መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

አስቴር 9

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1አዳር ተብሎ በሚጠራው በአሥራ ሁለተኛው ወር፥ በአሥራ ሦስተኛውም ቀን የንጉሡ ሕግና ዐዋጅ ተግባራዊ በሚደረግበት፥ የአይሁድ ጠላቶች ሊያጠፏቸው ተስፋ ባደረጉበት ቀን ነገሩ ተቀየረ። አይሁዶች በሚጠሏቸው ላይ የበላይነትን አገኙ።
2አይሁድ ሊያጠፏቸው በሞከሩት ላይ እጆቻቸውን ለማንሣት ከንጉሥ አርጤክስስ አውራጃዎች ሁሉ ወደ ከተሞቻቸው ተሰበሰቡ። እነርሱን መፍራት በሕዝብ ሁሉ ላይ ወድቆ ስለነበረ ማንም ሊቃወማቸው አልቻለም።
3የአውራጃዎቹ አለቆች፥ የአውራጃ ገዢዎች፥ መኳንንቶችና የንጉሡ አስተዳዳሪዎች መርዶክዮስን በመፍራት ተይዘው ስለነበር አይሁድን አገዟቸው።
4መርዶክዮስ በንጉሡ ቤት ታላቅ ነበር፥ ዝናውም በአውራጃዎቹ ሁሉ ተሰራጨ፥ መርዶክዮስ የተባለውም ሰው ታላቅ ሆነ።
5አይሁድም ጠላቶቻቸውን በሰይፍ አጠቋቸው፥ ገደሏቸው፥ አጠፏቸውም፥ በእነዚያ ይጠሏቸው በነበሩት ላይ ደስ ያሰኛቸውን አደረጉባቸው።
6አይሁድ በራሱ በሱሳ ግንብ አምስት መቶ ሰዎችን ገደሉ፥ አጠፉም።
7የአይሁድ ጠላት የሐመዳቱን ልጅ
8የሐማን አሥሩን ወንዶች ልጆቱን፥ ፓርሻንዳታን፥ ደልፎንን፥ አስፓታን፥
9ፖራታን፥ አዳልያን፥ አሪዳታን፥
10ፓርማሽታን፥ አሪሳይን፥ አሪዳይንና ዋይዛታን ገደሉ። ነገር ግን ምንም ዝርፊያ አልፈጸሙም።
11በተመሸገችው ከተማ፥ በሱሳ፥ በዚያን ቀን የተገደሉት ሰዎች ብዛት ለንጉሡ ተነገረው።
12ንጉሡም ንግሥት አስቴርን፥ "አይሁድ አሥሩን የሐማ ወንዶች ልጆች ጨምሮ በሱሳ ከተማ ውስጥ አምስት መቶ ሰዎችን ገደሉ። በቀሩት የንጉሡ አውራጃዎች ምን አድርገው ይሆን? አሁን የምትለምኚው ምንድነው? እርሱም ይሰጥሻል። የምትጠይቂውስ ምንድነው? እርሱም ይደረግልሻል" አላት።
13አስቴርም፥ "ንጉሡን ደስ የሚለው ከሆነ፥ በሱሳ የሚገኙ አይሁዶች ዛሬ ያደረጉትን ነገም ደግሞ እንዲያደርጉ ይፈቀድላቸው፥ አሥሩ የሐማ ልጆች ሬሳም በመስቀያ ይሰቀል" አለችው።
14ስለዚህ ንጉሡ ይህ እንዲፈጸም አዘዘ። ዐዋጁም በሱሳ ተሰራጨ፥ አሥሩን የሐማ ወንዶች ልጆች ሰቀሏቸው።
15በአዳር ወር በአሥራ አራተኛው ቀን በሱሳ ይኖሩ የነበሩ አይሁድ አንድ ላይ ተሰብስበው ሦስት መቶ ተጨማሪ ሰዎችን ገደሉ፥ እጆቻቸውን ግን ለመበዝበዝ አልዘረጉም።
16በንጉሡ አውራጃዎች ይኖሩ የነበሩት፥ የቀሩት አይሁድ ሕይወታቸውን ለመከላከል በአንድ ላይ ተሰባሰቡ፥ ይጠሏቸው የነበሩትን ሰባ አምስት ሺህ ሰው ገደሉ፥ ከጠላቶቻቸውም ዐረፉ። ነገር ግን ወደ ገደሏቸው ሰዎች ጠቃሚ ቁሳቁስ እጆቻቸውን አልዘረጉም።
17በአዳር ወር በአሥራ ሦስተኛው ቀን ይህ ሆነ፥ በአሥራ አራተኛው ቀን ዐረፉ፥ ቀኑንም የግብዣና የደስታ አደረጉት።
