1በዚህ ምክንያት አሕዛብ ስለሆናችሁት ስለ እናንተ እኔ ጳውሎስ የክርስቶስ ኢየሱስ እስረኛ ሆኛለሁ።
2ለእናንተ ጥቅም ሲባል ስለ ተሰጠኝ የእግዚእብሔር ጸጋ መጋቢነት ሰምታችኋል ብዬ አስባለሁ።
3ቀደም ሲል እንደጻፍሁላችሁ እግዚአብሔር የተሰወረውን ምስጢር በመገለጥ እንዳውቅ አድርጓል።
4ይህን በምታነቡበት ጊዜ ስለ ክርስቶስ ምስጢር እኔ ያለኝን መረዳት መገንዘብ ትችላላችሁ።
5ምስጢሩም አሁን በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት ለሓዋርያቱ እና ለነቢያቱ የተገለጠው ያህል ባለፉት ዘመናት ለነበሩ ሰዎች አልተገለጠም ነበር።
6ይህም ምስጢር አሕዛብ በወንጌል አማካይነት አብረው ወራሾች፥ አብረው የካሉ ብልቶች እንዲሁም በክርስቶስ በተገኘው ተስፋ አብረው ተካፋዮች መሆናቸው ነው።
7እንደ እርሱ ኀይል አሠራር በተሰጠኝ በእግዚአብሔር የጸጋ ስጦታ አገልጋይ ሆኛለሁ።
8ምንም እንኳ ከቅዱሳን ሁሉ ያነስሁ ብሆንም፥ የማይመረመረውን የክርስቶስ የባለጠግነት ወንጌል ለአሕዛብ እሰብክ ዘንድ ይህ ጸጋ ለእኔ ተሰጠኝ።
9እንዲሁም የሁሉን ነገር ፈጣሪ በሆነው በእግዚአብሔር ላለፉት ዘመናት ተሰውሮ ስለነበረው ምስጢር የእግዚአብሔር ዕቅድ ምን እንደሆነ ለሁሉም እገልጥ ዘንድ ተሰጠኝ።
10በዚህም ምክንያት በቤተ ክርስቲያን አማካይነት ብዙ ገጽታ ያለው የእግዚአብሔር ጥበብ በሰማያዊ ስፍራ ላሉት አለቆችና ባለ ሥልጣናት እንዲታወቅ ነው።
11ይህም የሆነው በጌታችን በክርስቶስ ኢየሱስ በፈጸመው ዘላለማዊ ዕቅዱ መሠረት ነው።
12በክርስቶስ በማመናችን በእርሱ ሆነን በድፍረትና በልበ ሙሉነት ወደ እግዚአብሔር መቅረብ እንችላለንና።
13ስለዚህ ክብራችሁ በሆነው ለእናንተ ስል በምቀበለው መከራ ተስፋ እንዳትቆርጡ እለምናችኋለሁ።
14በዚህም ምክንያት በአብ ፊት እንበረከካለሁ፤
15እርሱም በሰማይና በምድር ላለ ቤተ ሰብ ሁሉ ስያሜ የሰጠ እና እነርሱንም የፈጠረ ነው።
16የምጸልየውም ትጠነክሩ ዘንድ በውስጣችሁ በሚኖረው በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት እንደ ክብሩ ባለጠግነት መጠን ኀይል እንዲሰጣችሁ ነው።
17ይህም በእምነት ክርስቶስ በልባችሁ እንዲኖር፥ በፍቅሩ ሥር እንድትሰዱና እንድትታነጹ ነው፤
18ደግሞም የክርስቶስ ፍቅር ስፋቱ፥ርዝመቱ፥ከፍታውና ጥልቀቱ ምን ያህል እንደ ሆነ ከቅዱሳን ሁሉ ጋር መረዳት ትችሉ ዘንድ ነው።
19እንዲሁም በእግዚአብሔር ፍጹም ሙላት ሁሉ ትሞሉ ዘንድ ፥ ከሰው ዕውቀት ሁሉ በላይ የሆነውን የክርስቶስን ታላቅ ፍቅር እንድታውቁ ነው።
20እንግዲህ በእኛ ውስጥ እንደሚሠራው ሀይሉ መጠን ሁሉንም ነገር እኛ ከምንለምነው ወይም ከምናስበው በላይ እጅግ አብልጦ ማድረግ ለሚቻለው
21በቤተ ክርስቲያንና በክርስቶስ ኢየሱስ በትውልዶች ሁሉ ከዘላለም እስከ ዘላለም ለእርሱ ክብር ይሁን፤አሜን።