊትና አራት አራት ክንፍ ነበሩት፥ የሰውም እጅ አምሳያ ከክንፎቻቸው በታች ነበረ።
22ፊቶቻቸውም በኮቦር ወንዝ በራዕይ ያየኋቸውን ፊቶች ይመስሉ ነበር ፣ እያንዳንዱም አቅንቶ ወደ ፊት ይሄድ ነበር።