መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

አስቴር 2

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ከእነዚህ ነገሮች በኋላ የንጉሡ አርጤክስስ ቁጣ በበረደለት ጊዜ ንግሥት አስጢንን፥ እርሷም ያደረገችውን አሰበ። እንዲሁም በእርሷ ላይ ያስተላለፈውን የፍርድ ውሳኔ አሰበ።
2ከዚያም ያገለግሉት የነበሩት የንጉሡ ወጣቶች፥ "የተዋቡ ልጃገረዶች ለንጉሡ ይፈለጉለት።
3የተዋቡ ልጃገረዶችን በሙሉ በሱሳ ቤተመንግሥት ወደሚገኘው የሴቶች መኖሪያ እንዲሰበስቧቸው በመንግሥቱ አውራጃዎች ሁሉ ንጉሡ ኃላፊዎችን ይሹም። እነርሱም የሴቶች ኃላፊ በሆነው የንጉሡ ሹም በሄጌ ጥበቃ ሥር ይደረጉ፥ እርሱም መዋቢያዎቻቸውን ይስጣቸው።
4ንጉሡን ደስ የምታሰኘው ልጃገረድ በአስጢን ፈንታ ንግሥት ትሁን።" ይህም ምክር ንጉሡን አስደሰተው፥ እርሱም እንደዚሁ አደረገ።
5በሱሳ ከተማ መርዶክዮስ የሚባል አንድ አይሁዳዊ ነበር፥ እርሱም ብንያማዊ ሲሆን የቂስ ልጅ፥ የሰሜኢ ልጅ፥ የኢያዕር ልጅ ነበር።
6እርሱም የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ከማረከው ከይሁዳ ንጉሥ ከኢኮንያን ጋር ተማርከው ከተወሰዱት ምርኮኞች ጋር ከኢየሩሳሌም ተወስዶ ነበር።
7እርሱም አባትም ሆነ እናት አልነበራትምና የአጎቱን ልጅ ሀደሳ የተባለችውን አስቴርን ያሳድግ ነበር። ልጃገረዲቱም የተዋበ ተክለሰውነትና ማራኪ ገጽታ ነበራት። መርዶክዮስ እንደ ራሱ ልጅ አድርጎ ወስዷት ነበር።
8የንጉሡ መመሪያና ትዕዛዝ በታወጀ ጊዜ ብዙ ልጃገረዶችን ወደ ሱሳ ቤተመንግሥት ሰበሰቧቸው። እነርሱም ከሄጌ ጥበቃ ሥር ተደረጉ። አስቴርም ደግሞ ወደ ቤተመንግሥቱ ተወስዳ ከሴቶቹ ተቆጣጣሪ ከሄጌ ሥር ተደረገች።
9ልጃገረዲቱ ደስ አሰኘችው፥ በፊቱም ሞገስን አገኘች። ወዲያውም የምግብ ድርሻዋንና መዋቢያዎቿን ሰጣት። ለእርሷም ከንጉሡ ቤተመንግሥት የሚያገለግሏትን ሰባት ልጃገረዶች መደበላት፥ እርሷንና የሚያገለግሏትን ልጃገረዶች በሴቶቹ መኖሪያ ውስጥ ወደ ተሻለው ክፍል አዛወራቸው።
10መርዶክዮስ እንዳትናገር አዝዟት ስለ ነበር፥ አስቴር ሕዝቧንም ሆነ ወገንዋን ለማንም አልተናገረችም ነበር።
11መርዶክዮስ የአስቴርን ደኅንነትና ያለችበትን ሁኔታ ለማወቅ በየዕለቱ በሴቶቹ መኖሪያ በስተውጭ ባለው አደባባይ ይመላለስ ነበር።