18በሱሳ ይኖሩ የነበሩ አይሁድ ግን በአሥራ ሦስተኛውና በአሥራ አራተኛው ቀን በአንድ ላይ ተሰባሰቡ። በአሥራ አምስተኛው ቀን ዐረፉ፥ የግብዣና የደስታም ቀን አደረጉት።
19በገጠር ከተሞች የሚኖሩ የመንደሩ አይሁድ የአዳርን ወር አሥራ አራተኛውን ቀን የግብዣና የደስታ ቀን አድርገው የሚያከብሩትና እርስ በርሳቸው የምግብ ስጦታ መለዋወጫ ቀን ያደረጉት ለዚህ ነው።
20መርዶክዮስ እነዚህን ነገሮች ሁሉ በመጻፍ በንጉሥ አርጤክስስ አውራጃዎች ሁሉ በቅርብና በሩቅ ለሚኖሩ አይሁዶች በሙሉ በየዓመቱ በአዳር ወር
21አሥራ አራተኛውንና አሥራ አምስተኛውን ቀን እንዲጠብቁት በማዘዝ ደብዳቤዎችን ጻፈላቸው።
22እነዚህ ቀናት አይሁድ ከጠላቶቻቸው ያረፉባቸው፥ ሀዘናቸው ወደ ደስታ፥ ልቅሶአቸውም ወደ ደስታ በዓል የተለወጠባቸው ቀናት ነበሩ። እነርሱም ቀኖቹን የግብዥና የደስታ፥ ለእርስ በርሳቸውም የምግብ ስጦታ የሚለዋወጡበት፥ ለድሆችም ስጦታ የሚያበረክቱባቸው መሆን ነበረባቸው።
23ስለዚህ አይሁድ መርዶክዮስ በጻፈላቸው ደብዳቤ መሠረት የጀመሩትን በዓል ማክበራቸውን ቀጠሉ።
24በዚያን ጊዜ የአይሁዶች ሁሉ ጠላት፥ የሐመዳቱ ልጅ ሐማ፥ አይሁድን ለማጥፋት አሢሮ ነበር፥ ሊሰባብርና ሊያፈርሳቸውም ፉር የተባለውን ዕጣ ጥሎ ነበር።
25ጉዳዩ ወደ ንጉሡ ፊት በቀረበ ጊዜ ግን ሐማ በአይሁድ ላይ ያዘጋጀው ክፉ ዕቅድ በእርሱ በራሱ ላይ እንዲመለስበትና ወንዶች ልጆቹ በስቅላት እንዲቀጡ በደብዳቤ አዘዘ።
26ስለዚህ ፉር ከሚለው ስም በመነሣት አነዚህን ቀናት ፉሪም ብለው ጠሯቸው። በዚህ ደብዳቤ በተጻፉት፥ እነርሱም ባዩትና በደረሰባቸው ነገር ምክንያት አይሁድ አዲስ ልማድና አደራረግን ተቀበሉ።
27ይህም ልማድ ለእነርሱ፥ ለትውልዳቸውና እነርሱን ለተጠጋ ሁሉ የሚቀጥል ነበር። በየዓመቱ እነዚህ ሁለት ቀናት መከበር ነበረባቸው። ቀኖቹንም በየዓመቱ በተመሳሳይ ጊዜ፥ በአንድ ዓይነት መንገድ ማክበር ነበረባቸው። አነዚህ ቀኖች በየትውልዱ፥ በየቤተሰቡ፥ በየአውራጃውና በየከተማው መታሰብና መከበር ይኖርባቸዋል።
28እነዚህ አይሁዶችና ትውልዶቻቸው እነዚህን የፉሪም ቀናት ፈጽመው እንዳይረሷቸው፥ በታማኝነት መጠበቃቸውንም በፍጹም ማቋረጥ አይኖርባቸውም።
29የአቢካኢል ልጅ ንግሥት አስቴርና አይሁዳዊው መርዶክዮስ ስለ ፉሪም ይህንን ሁለተኛ ደብዳቤ በሙሉ ሥልጣን ጽፈው አጸኑት።
30በአርጤክስስ መንግሥት በ127 አውራጃዎች ውስጥ ለሚኖሩ አይሁድ በሙሉ ደኅንነትንና እውነትን የሚመኙላቸው ደብዳቤዎች ተጻፉላቸው።
31አይሁዳዊው መርዶክዮስና ንግሥት አስቴር አይሁድን እንዳዘዙት የፉሪም ቀናት በተወሰነላቸው ጊዜያት እንዲደረጉ እነዚህ ደብዳቤዎች አጸኑት። አይሁድ ልክ የጾሙንና የለቅሶውን ጊዜ አንደተቀበሉት ይህንን ትዕዛዝ ደግሞ ለራሳቸውና ለልጆቻቸው ተቀበሉት።
32ፉሪምን በሚመለከት የአስቴር ትዕዛዝ እነዚህን መመሪያዎች አጸና፥ እርሱም በመጽሐፍ ተጻፈ።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።