1ከሥስት ቀን በኋላ አስቴር የንግሥትነትዋን ልብስ ለብሳ በንጉሡ መኖሪያ ፊት ለፊት፥ በንጉሡ ቤተመንግሥት ውስጠኛው አደባባይ ልትቆም ሄደች። ንጉሡም በቤቱ መግቢያ በር ትይዩ በንጉሣዊ ዙፋኑ ላይ ተቀምጦ ነበር።
2ንጉሡ ንግሥት አስቴርን አደባባዩ ላይ ቆማ ባያት ጊዜ፥ በፊቱ ሞገስን አገኘች። እርሱም የወርቁን በትር አንስቶ ዘረጋላት። ስለዚህ አስቴር ቀረበችና የበትሩን ጫፍ ነካች።
3ከዚያም ንጉሡ፥ "ንግሥት አስቴር! ምንድነው የምትፈልጊው? ጥያቄሽስ ምንድነው? የመንግሥቴን ግማሽ ከሆነም ይሰጥሻል።"
4አስቴርም፥ "ንጉሡን ደስ የሚለው ከሆነ ንጉሡ ከሐማ ጋር ወዳዘጋጀሁለት ግብዣ ዛሬ ይምጣ" አለችው።
5ከዚያም ንጉሡ፥ "አስቴር ያለችው እንዲደረግ፥ በአስቸኳይ ሐማን ጥሩት" አለ። ስለዚህ ንጉሡና ሐማ አስቴር ወዳዘጋጀችው ግብዣ ሄዱ።
6በግብዣው ላይ ወይኑ እየቀረበ እያለ ንጉሡ አስቴርን፥ "ልመናሽ ምንድነው? ይሰጥሻል። ጥያቄሽ ምንድነው? እስከ መንግሥቴ ግማሽ ይሰጥሻል" አላት።
7አስቴርም፥ "በንጉሡ ዓይን ሞገስን ካገኘሁ፥
8የለመንኩትን ሊሰጠኝና ጥያቄዬን ሊያከብርልኝ ንጉሡን ደስ የሚለው ከሆን ልምናዬና ጥያቄዬ ይህ ነው። ነገ በማዘጋጅልህ ግብዣ ላይ ንጉሡ ከሐማ ጋር ይምጣ፥ እኔም የንጉሡን ጥያቄ እመልሳለሁ" አለችው።
9ሐማ በዚያን ቀን ደስ ብሎት፥ ልቡም ሐሴት አድርጎ ሄደ። ነገር ግን ሐማ መርዶስዮስን በፊቱ ሳይፈራና ሳይንቀጠቀጥ፥ ከተቀመጠበትም ሳይነሳ በንጉሡ በር ባየው ጊዜ በመርዶክዮስ ላይ እጅግ ተናደደ።
10ሆኖም ሐማ ራሱን ተቆጣጠረና ወደ ራሱ ቤት ሄደ።
11ጓደኞቹን አስጠራና ከሚስቱ ዞሳራ ጋር በአንድ ላይ ሰበሰባቸው። ሐማም የብልጽግናውን ክብርና የልጆቹን ብዛት፥ ከንጉሡ አገልጋዮችና ከሹማምንቱ ሁሉ በላይ እንዴት በማዕረግ አንደበለጣቸው አወራላቸው።
12ሐማም፥ "ንግሥት አስቴር ወዳዘጋጀችው ግብዣ እንኳን ከእኔ በቀር ከንጉሡ ጋር እንዲመጣ የጋበዘችው የለም። ነገም ደግሞ ከንጉሡ ጋር ግብዣዋ ላይ እንድገኝ ጋብዛኛለች።
13ነገር ግን አይሁዳዊው መርዶክዮስ በንጉሡ በር ተቀምጦ ካየሁት ይህ ሁሉ ልምምዴ ምንም አይጠቅመኝም።"
14ከዚያም ሚስቱ ዞሳራ ሐማንና ጓደኞቹን ሁሉ፥ "ቁመቱ ሃምሳ ክንድ የሆነ መስቀያ ያዘጋጁ። መርዶክዮስን በዚያ ላይ እንዲሰቅሉት ነገ ጠዋት ለንጉሡ ንገረው። ከዚያም ደስ ብሎህ ከንጉሡ ጋር ወደ ግብዣው ሂድ" አለቻቸው። ይህም ሐማን አስደሰተው፥ መስቀያው እንዲዘጋጅም አስደረገ።