መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

አስቴር 1

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1በአርጤክስስ ዘመን (እርሱም ከህንድ እስከ ኢትዮጵያ ድረስ በአንድ መቶ ሃያ ሰባት አገሮች የነገሠው ነው)
2በእነዚያ ጊዜያት ንጉሡ አርጤክስስ በሱሳ ግንብ ውስጥ ባለው የመንግሥቱ ዙፋን ላይ ተቀመጠ።
3በነገሠ በሦስተኛው ዓመት ለሹማምንቱና ለአገልጋዮቹ በሙሉ ግብዣ አደረገላቸው። የፋርስና የሜዶን የጦር አዛዦች፥ ባላባቶችና የአውራጃ አስተዳዳሪዎችም በፊቱ ነበሩ።
4የመንግሥቱን ውበት ባለጸግነትና የግርማውን ክብር ታላቅነት ለብዙ ቀናት ማለትም ለ180 ቀናት አስጎበኛቸው።
5እነዚህ ቀናት ካበቁ በኋላ ንጉሡ ለሰባት ቀናት የሚቆይ ግብዣ አዘጋጀ። ግብዣው የተዘጋጀው ከታላቁ ጀምሮ እስከ ታናሹ ድረስ በሱሳ ቤተመንግሥት ውስጥ ለነበሩት ሰዎች ሁሉ ነበር። ይህም የተደረገው በንጉሡ ቤተመንግሥት መናፈሻ በሚገኘው አደባባይ ውስጥ ነበር።
6ከጥጥ የተሠሩ ነጭና ሰማያዊ መጋረጃዎች ነጭና ሐምራዊ ገመድ በብር ቀለበቶቹ ውስጥ አልፈው በእምነበረዱ ቋሚዎች ላይ በመሰቀላቸው የመናፈሻው አደባባይ ተውቦ ነበር። በቀይ ዓለት፥ በእምነበረድ፥ በእንቁ እናትና የተለያየ ቀለም ባላቸው የንጣፍ ድንጋዮች ባሉት ሥዕላዊ ወለል ላይ የወርቅና የብር ድንክ አልጋዎች ነበሩ።
7መጠጡ በወርቃማ መጠጫዎች ይቀርብ ነበር። እያንዳንዱ መጠጫ የተለያየ ነበር፥ ከንጉሡ ለጋስነት የተነሣም የቤተመንግሥቱ ወይን የተትረፈረፈ ነበር።
8መጠጡ ይቀርብ የነበረውም፥ "ግዴታ መኖር የለበትም" የሚለውን መመሪያ በመከተል ነበር። እንግዶቹ እያንዳንዳቸው በሚፈልጉት መጠን እንዲቀርብላቸው ንጉሡ የቤተመንግሥቱን ሠራተኞች አዝዞ ነበር።
9ንግሥት አስጢን በበኩሏ በንጉሡ አርጤክስስ ንጉሣዊ ቤተመንግሥት ለሴቶች ግብዣ አደረገች።
10በሰባተኛው ቀን ንጉሡ ከወይን ጠጅ የተነሣ ልቡን ደስታ በተሰማው ጊዜ ምሁማንን፥ ባዛንን፥ ሐርቦናን፥ ገበታን፥ ዘቶልታን፥ ዜታርንና ከርከስን (በፊቱ የሚያገለግሉትን ሰባቱን ሹማምንት) ንግሥት አስጢን ዘውዷን ደፍታ በፊቱ እንድትቀርብ አዘዛቸው።
11ተክለ ሰውነቷ ያማረ ነበርና ውበቷን ለሕዝቡና ለሹማምንቱ ለማሳየት ፈለገ።
12ንግሥት አስጢን ግን ንጉሡ በሹማምንቱ በላከባት ቃል መሠረት ለመምጣት እምቢ አለች። ከዚያም ንጉሡ በጣም ተቆጣ፥ ቁጣውም በውስጡ ነደደ።
13ስለዚህ ንጉሡ ዘመኑን ከሚመረምሩ ጥበበኞች ሰዎች ጋር ተመካከረ (ሕግንና ዳኝነትን ስለሚያውቁት ሰዎች ሁሉ የንጉሡ ልምድ እንዲህ ነበርና) ።
14የቅርቦቹ የነበሩትም ሰባቱ የፋርስና የሜዶን መሳፍንት የሆኑት አርቄስዮስ፥ ሼታር፥ አድማታ፥ ተርሺሽ፥ ሜሬስ፥ ማሌሴዓርና ምሙካን ነበሩ። እነዚህ ለንጉሡ የሚቀርቡና በመንግሥቱ ውስጥ ከፍተኛውን ሥልጣን የያዙ ናቸው።
15"በሹማምንቱ የተላከባትን የንጉሡን የአርጤክስስን ትዕዛዝ አልታዘዘችምና በሕጉ መሠረት በንግሥት አስጢን ላይ መደረግ ያለበት ምንድነው?"
16ምሙካንም በንጉሡና በመኳንንቱ ፊት እንዲህ አለ፥ "ንግሥቲቱ አስጢን የበደለችው መኳንንቱን ሁሉና በንጉሡ በአርጤክስስ ግዛቶች ሁሉ የሚገኘውን ሕዝብ በሙሉ ደግሞ እንጂ ንጉሡን ብቻ አይደለም።
17የንግሥቲቱ ጉዳይ በሁሉም ሴቶች የሚታወቅ ይሆናል። ይህም ባሎቻቸውን እንዲንቁ ያደርጋል። እነርሱም፥ 'ንግሥት አስጢንን በፊቱ እንዲያቀርቧት ንጉሡ አርጤክስስ አዘዘ፥ እርስዋ ግን እምቢ አለች' ይላሉና።
18የንግሥቲቱን ጉዳይ የሰሙ የመኳንንቱ ሚስቶችም ይህ ቀን ከማለፉ በፊት ለንጉሡ መካንንቶች በሙሉ ተመሳሳዩን ቃል ይናገራሉ። ብዙ ንቀትና ቁጣም ይሆናል።
19ንጉሡን ደስ የሚለው ከሆነ፥ አስጢን ዳግመኛ በፊቱ እንዳትቀርብ ንጉሣዊ ትዕዛዝ ያውጣ፥ ሊለወጥ የማይቻል ሆኖም በፋርስና በሜዶን ሕግ ውስጥ ይጻፍ። የንግሥትነቷን ክብርም ንጉሡ ክእርስዋ ለምትሻል ለሌላይቱ ይስጥ።
20የንጉሡ ትዕዛዝ በሰፊው መንግሥቱ ሁሉ በሚታወጅበት ጊዜ፥ ከታላቁ እስከ ታናሹ ድረስ ሚስቶች ሁሉ ባሎቻቸውን ያከብራሉ።"
21ንጉሡና መካንንቶቹ በዚህ ምክር ተደሰቱ፥ ንጉሡም የምሙካንን ምክር ተግባራዊ አደረገው።
22እርሱም ደብዳቤዎችን ለእያንዳንዱ አውራጃ በየራሱ ጽሕፈትና ለእያንዳንዱ ሕዝብ በየራሱ ቋንቋ አድርጎ ወደ መንግሥቱ አውራጃዎች በሙሉ ላከው። እርሱም እያንዳንዱ በቤተሰቡ ላይ ገዥ እንዲሆን አዘዘ። ይህም ትዕዛዝ በመንግሥቱ ውስጥ ላለ ለእያንዳንዱ ሕዝብ በየቋንቋው ተሰጠው።
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።