መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

አስቴር 6

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1በዚያ ሌሊት ንጉሡ እንቅልፉን መተኛት አልቻለም። እርሱም በዘመነ መንግሥቱ የተከናወኑ ሁነቶች በታሪክነት የተመዘገቡበትን መዝገብ እንዲያመጡለት አገልጋዮቹን አዘዛቸው፥ እነርሱም ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ለንጉሡ ያነቡለት ነበር።
2ገበታና ታራ፥ ሁለቱ በር ጠባቂ የንጉሥ ሹሞች ንጉሥ አርጤክስስን ለመግደል ማቀዳቸውን መርዶክዮስ መናገሩ ተመዝግቦ ተገኘ።
3ንጉሡም፥ "ይህንን ስላደረገ ለመርዶክዮስ ክብርና እውቅና ለመስጠት ምን ተደረገለት?" ብሎ ጠየቀ። ከዚያም ንጉሡን የሚያገለግሉ ወጣቶች፥ "ምንም አልተደረገለትም" አሉት።
4ንጉሡም፥ "በአደባባዩ ውስጥ ያለው ማነው?" አለ። በዚያን ጊዜ ሐማ መርዶክዮስን ባዘጋጀለት መስቀል ላይ ለማሰቀል ለንጉሡ ለመንገር ወደ ውጪኛው አደባባይ ገብቶ ነበር።
5የንጉሡም አገልጋዮች፥ "ሐማ አደባባዩ ውስጥ ቆሟል" አሉት። ንጉሡም፥ "ይግባ" አለ።
6ሐማ በገባ ጊዜም ንጉሡ፥ "ንጉሥ ሊያከብረው ለሚወደው ሰው ምን ይደረግለት?"አለው። ሐማም በልቡ፥"ከእኔ የበለጠ ንጉሡ ሊያከብረው የሚወደው ማን ይኖራል?" ብሎ አሰበ።
7ሐማም ንጉሡን፥ "ንጉሡ ሊያከብረው ለሚወደው ሰው፥
8ንጉሡ ይለብሰው የነበረ ንጉሣዊ ልብስ ይምጣለት፥ ንጉሡ ይቀመጥበት የነበረና በራሱ ላይ የክብር ጌጥ የተደረገለት ፈረስ ይምጣለት።
9ከዚያም ልብሶቹና ፈረሱ ከንጉሡ ሹማምንት እጅግ በተመረጡት በአንደኛው እጅ ይሰጡ፥ እነርሱም ንጉሡ ሊያከብረው የወደደውን ሰው ያልብሱት፥ በፈረሱ ላይ በማስቀመጥም በከተማው ዋና ዋና ጎዳናዎች ይምሩት፥ በፊቱም "ንጉሡ ሊያከብረው ለሚወደው ሰው የሚደረግለት እንዲህ ነው!" እያሉ ያውጁ" አለ።
10ከዚያም ንጉሡ ሐማን፥ "ፍጠን፥ እንደተናገርከው ልብሶቹንና ፈረሱን ውሰድ፥ በንጉሡ በር ለሚቀመጠው ለአይሁዳዊው ለመርዶክዮስ ይህንኑ አድርግለት። ከተናገርከውም አንድ አንዳይጎድል" አለው።
11ከዚያም ሐማ ልብሱንና ፈረሱን ወሰደ። መርዶክዮስን አልብሶና ፈረስ ላይ አስቀምጦ በከተማው ዋና ዋና ጎዳናዎች አዟዟረው። በፊቱም፥ "ንጉሡ ሊያከብረው ለሚወደው ሰው የሚደረግለት እንዲህ ነው!" እያለ ዐወጀ።
12መርዶክዮስ ወደ ንጉሡ በር ተመለሰ። ሐማ ግን ፊቱን ሸፍኖና አዝኖ በጥድፊያ ወደ ቤቱ ሄደ።
13ሐማም ለሚስቱ ለዞሳራና ለጓደኞቹ ሁሉ የገጠመውን ነገር በሙሉ ነገራቸው። በጥበባቸው የታወቁት ሰዎቹና ምስቱ ዞሳራም፥ "በፊቱ መውደቅ የጀመርከለት መርዶክዮስ አይሁዳዊ ከሆነ በርግጥ በፊቱ ትወድቃለህ እንጂ አታሸንፈውም" አሉት።
14ከእርሱ ጋር እየተነጋገሩ እያሉ የንጉሡ ሹማምንት መጡ። እነርሱም አስቴር ወዳዘጋጀችው ግብዣ ሐማን አቻኮሉት።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።