1ከእነዚህ ነገሮች በኋላ ንጉሡ አርጤክስስ አጋጋዊውን የሐመዳቱን ልጅ ሐማን በሹመት አላቀው፥ የሥልጣኑንም ወንበር ከእርሱ ጋር ከነበሩት ሹማምንት ሁሉ በላይ አደረገለት።
2በንጉሡ በር የሚጠብቁ የንጉሡ አገልጋዮች ሁሉ ንጉሡ በሰጣቸው ትዕዛዝ መሠረት ሁልጊዜ ለሐማ በመንበርከክ አክብሮታቸውን ያሳዩት ነበር። መንዶክዮስ ግን አልተንበረከከለትም፥ አክብሮትም አላሳየውም።
3ከዚያም በንጉሡ በር የሚጠብቁት የንጉሡ አገልጋዮች መርዶክዮስን፥ "የንጉሡን ትዕዛዝ የማታከብረው ለምንድነው?" አሉት።
4ይህንን በየቀኑ ቢናገሩትም እርሱ ግን ቃላቸውን ለመቀበል እምቢ አለ። አይሁዳዊ መሆኑን ነግሯቸው ስለነበረ መርዶክዮስ በዚህ ሁኔታ እንዴት እንደሚቀጥል ለማየት ጉዳዩን ለሐማ ነገሩት።
5ሐማም መርዶክዮስ ተንበርክኮ እንዳልሰገደለት ባየ ጊዜ ሐማ በንዴት ተሞላ።
6የመርዶክዮስን የዘር ማንነት የንጉሡ አገልጋዮች ነግረውት ስለ ነበረ መርዶክዮስን ብቻ የመግደልን ሃሳብ ናቀው። በመላው አርጤክስስ መንግሥት ውስጥ የነበሩትን የመርዶክዮስ ወገን የሆኑትን አይሁድ በሙሉ ለመደምሰስ ፈለገ።
7ንጉሡ አርጤክስስ በነገሠ በአሥራ ሁለተኛው ዓመት፥ በመጀመሪያው ወር (እርሱም የኒሳን ወር ነው) ፥ ፉር የሚባለውን፥ ቀኑንና ወሩን ለመምረጥ የሚያስችላቸውን የእያንዳንዱን ቀንና ወር ዕጣ በሐማ ፊት ጣሉ። በዕጣው መሠረት የአዳርን (አሥራ ሁለተኛውን ወር) መረጡ።
8ከዚያም ሐማ ንጉሡን አርጤክስስን፥ "በመንግሥትህ አውራጃዎች ሁሉ ተበታትኖና ተሠራጭቶ የሚኖር አንድ ሕዝብ አለ። ሕጋቸው ከሌላው ሕዝብ የተለየ ነው፥ የንጉሡንም ሕጎች አያከብሩም፥ ስለዚህ ንጉሡ በሕይወት እንዲኖሩ ሊተዋቸው አይገባውም።
9ንጉሡ ደስ የሚለው ከሆነ እንዲገደሉ ትዕዛዝ ይስጥ፥ እኔም ወደ ንጉሡ ግምጃ ቤት ገቢ እንዲያደርጉት በንጉሡ ንብረት ኃላፊዎች በሆኑት እጅ አሥር ሺህ መክሊት ብር መዝኜ እሰጣለሁ"አለው።
10ከዚያም ንጉሡ ማኅተም ያለበትን ቀለበት ከጣቱ አውልቆ ለአይሁዶቹ ጠላት፥ ለአጋጋዊው ለሐመዳቱ ልጅ ለሐማ ሰጠው።
11ንጉሡም ሐማን፥ "ገንዘቡ ለአንተና ለሕዝብህ ተመልሶ ማየት እፈልጋለሁ። አንተም በእርሱ የፈለግኸውን ሁሉ ታደርግበታለህ" አለው።
12ከዚያም በመጀመሪያው ወር በአሥራ ሦስተኛው ቀን የንጉሡ ጸሐፊዎች ተጠሩ፥ ለንጉሡ የአውራጃ አስተዳዳሪዎች፥ በአውራጃዎቹ ሁሉ ላይ ለነበሩት፥ ልዩ ልዩ ሕዝቦችን ለሚያስተዳድሩትና ለሕዝቡ ሁሉ ሹማምንት፥ ለየአውራጃዎቹ በየራሳቸው ጽሑፍና ለእያንዳንዱም ሕዝብ በየራሱ ቋንቋ ሐማ ያዘዘው ሁሉ በዐዋጁ ውስጥ ተጻፈ። ዐዋጁም በንጉሡ አርጤክስስ ስም ተጽፎ በቀለበቱ ታተም።
13በአሥራ ሁለተኛው ወር (እርሱም የአዳር ወር ነው) ፥ በአሥራ ሦስተኛው ቀን፥ በአንድ ቀን ውስጥ አይሁዶችን በሙሉ፥ ከወጣት እስከ ሽማግሌ፥ ልጆችንና ሴቶችን በአንድ ቀን እንዲያጠፉ፥ እንዲገድሉና እንዲደመስሱና ንብረታቸውንም እንዲዘርፉ ደብዳቤዎቹም በመልዕክተኞቹ እጅ ለንጉሡ አውራጃዎች ሁሉ ተላከ።
14የደብዳቤው ቅጅም በየአውራጃው ሕግ ተደረገ። ለዚያ ቀን ይዘጋጁ ዘንድ በየአውራጃው ያሉ ሕዝቦች ሁሉ እንዲያውቁት ተደረገ።
15መልዕክተኞቹም የንጉሡን ዐዋጅ ለማሰራጨት በጥድፊያ ሄዱ። አዋጁ በሱሳ ቤተመንግሥት ውስጥም ደግሞ ተሰራጨ። ንጉሡና ሐማ ለመጠጣት ተቀመጡ፥ የሱሳ ከተማ ግን ተበጥብጣ ነበር።