12እያንዳንዷ ልጃገረድ ወደ ንጉሡ አርጤክስስ የምትሄድበት ተራ በደረሰ ጊዜ - ለሴቶቹ በወጣው ደንብ መሠረት እያንዳንዷ ልጃገረድ ስድስት ወር በከርቤ ዘይት፥ ስድስት ወር ደግሞ በሽቶዎችና በመዋቢያዎች ለአሥራ ሁለት ወራት የውበት አያያዝ ጊዜአቸውን ማጠናቀቅ ነበረባቸው -
13አንዲት ልጃገረድ ወደ ንጉሡ በምትሄድበት ጊዜ ወደ ቤተመንግሥት እንድትወስደው የፈለገችው ሁሉ ከሴቶቹ መኖሪያ ይሰጣት ነበር።
14ሲመሽ ትገባና ሲነጋ ወደ ሁለተኛው የሴቶች መኖሪያ፥ በቁባቶቹ ላይ ኃላፊ ወደሆነው የንጉሥ ሹም ወደ ሻአሽጋዝ ጥበቃ ሥር ትመለስ ነበር። ንጉሡ ተደስቶባት ዳግም ካልጠራት በስተቀር ሁለተኛ ወደ እርሱ መመለስ አትችልም ነበር።
15ወደ ንጉሡ ለመግባት የአስቴር (መርዶክዮስ እንደ ራሱ ልጅ አድርጎ የወሰዳት የአቢካኤል ልጅ) ተራ በደረሰ ጊዜ በሴቶች ላይ ኃላፊ የሆነው የንጉሡ ሹም ሄጌ ከነገራት በቀር ምንም ነገር አልጠየቀችም። አስቴርም በሚያዩዋት ሁሉ ፊት ሞገስን ታገኝ ነበር።
16አስቴርም ንጉሡ አርጤክስስ በነገሠ በሰባተኛው ዓመት፥ ቴቤት ተብሎ በሚጠራው በአሥረኛው ወር፥ ወደ ንጉሣዊ መኖሪያው ተወሰደች።
17ንጉሡም ከሌሎቹ ሴቶች ሁሉ ይልቅ አስቴርን ወደዳት፥ ከደናግሉም ሁሉ ይልቅ በፊቱ ሞገስንና መወደድን አገኘች፥ ስለዚህ የእቴጌነትን ዘውድ በራሷ ላይ አደረገላት፥ በአስጢንም ምትክ ንግሥት አደረጋት።
18ንጉሡም "የአስቴር ግብዣ" ብሎ የጠራውን ታላቅ ግብዣ ለሹማምንቱና ለአገልጋዮቹ ሁሉ አደረገ፥ አውራጃዎቹንም ከቀረጥ አሳረፋቸው። ደግሞም በንጉሣዊ ልግስናው ስጦታዎችን ሰጠ።
19ደናግሎቹ ለሁለተኛ ጊዜ በተሰበሰቡ ጊዜ መርዶክዮስ በንጉሡ በር ይቀመጥ ነበር።
20አስቴር ሕዝቧን ወይም ወገኗን መርዶክዮስ ባዘዛት መሠረት ገና ለማንም አልተናገረችም ነበር። እርሷም በልጅነትዋ ጊዜ ታደርግ አንደነበረው የመርዶክዮስን ምክር መከተልዋን ቀጠለች።
21በእነዚያም ቀናት መርዶክዮስ በንጉሡ በር ተቀምጦ እያለ በሩን ይጠብቁ የነበሩት ሁለቱ የንጉሡ ሹማምንት ገበታና ታራ ተቆጡ፥ ንጉሡን አርጤክስስንም ለመግደል ፈለጉ።
22መርዶክዮስ ጉዳዩን ባወቀ ጊዜ ለንግሥት አስቴር ነገራት፥ እርሷም በመርዶክዮስ ስም ለንጉሡ ነገረችው።
23መረጃው ሲመረመር እውነት ሆኖ ተገኝ፥ ሁለቱም ሰዎች በስቅላት ተቀጡ። ታሪኩም በንጉሡ ፊት በታሪክ መዝገብ ላይ ተጻፈ።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።