መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ዘጸአት 5

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1እነዚህ ነገሮች ከሆኑ በኋላ፣ ሙሴና አሮን ወደ ፈርዖን ሄደው፣ እንደዚህ አሉ፤ «የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፡- ‹በምድረ በዳው ለእኔ በዓል እንዲያደርጉ ሕዝቤን ልቀቅ፡፡»›
2ፈርዖንም፣ «እግዚአብሔር ማን ነው? ቃሉን የምሰማው፣ እስራኤልንስ የምለቅ ለምንድን ነው? እግዚአብሔርን አላውቀውም፤ እስራኤልንም አልለቅም» አለ፡፡
3ሙሴና አሮንም፣ «የዕብራውያን አምላክ ከእኛ ጋር ተገናኝቶአል፡፡ በመቅሠፍትና በሰይፍ እንዳይመታን፣ ወደ ምድረ በዳው የሦስት ቀን ጕዞ እንድናደርግና ለእግዚአብሔር እንድንሠዋ ፍቀድልን» አሉት፡፡
4የግብፅ ንጉሥ ግን፣ «አንተ ሙሴ አንተም አሮን! ሕዝቡን ሥራቸውን አስፈትታችሁ የምትወስዷቸው ለምንድን ነው? ወደ ሥራችሁ ሂዱ» አላቸው፡፡
5እንዲህ አላቸው፤ «በምድራችን አሁን ብዙ ዕብራውያን አሉ፤ እናንተም ሥራ ታስፈቷቸዋላችሁ፡፡»
6በዚያው ቀን ፈርዖን ለሕዝቡ አሠሪዎችና ተቈጣጣሪዎች ትእዛዝ ሰጠ፡፡ እንዲህም አለ፤
7«እንደ ቀድሞው፣ ከእንግዲህ ወዲያ ለሸክላ ሥራ ጭድ አታቅርቡ፡፡ እነርሱ ራሳቸው ይሂዱና ጭድ ይሰብስቡ፡፡
8ሆኖም በፊት የሚሠሩትን አንድ ዐይነት የሸክላ ቊጥር አሁንም ሠርተው እንዲያቀርቡ ማድረግ አለባችሁ፡፡ ከዚያ ያነሰ አትቀበሉ፤ ምክንያቱም ሰነፎች ናቸው፡፡ ‹እንሂድ ፍቀድልንና ለአምላካችን እንሠዋ› እያሉ የሚጮኹትም ለዚህ ነው፡፡
9እንዲተጉና ለማይረባ ንግግር ትኵረት እንዳይሰጡ ሥራውን ጨምራችሁ አክብዱባቸው፡፡»
10ስለዚህ የሕዝቡ አሠሪ አለቆችና ተቈጣጣሪዎች ወጥተው ሄዱ፤ ለሕዝቡም ነገሯቸው፡፡ እንዲህም አሉ፤ «ፈርዖን የሚለው ይህ ነው፡- ‹ከእንግዲህ ወዲያ ምንም ጭድ አልሰጣችሁም፡፡
11ሂዱና ማግኘት ከምትችሉበት ፈልጋችሁ አምጡ፤ የሥራችሁ መጠንም አይቀላለም፡፡»
12ሕዝቡ በጭድ ፈንታ ገለባ ለመሰብሰብ በግብፅ ምድር ሁሉ ተሠራጩ፡፡
13አለቆቹ፣ «ጭድ በሚቀርብላችሁ ጊዜ የምትሠሩትን ሥራችሁን ጨርሱ» ይሏቸውና ያስጠነቅቋቸው ነበር፡፡»
14ፈርዖን የመደባቸው አሠሪ አለቆች የሠራተኞች ተቈጣጣሪ ያደረጓቸውን እስራኤላውያን ኀላፊዎች ገረፏቸው፡፡ አሠሪ አለቆቹ፣ «በፊት ታደርጉት እንደ ነበረው፣ ትናንትናም ዛሬም የሚጠበቅባችሁን ሸክላ በሙሉ ሠርታችሁ ያላቀረባችሁ ለምንድን ነው?» እያሉ ይጠይቋቸው ነበር፡፡
15እስራኤላውያን ተቈጣጣሪዎቹም ወደ ፈርዖን መጥተው አቤቱታ አቀረቡ፡፡ እንደዚህም አሉት፤ «ባሪያዎችህን በዚህ መንገድ ለምን እንድንኖር ታደርጋለህ?
16ጭድ አይሰጡንም፤ ነገር ግን አሁንም ‹ሸክላ ሥሩ!› ይሉናል፡፡ እኛ ባሪያዎችህ ተገርፈናልም፤ ስሕተቱ ግን የገዛ ሕዝብህ ነው፡፡»
17ግን እንዲህ አለ፤ «እናንተ ሰነፎች! እናንተ ሰነፎች! ‹ለእግዚአብሔር እንድንሠዋ ፍቀድልን› ትላላችሁ፡፡
18ወደ ሥራ ተመለሱ፡፡ አንዳችም ጭድ አይሰጣችሁም፤ ነገር ግን አሁንም ያንኑ የሸክላ ቊጥር መሥራት አለባችሁ፡፡»
19«የየቀኑን የሸክላ ቊጥር መቀነስ የለባችሁም» የሚለው ሲነገራቸው፣ እስራኤላውያን ተቈጣጣሪዎች ችግር ውስጥ እንደ ነበሩ አስተዋሉ፡፡
20ከፈርዖን ዘንድ ሲወጡ፣ ከቤተ መንግሥቱ ውጭ ቆመው ከነበሩት ከሙሴና ከአሮን ጋር ተገናኙ፡፡
21ለሙሴና ለአሮንም እንዲህ አሏቸው፣ «እግዚአብሔር ይይላችሁ፣ ይፍረድባችሁም፤ ምክንያቱም በፈርዖንና በአገልጋዮቹ ፊት አስጸያፊዎች እንድንሆን አድርጋችሁናል፡፡»
22ወደ እግዚአብሔር ተመልሶ፣ «ጌታ ሆይ፣ በዚህ ሕዝብ ላይ መከራ እንዲደርስበት ያደረግህ ለምንድን ነው? እኔንስ ቀድሞውኑ ለምን ላክኸኝ?
23ስም ልነግረው ወደ ፈርዖን ከመጣሁበት ጊዜ ጀምሮ፣ በዚህ ሕዝብ ላይ መከራ አምጥቶአል፤ አንተም ሕዝብህን ከቶ ነጻ አላወጣኸውም» አለው፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።