መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

አስቴር 8

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1በዚያም ቀን ንጉሡ አርጤክስስ የአይሁዶችን ጠላት፥ የሐማን ንብረት፥ ለንግሥት አስቴር ሰጣት። መርዶክዮስ እንዴት እንደሚዛመዳት ለንጉሡ ነግራው ስለ ነበረ፥ መርዶክዮስ በንጉሡ ፊት ማገልገል ጀመረ።
2ንጉሡ ከሐማ መልሶ የወሰደውን ማኅተም ያለበትን ቀለበት አውልቆ ለመርዶክዮስ ሰጠው። አስቴርም መርዶክዮስን በሐማ ይዞታ ላይ ኃላፊ አድርጋ ሾመችው።
3ከዚያም አስቴር ንጉሡን ደግማ ተናገረችው። እርሷም በምድር ላይ ተደፍታ አጋጋዊው ሐማ በአይሁድ ላይ ያሴረውን የጥፋት ዕቅድ ማብቂያ እንዲያደርግለት እያለቀሰች ለመነችው።
4ከዚያም ንጉሡ የወርቁን በትረ መንግሥት ለአስቴር ዘረጋላት። እርሷም ተነሥታ በንጉሡ ፊት ቆመች።
5እርሷም፥ "ንጉሡን ደስ የሚለው ከሆነና በፊትህ ሞገስን ካገኘሁ፥ ነገሩም በንጉሡ ፊት ትክክል መስሎ ከታየውና እኔም በዓይንህ ፊት ተወድጄ ከሆነ፥ በአጋጋዊው በሐመዳቱ ልጅ በሐማ የተጻፈውን፥ በንጉሡ አውራጃዎች ሁሉ የሚኖሩትን አይሁድ ለማጥፋት የጻፈውን ድብዳቤ የሚሽር አዋጅ ይጻፍ።
6በሕዝቤ ላይ የሚደርሰውን እልቂት ለማየት እንዴት መታገሥ እችላለሁ? የዘመዶቼን ጥፋት መመልከቱንስ እንዴት መቋቋም እችላለሁ?" አለችው።
7ንጉሥ አርጤክስስ ንግሥት አስቴርንና አይሁዳዊውን መርዶክዮስን፥ "ተመልከቱ፥ የሐማን ቤት ለአስቴር ሰጠኋት፥ አይሁድን ሊያጠቃ ስለነበርም እርሱን በመስቀያው ላይ ሰቀሉት።
8ለአይሁዶች በንጉሡ ስም ሌላ ዐዋጅ ጻፉ፥ በንጉሡም የቀለበት ማኅተም አትሙበት። ቀደም ሲል በንጉሡ ስም የተጻፈውና በንጉሡ ቀለበት የታተመው ዐዋጅ ሊሻር አይቻልምና።"
9በሦስተኛው ወር፥ እርሱም የኒሳን ወር ነው፥ ከወሩም በሃያ ሦስተኛው ቀን በዚያን ጊዜ የንጉሡ ጸሐፊዎች ተጠርተው ነበር። ዐዋጁም አይሁድን በሚመለከት መርዶክዮስ ያዘዘው ሁሉ ተካትቶ ተጽፎበት ነበር። ለየአውራጃው አስተዳዳሪዎች ተጽፎ ነበር፥ ከህንድ እስከ ኢትዮጵያ ለሚዋሰኑት 127 የአውራጃ አስተዳዳሪዎችና አለቆች፥ ለእያንዳንዱ አውራጃ በየራሱ ጽሑፍና ለእያንዳንዱ ሕዝብ በየራሱ ቋንቋ፥ ደግሞም ለአይሁድ በራሳቸው ጽሑፍና ቋንቋ ተጻፈ።
10መርዶክዮስ በንጉሥ አርጤክስስ ስም ጽፎ በንጉሡ የቀለበት ማኅተም አተመው። ደብዳቤዎቹንም ለንጉሡ አገልግሎት በሚውሉና ለዚሁ በተገሩ ፈጣን ፈረሶች በሚጋልቡ መልዕክተኞች ላከው።
11በየከተማው ያሉ አይሁዶች በአንድ ላይ እንዲሰባሰቡና ሕይወታቸውን እንዲከላከሉ፤ ልጆችንም ሆነ ሴቶችን ጨምሮ ከየትኛውም ሕዝብም ሆነ አውራጃ እነርሱን ለማጥቃት መሣሪያ የሚያነሣውን ኃይል ሁሉ እንዲያጠፉ፥ እንዲገድሉና እንዲደመስሱ ንብረታቸውንም እንዲበዘብዙ ንጉሡ ፈቃድ ሰጣቸው።
12ይህ በንጉሥ አርጤክስስ አውራጃዎች ሁሉ በአሥራ ሁለተኛው ወር፥ እርሱም አዳር የሚባለው ወር ነው፥ በአሥራ ሦስተኛው ቀን ተግባራዊ የሚደረግ ነበር።
13የዐዋጁ ቅጅ ሕግ ሆኖ በመውጣት ሕዝብ ሁሉ እንዲያውቀው ተደረገ። አይሁድ በዚያን ቀን ጠላቶቻቸውን ለመበቀል ዝግጁዎች መሆን ነበረባቸው።
14ስለዚህ መልዕክተኞቹ ለንጉሡ አገልግሎት በሚውሉ የቤተመንግሥት ፈረሶች ላይ ተቀመጡባቸው። እነርሱም ፈጥነው ሄዱ። ደግሞም የንጉሡ ዐዋጅ ከሱሳ ቤተመንግሥት ተነገረ።
15ከዚያም መርዶክዮስ ንጭና ሰማያዊ የክብር ልብስ ለብሶ፥ ታላቅ የወርቅ አክሊልም ደፍቶ፥ ከሐምራዊና ከጥሩ የተልባ እግር የተሠራ መጎናጸፊያ ደርቦ ከንጉሡ ፊት ወጣ። የሱሳ ከተማም ደስ አላት፥ እልልም አለች።
16ለአይሁድም ብርሃንና ፈንጠዚያ፥ ደስታና ክብር ሆነላቸው።
17የንጉሡ ዐዋጅ በደረሰበት ሁሉ፥ በየአውራጃውና በየከተማው በአይሁድ መካከል ደስታና ፈንጠዚያ፥ ግብዣና በዓል ሆነ። አይሁድን መፍራት በላያቸው ላይ ወድቆ ስለነበረ በምድሩ ከሚኖሩ ልዩ ልዩ ሕዝቦች ብዙዎቹ አይሁድ ሆኑ።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።